ኢሳይያስ 20 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ኢሳይያስ 20:1-6

በግብፅና በኢትዮጵያ ላይ የተነገረ ትንቢት

1ዋናው የጦር አዛዥ20፥1 ዋናው የጦር አዛዥ የሚለውን ዕብራይስጡ ተርታን ይለዋል። በአሦር ንጉሥ በሳርጎን ተልኮ፣ የአዛጦንን ከተማ ወርሮ በያዘበት ዓመት፣ 2በዚያ ጊዜ እግዚአብሔር የአሞጽን ልጅ ኢሳይያስን፣ “ማቁን ከሰውነትህ፣ ጫማህን ከእግርህ አውልቅ” ሲል ተናገረው። እርሱም እንዲሁ አደረገ፤ ዕርቃኑንና ባዶ እግሩን ተመላለሰ።

3ከዚያም እግዚአብሔር እንዲህ አለ፤ “ባሪያዬ ኢሳይያስ ሦስት ዓመት በግብፅና በኢትዮጵያ ለምልክትና ለማስጠንቀቂያ ዕርቃኑንና ባዶ እግሩን እንደ ሄደ፣ 4እንዲሁ የአሦር ንጉሥ ወጣትና ሽማግሌ የሆኑትን የተማረኩ ግብፃውያንንና የተሰደዱ ኢትዮጵያውያንን ዕርቃናቸውንና ባዶ እግራቸውን ይወስዳቸዋል፤ መቀመጫቸውን ገልቦ በመስደድም ግብፅን ያዋርዳል። 5በኢትዮጵያ ተስፋ ያደረጉ፣ በግብፅ የተመኩ ይፈራሉ፤ ይዋረዳሉም። 6በዚያ ቀን በዚህ ባሕር ዳርቻ የሚኖረው ሕዝብ፣ ‘የተመካንባቸው፣ ከአሦር ንጉሥ ለማምለጥና ነጻ ለመውጣት የተሸሸግንባቸው ምን እንደ ደረሰባቸው ተመልከቱ፤ እንግዲህ እኛስ እንዴት እናመልጣለን?’ ይላል።”