መሳፍንት 7 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

መሳፍንት 7:1-25

ጌዴዎን ምድያማውያንን ድል አደረገ

1ይሩበኣል የተባለው ጌዴዎን፣ ከእርሱም ጋር የነበሩት ሰዎች ሁሉ በጧት ተነሥተው በሐሮድ ምንጭ አጠገብ ሰፈሩ። የምድያማውያንም ሰፈር እስራኤላውያን ከሰፈሩበት በስተ ሰሜን በኩል፣ በሞሬ ኰረብታ አጠገብ በሸለቆው ውስጥ ነበር። 2እግዚአብሔር ጌዴዎንን እንዲህ አለው፤ “ምድያማውያንን በእጃቸው አሳልፌ እንዳልሰጥ አብረውህ ያሉት ሰዎች በጣም ብዙ ናቸው፤ እስራኤላውያን የገዛ ኀይላቸው እንዳዳናቸው በመቍጠር እንዳይታበዩብኝ፣ 3‘ማንም የፈራ ቢኖር የገለዓድን ተራራ ትቶ ወደ መጣበት ይመለስ’ ብለህ ለሕዝቡ ዐውጅ።” ስለዚህ ሃያ ሁለቱ ሺሕ ሲመለሱ ዐሥሩ ሺሕ ብቻ ቀሩ።

4እግዚአብሔር ጌዴዎንን እንዲህ አለው፤ “አሁንም ሰዎቹ ብዙ ናቸው፤ ወደ ወንዝ ይዘሃቸው ውረድ፤ በዚያም እለይልሃለሁ። ‘ይህ ከአንተ ጋር ይሂድ’ የምለው፣ ከአንተ ጋር ይሄዳል፤ ነገር ግን፣ ‘ይህ ከአንተ ጋር አይሂድ’ የምለው፣ ከአንተ ጋር አይሄድም።”

5ስለዚህ ጌዴዎን ሰዎቹን ወደ ወንዝ ይዟቸው ወረደ፤ እዚያም እግዚአብሔር፤ “ውሻ በምላሱ እየጨለፈ እንደሚጠጣ ሁሉ፣ በምላሳቸው የሚጠጡትን፣ በጕልበታቸው ተንበርክከው ከሚጠጡት ለይ” አለው። 6ሦስት መቶ ሰዎች ውሃውን በእጃቸው እያፈሱ ጠጡ፤ የቀሩት ሁሉ ግን ለመጠጣት በጕልበታቸው ተንበረከኩ።

7እግዚአብሔርም ጌዴዎንን፣ “ውሃውን በእጃቸው እያፈሱ በጠጡት ሦስት መቶ ሰዎች አድናችኋለሁ፤ ምድያማውያንንም በእጃችሁ አሳልፌ እሰጣችኋለሁ፤ የቀሩት በሙሉ ወደየመጡበት ይመለሱ” አለው። 8ጌዴዎንም የቀሩትን እስራኤላውያን በሙሉ ወደ የድንኳናቸው እንዲመለሱ አደረገ፤ ሦስት መቶውን ግን አስቀራቸው፤ እነርሱም የሚመለሱትን ሰዎች ስንቅና መለከት ወሰዱ።

በዚህ ጊዜ የምድያማውያኑ ሰፈር ከእነርሱ በታች በሸለቋማው ውስጥ ነበር። 9በዚያች ሌሊት እግዚአብሔር ጌዴዎንን እንዲህ አለው፤ “ተነሥ፤ በሰፈሩም ላይ ውረድ፤ በእጅህ አሳልፌ ሰጥቼሃለሁና። 10አደጋ ለመጣል የምትፈራ ከሆነ ግን፣ ፉራ ከተባለው አገልጋይህ ጋር ወደ ሰፈሩ ውረድ፤ 11የሚሉትንም አድምጥ፤ ከዚያ በኋላ በሰፈሩ ላይ አደጋ ለመጣል ድፍረት ታገኛለህ።” ስለዚህም ጌዴዎን አገልጋዩን ፉራን አስከትሎ እስከ ሰፈሩ ዳርቻ ወረደ። 12ብዛታቸው እንደ አንበጣ መንጋ የሆነ ምድያማውያን፣ አማሌቃውያንና ሌሎችም የምሥራቅ ሕዝቦች በሸለቆው ውስጥ ሰፍረው ነበር፤ የግመሎቻቸውም ብዛት በባሕር ዳርቻ እንዳለ አሸዋ ስፍር ቍጥር አልነበረውም።

13አንድ ሰው ያየውን ሕልም ለጓደኛው በሚነግርበት ጊዜ ጌዴዎን እዚያ ደረሰ። ያም ሰው፣ “በሕልሜ ክብ የሆነ አንድ የገብስ ቂጣ ከላይ ተንከባሎ በምድያማውያን ሰፈር ላይ ሲወርድ፣ ድንኳኑንም ሲመታው ከአመታቱም ኀይለኛነት የተነሣ ድንኳኑ ተገልብጦ ሲፈራርስ አየሁ” በማለት ይነግረው ነበር።

14ጓደኛውም መልሶ፣ “ይህ የእስራኤላዊው የኢዮአስ ልጅ የጌዴዎን ሰይፍ እንጂ ሌላ ነገር ሊሆን አይችልም፤ እነሆ፤ እግዚአብሔር ምድያማውያንንና ሰፈሩን በሙሉ በእጁ አሳልፎ ሰጥቶታልና” አለው።

15ጌዴዎንም ሕልሙንና ፍቺውን በሰማ ጊዜ ለእግዚአብሔር ሰገደ፤ ከዚያም ወደ እስራኤላውያን ሰፈር ወጥቶ፣ “እግዚአብሔር የምድያማውያንን ሰፈር በእጃችሁ አሳልፎ ሰጥቷልና ተነሡ” አላቸው። 16ሦስቱን መቶ ሰዎች በሦስት ቡድን ከፍሎ፣ እያንዳንዱን ሰው ቀንደ መለከትና በውስጡ ችቦ ያለበት ባዶ ማሰሮ በእጁ እንዲይዝ አደረገ።

17ጌዴዎንም እንዲህ አላቸው፤ “እኔን ተመልከቱ፤ የማደርገውንም አድርጉ፤ በሰፈሩ ዳርቻ ስደርስ እኔ የማደርገውን አይታችሁ ልክ እንደዚያው አድርጉ። 18እኔና አብረውኝ ያሉት ሁሉ ቀንደ መለከቶቻችንን በምንነፋበት ጊዜ እናንተም በሰፈሩ ዙሪያ ሁሉ ቀንደ መለከቶቻችሁን እየነፋችሁ፣ ‘ለእግዚአብሔርና ለጌዴዎን’ ብላችሁ ጩኹ።”

19ዘቦቹ ተቀያይረው የእኩለ ሌሊቱን ጥበቃ በጀመሩበት ጊዜ፣ ጌዴዎንና አብረውት የነበሩት መቶ ሰዎች በሰፈሩ ዳርቻ ደረሱ፤ እነርሱም ቀንደ መለከቶቻቸውን ነፉ፤ የያዟቸውንም ማሰሮች ሰበሩ። 20በሦስት ቡድን የተከፈሉት ሰዎች ቀንደ መለከቶቻቸውን ነፉ፤ ማሰሮቻቸውንም ሰበሩ፤ ችቦዎቻቸውን በግራ እጆቻቸው፣ የሚነፏቸውንም ቀንደ መለከቶች በቀኝ እጆቻቸው ይዘው፣ “የእግዚአብሔርና የጌዴዎን ሰይፍ” በማለት ጮኹ። 21እያንዳንዱ ሰው በሰፈሩ ዙሪያ የተመደበበትን ቦታ እንደ ያዘም ምድያማውያኑ እየጮኹ ሸሹ።

22የሦስት መቶው ቀንደ መለከት ድምፅ እንደ ተሰማም እግዚአብሔር በሰፈሩ ውስጥ ያለው ሰው አንዱ በሌላው ላይ ሰይፉን እንዲመዝበት አደረገ፤ ሰራዊቱ በጽሬራ አቅጣጫ ወደ ቤት ሺጣ፣ ከዚያም ዐልፈው በጠባት አጠገብ እስካለው እስከ አቤላሞሖላ ድንበር ድረስ ሸሽተው ሄዱ። 23በንፍታሌም፣ በአሴርና በመላው የምናሴ ምድር የሚገኙ እስራኤላውያን ተጠርተው ወጡ፤ ምድያማውያንንም አሳደዱ። 24ጌዴዎንም በኤፍሬም ኰረብታማ አገር ለሚኖሩት ሁሉ፣ “በምድያማውያን ላይ ውረዱ፤ እስከ ቤትባራ ድረስ ያለውንም የዮርዳኖስ ወንዝ ቀድማችሁ ያዙ” አላቸው።

ስለዚህ የኤፍሬም ሰዎች ሁሉ ተጠርተው ወጡ፤ እስከ ቤትባራ ድረስ ያለውንም የዮርዳኖስን ወንዝ ያዙ። 25እንዲሁም ሔሬብና ዜብ የተባሉትን ሁለቱን የምድያም መሪዎች ያዙ። ሔሬብን በሔሬብ ዐለት አጠገብ፣ ዜብን ደግሞ በዜብ የወይን መጭመቂያ ላይ ገደሏቸው፤ ምድያማውያንንም አሳደዱ፤ የሔሬብንና የዜብን ራስ ቈርጠው ጌዴዎን ወዳለበት ወደ ዮርዳኖስ ይዘው መጡ።