ኢሳይያስ 13 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ኢሳይያስ 13:1-22

በባቢሎን ላይ የተነገረ ትንቢት

1የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ስለ ባቢሎን ያየው ንግር፤

2በተራቈተ ኰረብታ ዐናት ላይ ምልክት ስቀሉ፤

ድምፃችሁን ከፍ አድርጋችሁ ጩኹ፤

በመሳፍንቱም በር እንዲገቡ፣

በእጅ ምልክት ስጡ።

3በድል አድራጊነቴ ደስ የሚላቸውን ቅዱሳኔን አዝዛለሁ፤

ቍጣዬንም እንዲፈጽሙ፣

ተዋጊዎቼን ጠርቻለሁ።

4በተራሮች ላይ እንደ ብዙ ሕዝብ ድምፅ

የሚሰማውን ጩኸት አድምጡ፤

በመንግሥታትም መካከል፣

እንደ ተጨናነቀ ሕዝብ ድምፅ የሆነውን ውካታ ስሙ!

የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር

ሰራዊቱን ለጦርነት አሰልፏል።

5እግዚአብሔርና የቍጣው ጦር መሣሪያ፣

ምድሪቱን በሙሉ ለማጥፋት፣

ከሩቅ አገር፣

ከሰማያትም ዳርቻ መጥተዋል።

6የእግዚአብሔር ቀን ቀርቧልና አልቅሱ፤

ሁሉን ቻይ13፥6 ዕብራይስጡ ሻዳይ ይላል። ከሆነ አምላክ ዘንድ ጥፋት ይመጣልና።

7ስለዚህ እጆች ሁሉ ሽባ ይሆናሉ፤

የሰውም ሁሉ ልብ ይቀልጣል።

8ሽብር ይይዛቸዋል፤

ሥቃይና ጭንቀት ይደርስባቸዋል፤

ምጥ እንደ ያዛት ሴት ያምጣሉ፤

እርስ በርሳቸው በድንጋጤ ይተያያሉ፤

ፊታቸውም በፍርሀት ቀይ ይሆናል።

9እነሆ፤ የእግዚአብሔር ቀን ጨካኝ ነው፤

ምድርን ባድማ ሊያደርጋት፣

በውስጧም ያሉትን ኀጢአተኞች ሊያጠፋ፣

ከመዓትና ከብርቱ ቍጣ ጋር ይመጣል።

10የሰማይ ከዋክብትና ሰራዊታቸው፣

ብርሃን አይሰጡም፤

ፀሓይ ገና ከመውጣቷ ትጨልማለች፤

ጨረቃም ብርሃኗን አትሰጥም።

11ዓለምን ስለ ክፋቷ፣

ክፉዎችንም ስለ ኀጢአታቸው እቀጣለሁ፤

የትዕቢተኞችን እብሪት እሽራለሁ፤

የጨካኞችንም ጕራ አዋርዳለሁ።

12ሰውን ከነጠረ ወርቅ ይልቅ ውድ፣

ከኦፊርም ወርቅ ይበልጥ ብርቅ አደርጋለሁ።

13ስለዚህ በሰራዊት ጌታ በእግዚአብሔር መዓት፣

ቍጣው በሚነድድበት ቀን፣

ሰማያትን እነቀንቃለሁ፤

ምድርንም ከስፍራዋ አናውጣለሁ።

14እንደሚታደን ሚዳቋ፣

እረኛም እንደሌለው የበግ መንጋ፣

እያንዳንዱ ወደ ወገኑ ይመለሳል፣

እያንዳንዱም ወደ አገሩ ይሸሻል።

15የተማረከ ሁሉ ይወጋል፤

የተያዘም ሁሉ በሰይፍ ይወድቃል።

16ዐይናቸው እያየ ሕፃናታቸው ይጨፈጨፋሉ፤

ቤታቸው ይዘረፋል፤ ሚስቶቻቸው ይደፈራሉ።

17እነሆ፤ ለብር ደንታ የሌላቸውን፣

በወርቅም ደስ የማይሰኙትን፣

ሜዶናውያንን አስነሣባቸዋለሁ።

18ቀስታቸው ጐበዞችን ይፈጃል፤

ሕፃናትን አይምሩም፤

ዐይናቸውም ለልጆች አይራራም።

19የመንግሥታት ዕንቍ፣

የከለዳውያን13፥19 ወይም፣ ባቢሎናውያን ማለት ነው። ትምክሕት

የሆነችውን ባቢሎንን፣

እግዚአብሔር እንደ ሰዶምና እንደ ገሞራ ይገለብጣታል።

20በዘመናት ሁሉ የሚቀመጥባት አይኖርም፤

የሚቀመጥባትም የለም፤

ዐረብ በዚያ ድንኳኑን አይተክልም፤

እረኛም መንጋውን በዚያ አያሳርፍም።

21ነገር ግን የምድረ በዳ አራዊት በዚያ ይተኛሉ፤

ቀበሮዎች ቤቶቿን ይሞላሉ፤

ጕጕቶች በዚያ ይኖራሉ፤

በበረሓ ፍየል የሚመሰሉ አጋንንትም ይዛለሉበታል።

22ጅቦች በምሽጎቿ፣

ቀበሮዎችም በተዋቡ ቤተ መንግሥቶቿ ይጮኻሉ፤

ጊዜዋ ቀርቧል፤

ቀኗም አይራዘምም።