ኢሳይያስ 17 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ኢሳይያስ 17:1-14

በደማስቆ ላይ የተነገረ ንግር

1ስለ ደማስቆ የተነገረ ንግር፤

“እነሆ፤ ደማስቆ ከእንግዲህ ከተማነቷ ይቀራል፤

የፍርስራሽ ክምር ትሆናለች።

2የአሮኤር ከተሞች ባድማ ይሆናሉ፤

የመንጎች መሰማሪያ ይሆናሉ፤

የሚያስፈራቸውም የለም።

3የተመሸገ ከተማ ከኤፍሬም፣

የመንግሥት ሥልጣን ከደማስቆ ይወርዳል፤

የሶርያም ቅሬታ

እንደ እስራኤላውያን ክብር ይሆናል”

ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር

4“በዚያን ቀን የያዕቆብ ክብር ይደበዝዛል፤

የሰውነቱም ውፍረት ይሟሽሻል።

5ዐጫጅ የቆመውን ሰብል ሰብስቦ፣

ዛላውንም በክንዱ እንደሚያጭድ፣

ይህም በራፋይም ሸለቆ

እንደሚለቀም ቃርሚያ ይሆናል።

6ሆኖም የወይራ ዛፍ ሲመታ፣

ሁለት ወይም ሦስት ፍሬ በቅርንጫፍ ራስ ላይ እንደሚቀር፣

አራት ወይም አምስት ፍሬ ችፍግ ባለው ቅርንጫፍ ላይ እንደሚቀር፣

እንዲሁ ጥቂት ቃርሚያ ይተርፋል”

ይላል የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር

7በዚያ ቀን ሰዎች ወደ ፈጣሪያቸው ይመለከታሉ፤

ዐይኖቻቸውም ወደ እስራኤል ቅዱስ ያያሉ።

8በእጃቸውም ወደ ሠሯቸው መሠዊያዎች አይመለከቱም፤

በጣቶቻቸው ላበጇቸው የዕጣን መሠዊያዎች፣

ለአሼራም የአምልኮ ዐምዶች

ክብር አይሰጡም።

9በዚያን ቀን በእስራኤል ልጆች ምክንያት የተተዉት ጠንካራ ከተሞች ጥሻና ውድማ እንደ ሆኑ ሁሉ፣ እነዚህ ሁሉ ባድማ ይሆናሉ።

10አዳኝ አምላክህን ረስተሃል፤

መሸሸጊያ ዐለትህንም አላስታወስህም፤

ስለዚህ ምርጥ ተክል ብትተክልም፣

እንግዳ ዘርንም ብትዘራ፣

11በተከልህበት ቀን እንዲበቅል፣

በዘራህበትም ማግስት እንዲያብብ ብታደርግ እንኳ፣

መከሩ በደዌና በማይሽር ሕመም ቀን፣

እንዳልነበረ ይሆናል።

12አቤት፤ የብዙ ሕዝቦች የቍጣ ድምፅ

እንደ ባሕር ሞገድ ይጮኻል!

አቤት፤ የሰዎች ከፍተኛ ጩኸት

እንደ ኀይለኛ ውሃ ያስገመግማል!

13ሰዎቹ እንደ ኀይለኛ ውሃ ጩኸት ቢያስገመግሙም፣

እርሱ ሲገሥጻቸው፣

በኰረብታ ላይ በነፋስ እንደሚበንን ትቢያ፣

በዐውሎ ነፋስ ፊት እንደሚበተን ገለባ ይበተናሉ።

14እነሆ፤ ሲመሽ ድንገተኛ ሽብር ሆነ!

ከመንጋቱ በፊት ግን አንዳቸውም አልተገኙም።

የዘረፉን ዕድል ፈንታ፣

የበዘበዙን ዕጣ ይህ ሆነ።