አስቴር 8 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

አስቴር 8:1-17

ንጉሡ በአይሁድ ስም የተናገረው ዐዋጅ

1በዚያኑ ዕለት ንጉሥ ጠረክሲስ የአይሁድን ጠላት የሐማን ቤት ንብረት ለንግሥት አስቴር ሰጣት፤ አስቴርም መርዶክዮስ እንዴት እንደሚዛመዳት ለንጉሡ ነግራው ስለ ነበር፣ መርዶክዮስ ወደ ንጉሡ ዘንድ ቀረበ። 2ንጉሡ ከሐማ መልሶ የወሰደውን ባለ ማኅተም ቀለበት አውልቆ ለመርዶክዮስ ሰጠው፤ አስቴርም መርዶክዮስን በሐማ ቤት ንብረት ላይ ሾመችው።

3አስቴር በንጉሡ እግር ላይ ወድቃ በማልቀስ ልመናዋን እንደ ገና አቀረበች። አጋጋዊው ሐማ በአይሁድ ላይ የሸረበው ክፉ ሤራ እንዲሽር ለመነችው። 4ከዚያም ንጉሡ የወርቅ ዘንጉን ለአስቴር ዘረጋላት፤ እርሷም ተነሥታ በፊቱ ቆመች።

5እንዲህም አለች፤ “ንጉሡን ደስ የሚያሰኘውና እኔም በፊቱ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ፣ ጕዳዩም በንጉሡ ዘንድ ተገቢ ሆኖ ከተገኘና በእኔም ደስ ከተሰኘ፣ የአጋጋዊው የሐመዳቱ ልጅ ሐማ በንጉሡ አውራጃዎች ሁሉ የሚገኙትን አይሁድ ለማጥፋት የሸረበውን ሤራና የጻፈውን ደብዳቤ የሚሽር ትእዛዝ ይጻፍ። 6በሕዝቤ ላይ መዓት ሲወርድ እያየሁ እንዴት ልታገሥ እችላለሁ? የቤተ ሰቤንስ መጥፋት እያየሁ እንዴት መቋቋም እችላለሁ?”

7ንጉሥ ጠረክሲስም ለንግሥት አስቴርና ለአይሁዳዊው ለመርዶክዮስ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እነሆ ሐማ አይሁድን ለማጥፋት ስላቀደ፣ ቤት ንብረቱን ለአስቴር ሰጥቻለሁ፤ እርሱንም በዕንጨት ላይ ሰቅለውታል። 8በንጉሥ ስም የተጻፈና በቀለበቱ የታተመ ደብዳቤ ሊሻር ስለማይችል፣ እናንተ ደግሞ አይሁድን በተመለከተ መልካም መስሎ የታያችሁን ሌላ ዐዋጅ በንጉሡ ስም ጽፋችሁ በንጉሡ የቀለበት ማኅተም ዐትሙት።”

9ኒሳን በተባለው በሦስተኛው ወር ሃያ ሦስተኛ ቀን የቤተ መንግሥቱ ጸሓፊዎች በአስቸኳይ ተጠርተው ነበር፤ እነርሱም የመርዶክዮስን ትእዛዝ ሁሉ ለአይሁድ፣ እንዲሁም ከህንድ ጀምሮ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ፣ በአንድ መቶ ሃያ ሰባት አውራጃዎች ለሚገኙ እንደራሴዎች፣ የአውራጃ ገዦችና መኳንንት ሁሉ ጻፉ። እነዚህም ትእዛዞች የተጻፉት በእያንዳንዱ አውራጃ ፊደልና በእያንዳንዱ ሕዝብ ቋንቋ፣ እንደዚሁም ለአይሁድ በገዛ ፊደላቸውና በገዛ ቋንቋቸው ነበር። 10መርዶክዮስ ትእዛዙን በንጉሥ ጠረክሲስ ስም ጽፎ በንጉሡ የቀለበት ማኅተም ዐተመው፤ ከዚያም በተለይ ለንጉሡ በተገሩ ፈጣን ፈረሶች በሚጋልቡ መልእክተኞች እጅ ላከው።

11የንጉሡም ዐዋጅ በየከተማው የሚኖሩ አይሁድ ሁሉ እንዲሰበሰቡና ራሳቸውን ከጥቃት እንዲከላከሉ እንዲሁም በራሳቸው፣ በሚስቶቻቸውና በልጆቻቸው ላይ አደጋ የሚያደርስባቸውን የየትኛውንም ዜጋ ወይም አውራጃ የታጠቀ ኀይል እንዲያጠፉ፣ እንዲገድሉ፣ እንዲደመስሱና የጠላቶቻቸውን ሀብት እንዲዘርፉ ፈቀደላቸው። 12አይሁድ በመላው የንጉሥ ጠረክሲስ አውራጃ ሁሉ ይህን እንዲፈጽሙ የተወሰነው አዳር በተባለው በዐሥራ ሁለተኛው ወር ዐሥራ ሦስተኛ ቀን ነበር። 13አይሁድ በዚያን ቀን ጠላቶቻቸውን ለመበቀል ዝግጁ እንዲሆኑ፣ የዋናው ዐዋጅ ቅጅ ሕግ ወደየአውራጃው እንዲላክና የየአገሩም ሕዝብ እንዲያውቀው ተደረገ።

14በቤተ መንግሥቱ ፈረሶች የተቀመጡ መልእክተኞችም፣ በንጉሡ አስቸኳይ ትእዛዝ ጋልበው ወጡ፤ ዐዋጁም በሱሳ ግንብ ተነገረ።

15መርዶክዮስ ሰማያዊና ነጭ የቤተ መንግሥት ልብስ ለብሶ፣ ትልቅ የወርቅ አክሊል ደፍቶ፣ ከቀጭን በፍታና ከሐምራዊ ግምጃ የተሠራ መጐናጸፊያ ተጐናጽፎ ከንጉሡ ፊት ወጣ፤ የሱሳ ከተማም ደስታ የተሞላበት በዓል አከበረች። 16ጊዜውም ለአይሁድ የደስታና የፈንጠዝያ፣ የተድላና የክብር ወቅት ሆነላቸው። 17የንጉሡ ዐዋጅ በደረሰበት በእያንዳንዱ አውራጃና በእያንዳንዱ ከተማ አይሁድ ደስ አላቸው፤ ሐሤት አደረጉ፤ የፈንጠዝያና የደስታም ቀን ሆነላቸው። አይሁድን ከመፍራታቸው የተነሣ፣ ከሌሎች አገር ዜጎች ብዙ ሕዝብ አይሁድ ሆኑ።