ሉቃስ 7 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ሉቃስ 7:1-50

የመቶ አለቃው እምነት

7፥1-10 ተጓ ምብ – ማቴ 8፥5-13

1ኢየሱስ ይህን ሁሉ በሕዝቡ ፊት ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ ወደ ቅፍርናሆም ገባ። 2በዚያም አንድ የመቶ አለቃ ነበረ፤ እጅግ የሚወድደው አገልጋዩም ታምሞበት ለሞት ተቃርቦ ነበር። 3እርሱም ስለ ኢየሱስ በሰማ ጊዜ አገልጋዩን እንዲፈውስለት ይለምኑት ዘንድ አንዳንድ የአይሁድ ሽማግሌዎችን ላከበት። 4መልእክተኞቹም ወደ ኢየሱስ በመጡ ጊዜ እንዲህ ብለው አጥብቀው ለመኑት፤ “ይህን ልታደርግለት ይገባዋል፤ 5ምክንያቱም ይህ ሰው ሕዝባችንን ይወድዳል፤ ምኵራባችንንም ያሠራልን እርሱ ነው።” 6ኢየሱስም ከእነርሱ ጋር ሄደ።

እርሱም ወደ ቤቱ በተቃረበ ጊዜ፣ የመቶ አለቃው ወዳጆቹን ልኮ እንዲህ አለው፤ “ጌታ ሆይ፤ ከቤቴ ጣራ በታች ልትገባ የሚገባኝ ሰው አይደለሁምና አትድከም፤ 7ከዚህም የተነሣ በአንተ ፊት ለመቅረብ እንኳ እንደሚገባኝ ራሴን አልቈጠርሁም፤ ብቻ አንድ ቃል ተናገር፤ አገልጋዬ ይፈወሳል። 8እኔ ራሴ የበላይ አለቃ አለኝ፤ ከበታቼም የማዝዛቸው ወታደሮች አሉኝ፤ አንዱን፣ ‘ሂድ’ ስለው ይሄዳል፤ ሌላውን፣ ‘ና’ ስለው ይመጣል፤ አገልጋዬንም፣ ‘ይህን አድርግ’ ስለው የታዘዘውን ያደርጋል።”

9ኢየሱስም ይህን ሲሰማ በእርሱ ተደነቀ፤ ዘወር ብሎም ይከተለው ለነበረው ሕዝብ፣ “እላችኋለሁ፤ እንዲህ ያለ ትልቅ እምነት በእስራኤል እንኳ አላገኘሁም” አላቸው። 10የተላኩት ሰዎችም ወደ ቤት በተመለሱ ጊዜ፣ አገልጋዩን ድኖ አገኙት።

ኢየሱስ የመበለቲቱን ልጅ ከሞት አስነሣው

7፥11-16 ተጓ ምብ – 1ነገ 17፥17-242ነገ 4፥32-37ማር 5፥21-2435-43ዮሐ 11፥1-44

11ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ብዙ ሳይቈይ፣ ናይን ወደምትባል ከተማ ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱና ብዙ ሕዝብም አብረውት ሄዱ። 12ወደ ከተማዋ መግቢያ በር ሲደርስም፣ እነሆ፤ ሰዎች የአንድ ሰው አስከሬን ተሸክመው ከከተማዋ ወጡ፤ ሟቹም ለእናቱ አንድ ልጅ ብቻ ነበር፤ እናቱም መበለት ነበረች፤ ብዙ የከተማውም ሕዝብ ከእርሷ ጋር ነበረ። 13ጌታም ባያት ጊዜ ራራላትና፣ “አይዞሽ፤ አታልቅሺ” አላት።

14ቀረብ ብሎም ቃሬዛውን ነካ፤ የተሸከሙትም ሰዎች ቀጥ ብለው ቆሙ፤ ኢየሱስም፣ “አንተ ጐበዝ፤ ተነሥ እልሃለሁ” አለው። 15የሞተውም ሰው ቀና ብሎ ተቀመጠ፤ መናገርም ጀመረ። ኢየሱስም ወስዶ ለእናቱ ሰጣት።

16ሁሉም በፍርሀት ተውጠው እግዚአብሔርን እያመሰገኑ፣ “ታላቅ ነቢይ በመካከላችን ተነሥቷል፤ እግዚአብሔርም ሕዝቡን ጐብኝቷል” አሉ። 17ይህም የኢየሱስ ዝና በመላው ይሁዳና7፥17 ወይም በአይሁድ ምድር በአካባቢው ባለው አገር ሁሉ ወጣ።

ኢየሱስና መጥምቁ ዮሐንስ

7፥18-35 ተጓ ምብ – ማቴ 11፥2-19

18የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርትም ይህን ሁሉ ለዮሐንስ ነገሩት። እርሱም ከመካከላቸው ሁለቱን ጠርቶ፣ 19“ይመጣል የተባለልህ አንተ ነህ ወይስ ሌላ እንጠብቅ? በሉት” ብሎ ወደ ጌታ ላካቸው።

20ሰዎቹም ወደ ኢየሱስ መጥተው፣ “መጥምቁ ዮሐንስ፣ ‘ይመጣል የተባለልህ አንተ ነህ? ወይስ ሌላ እንጠብቅ?’ ብሎ ወደ አንተ ልኮናል” አሉት።

21በዚያኑ ጊዜ ኢየሱስ ብዙ ሰዎችን ከበሽታ፣ ከደዌና ከርኩሳን መናፍስት ፈወሳቸው፤ የብዙ ዐይነ ስውራንንም ዐይን አበራ። 22ከዮሐንስ ተልከው የመጡትንም እንዲህ አላቸው፤ “ሄዳችሁ ያያችሁትንና የሰማችሁትን ለዮሐንስ ንገሩት፤ ዐይነ ስውራን ያያሉ፤ ዐንካሶች በትክክል ይራመዳሉ፤ ለምጻሞች7፥22 የግሪኩ ቃል የግድ ከለምጽ ጋር ብቻ የተያያዘ ሳይሆን፣ የተለያዩ የቈዳ በሽታዎችን ለመግለጽ ጥቅም ላይ ይውላል። ነጽተዋል፤ ደንቈሮዎች ይሰማሉ፤ ሙታን ተነሥተዋል፤ ለድኾችም ወንጌል ይሰበካል፤ 23በእኔ የማይሰናከል ሰው ሁሉ የተባረከ ነው።”

24የዮሐንስ መልእክተኞች ከሄዱ በኋላ፣ ኢየሱስ ለሕዝቡ ስለ ዮሐንስ ይናገር ጀመር፤ እንዲህም አለ፤ “ወደ በረሓ የወጣችሁት ምን ልታዩ ነው? ነፋስ የሚያወዛውዘውን ሸንበቆ? 25እኮ! ምን ልታዩ ወጣችሁ? ያማረ ልብስ የለበሰውን ሰው ነውን? ባማረ ልብስ የሚሽሞነሞኑና በድሎት የሚኖሩ በቤተ መንግሥት አሉላችሁ። 26እኮ! ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን ለማየት ይሆን? አዎን፣ እላችኋለሁ፤ ለማየት የወጣችሁት ከነቢይም የሚበልጠውን ነው። 27እንዲህ ተብሎ የተጻፈለትም እርሱ ነው፤

“ ‘መንገድህን በፊትህ የሚያስተካክል

መልእክተኛዬን ከአንተ አስቀድሜ እልካለሁ።’

28እላችኋለሁ፤ ከሴት ከተወለዱት መካከል ከዮሐንስ የሚበልጥ የለም፤ በእግዚአብሔር መንግሥት ግን ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል።”

29ቀረጥ ሰብሳቢዎች እንኳ ሳይቀሩ፣ ይህን የሰሙ ሁሉ፣ የዮሐንስን ጥምቀት በመጠመቅ ለእግዚአብሔር ተገቢውን ክብር ሰጡ፤ 30ፈሪሳውያንና ሕግ ዐዋቂዎች ግን በዮሐንስ እጅ ባለ መጠመቃቸው፣ እግዚአብሔር ለእነርሱ ያለውን ዐላማ አቃለሉ።

31ኢየሱስ በመቀጠል እንዲህ አለ፤ “እንግዲህ የዚህን ትውልድ ሰዎች በምን ልመስላቸው? ምንስ ይመስላሉ? 32በገበያ ቦታ ተቀምጠው እርስ በርሳቸው እየተጠራሩ እንዲህ የሚባባሉ ልጆችን ይመስላሉ፤

“ ‘ዋሽንት ነፋንላችሁ፤

አልጨፈራችሁም፤

ሙሾ አወረድንላችሁ፤

አላለቀሳችሁም።’

33ምክንያቱም መጥምቁ ዮሐንስ እህል ሳይበላና የወይን ጠጅ ሳይጠጣ ቢመጣ፣ ጋኔን አለበት አላችሁት፤ 34የሰው ልጅ ደግሞ እየበላና እየጠጣ ቢመጣ፣ ‘በላተኛና ጠጪ፣ የቀረጥ ሰብሳቢዎችና የኀጢአተኞች ወዳጅ’ አላችሁት። 35እንግዲህ የጥበብ ትክክለኛነት በልጆቿ ሁሉ ዘንድ ተረጋገጠ።”

አንዲት ሴት ኢየሱስን ሽቶ ቀባች

7፥37-39 ተጓ ምብ – ማቴ 26፥6-13ማር 14፥3-9ዮሐ 12፥1-8

7፥1442 ተጓ ምብ – ማቴ 18፥23-34

36ከዚህ በኋላ ከፈሪሳውያን አንዱ ምግብ አብሮት እንዲበላ ኢየሱስን ጋበዘው፤ እርሱም ወደ ፈሪሳዊው ቤት ሄዶ በማእድ ተቀመጠ። 37በዚያ ከተማ የምትኖር አንዲት ኀጢአተኛ ሴት፣ ኢየሱስ በፈሪሳዊው ቤት በማእድ መቀመጡን በሰማች ጊዜ አንድ የአልባስጥሮስ ብልቃጥ ሽቶ ይዛ መጣች። 38ከበስተ ኋላው እግሩ አጠገብ ቆማ እያለቀሰች እግሩን በእንባዋ ታርስ፣ በራሷም ጠጕር ታብሰው ጀመር፤ እግሩንም እየሳመች ሽቱውን ቀባችው።

39የጋበዘውም ፈሪሳዊ ይህን ባየ ጊዜ፣ “ይህ ሰው ነቢይ ቢሆን ኖሮ፣ የነካችው ሴት ማን እንደ ሆነች፣ ደግሞም ምን ዐይነት ሰው እንደ ሆነች ባወቀ ነበር፤ ኀጢአተኛ ናትና” ብሎ በልቡ ዐሰበ።

40ኢየሱስም፣ “ስምዖን ሆይ፤ የምነግርህ ነገር አለኝ” አለው።

እርሱም፣ “መምህር ሆይ፤ ንገረኝ” አለው።

41ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “ከአንድ አበዳሪ ገንዘብ የተበደሩ ሁለት ሰዎች ነበሩ፤ አንደኛው አምስት መቶ ዲናር፣ ሁለተኛው ደግሞ አምሳ ዲናር ነበረበት። 42የሚከፍሉትም ቢያጡ ዕዳቸውን ለሁለቱም ተወላቸው። እንግዲህ ከሁለቱ አበዳሪውን አብልጦ የሚወድደው የትኛው ነው?”

43ስምዖንም፣ “ብዙው ዕዳ የተተወለት ይመስለኛል” ሲል መለሰ።

ኢየሱስም፣ “ትክክል ፈርደሃል” አለው።

44ወደ ሴቲቱም ዘወር ብሎ ስምዖንን እንዲህ አለው፤ “ይህችን ሴት ታያታለህን? እኔ ወደ ቤትህ ገባሁ፤ አንተ ለእግሬ ውሃ እንኳ አላቀረብህልኝም፤ እርሷ ግን እግሬን በእንባዋ እያራሰች በጠጕሯ አበሰች። 45አንተ ከቶ አልሳምኸኝም፤ እርሷ ግን ከገባሁ ጀምራ እግሬን ከመሳም አላቋረጠችም። 46አንተ ራሴን ዘይት አልቀባህም፤ እርሷ ግን እግሬን ሽቶ ቀባች። 47ስለዚህ እልሃለሁ፤ እጅግ ወድዳለችና ብዙው ኀጢአቷ ተሰርዮላታል፤ በትንሹ የተሰረየለት ግን የሚወድደው በትንሹ ነው።”

48ኢየሱስም ሴቲቱን፣ “ኀጢአትሽ ተሰርዮልሻል” አላት።

49አብረውት በማእድ ተቀምጠው የነበሩ እንግዶችም፣ “ይህ ኀጢአትን እንኳ የሚያስተሰረይ እርሱ ማን ነው?” ብለው በልባቸው አሰቡ።

50ኢየሱስም ሴቲቱን፣ “እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ” አላት።