2 ዜና መዋዕል 12 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

2 ዜና መዋዕል 12:1-16

ሺሻቅ በኢየሩሳሌም ላይ ዘመተ

12፥9-16 ተጓ ምብ – 1ነገ 14፥2125-31

1ሮብዓም መንግሥቱን ከመሠረተና ካጸና በኋላ፣ እርሱና እስራኤል12፥1 በዜና መዋዕል ካልዕ መጽሐፍ ተደጋግሞ እንደ ተጠቀሰው ይህ ይሁዳ ነው። ሁሉ የእግዚአብሔርን ሕግ ተዉ። 2እግዚአብሔርን ከመበደላቸው የተነሣም፣ ሮብዓም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት የግብፅ ንጉሥ ሺሻቅ በኢየሩሳሌም ላይ ዘመተ። 3ከግብፅ አብረውት የመጡትን ዐሥራ ሁለት ሺሕ ሠረገላዎች፣ ስድሳ ሺሕ ፈረሰኞችና ስፍር ቍጥር የሌላቸውን የሊቢያ፣ የሱኪምና የኢትዮጵያ ወታደሮችን ይዞ፣ 4የተመሸጉትን የይሁዳ ከተሞች በቍጥጥሩ ሥር በማድረግ እስከ ኢየሩሳሌም ዘለቀ።

5ከዚህ በኋላ ነቢዩ ሸማያ ወደ ሮብዓምና ሺሻቅን ፈርተው በኢየሩሳሌም ወደ ተሰበሰቡት ወደ እስራኤል መሪዎች መጥቶ፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እናንተ ትታችሁኛል፤ ስለዚህ እኔም በሺሻቅ እጅ ትቼአችኋለሁ’ ” አላቸው።

6የእስራኤል መሪዎችና ንጉሡ ራሳቸውን በማዋረድ፣ “እግዚአብሔር ጻድቅ ነው” አሉ።

7እግዚአብሔርም ራሳቸውን እንዳዋረዱ ባየ ጊዜ፣ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ ሸማያ መጣ፤ “ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ስላዋረዱ እታደጋቸዋለሁ እንጂ አላጠፋቸውም፤ ቍጣዬም በሺሻቅ እጅ በኢየሩሳሌም ላይ አይፈስስም። 8ይሁን እንጂ እኔን በማገልገልና የሌሎችን አገሮች ነገሥታት በማገልገል መካከል ያለውን ልዩነት ያውቁ ዘንድ፣ ለእርሱ ይገዛሉ።”

9የግብፅ ንጉሥ ሺሻቅ ኢየሩሳሌምን በወረረ ጊዜ፣ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ንብረትና የቤተ መንግሥቱን ንብረት ዘርፎ ወሰደ፤ ሰሎሞን ያሠራው የወርቅ ጋሻ ሳይቀር፣ እንዳለ ሁሉንም አጋዘው። 10ንጉሥ ሮብዓምም በተወሰዱት ፈንታ የናስ ጋሻዎች ሠርቶ፤ የቤተ መንግሥቱን ቅጥር በሮች ለሚጠብቁ የዘብ አለቆች በኀላፊነት ሰጠ። 11ንጉሡ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በሚሄድበት ጊዜ ሁሉ፣ ዘበኞቹ ጋሻዎቹን አንግበው ያጅቡት ነበር፤ ከዚያም በኋላ ጋሻዎቹን ወደ ዘበኞች ክፍል ይመልሱ ነበር።

12ሮብዓም ራሱን ዝቅ አድርጎ ስላዋረደ፣ የእግዚአብሔር ቍጣ ከእርሱ ተመለሰ፤ ፈጽሞም አላጠፋውም። በይሁዳም ደግሞ በጥቂቱም ቢሆን መልካም ነገር ተገኝቶ ነበር።

13ንጉሥ ሮብዓም በሚገባ ተደላድሎ በኢየሩሳሌም በንጉሥነቱ ቀጠለ፣ ሲነግሥ ዕድሜው አርባ አንድ ዓመት ነበር፤ እግዚአብሔር ስሙን በዚያ ለማኖር ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ በመረጣት በኢየሩሳሌም ከተማ ተቀምጦም፣ ዐሥራ ሰባት ዓመት ገዛ፤ እናቱም ናዕማ የምትባል አሞናዊት ነበረች። 14እግዚአብሔርን ይሻ ዘንድ ልቡን ስላላዘጋጀ ክፉ ነገር አደረገ።

15ሮብዓም በዘመነ መንግሥቱ ያከናወናቸው ተግባሮች ሁሉ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ድረስ ነቢዩ ሸማያ በጻፈው የታሪክ መዝገብና ባለ ራእዩ አዶ በዘገበው የትውልድ ሐረግ ታሪክ የሚገኝ አይደለምን? በሮብዓምና በኢዮርብዓም መካከል የማያቋርጥ ጦርነት ነበር። 16ሮብዓም እንደ አባቶቹ ሁሉ አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ ተቀበረ፤ ልጁ አብያም በእርሱ ፈንታ ነገሠ።