New Amharic Standard Version

2 ዜና መዋዕል 34:1-33

ኢዮስያስ ያደረገው ተሐድሶ

34፥1-2 ተጓ ምብ – 2ነገ 22፥1-2

34፥3-7 ተጓ ምብ – 2ነገ 23፥4-20

34፥8-13 ተጓ ምብ – 2ነገ 22፥3-7

1ኢዮስያስ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ስምንት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ሠላሳ አንድ ዓመት ገዛ። 2እርሱም በእግዚአብሔር ፊት መልካም የሆነውን ነገር አደረገ፤ ወደ ቀኝም ወደ ግራም ሳይል፣ በአባቱ በዳዊት መንገድ ሄደ።

3በዘመነ መንግሥቱ በስምንተኛው ዓመት ገና ወጣት ሳለ፣ የአባቱን የዳዊትን አምላክ መፈለግ ጀመረ፤ በዐሥራ ሁለተኛውም ዓመት ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን ከኰረብታ መስገጃ ስፍራዎች፣ ከአሼራ፣ ምስል ዐምዶች፣ ከተቀረጹ ጣዖታትና ቀልጠው ከተሠሩ ምስሎች አነጻ። 4በእርሱም ትእዛዝ የበኣሊም መሠዊያዎችን አፈራረሱ፤ እርሱም ከበላያቸው የነበሩትን የዕጣን መሠዊያዎችን አደቀቀ፤ የአሼራን ምስል ዓምዶችን፣ ጣዖታቱንና ምስሎቹን ሰባብሮ ከፈጫቸው በኋላ ይሠዉላቸው በነበሩት ሰዎች መቃብር ላይ በተነ። 5የካህናቱን ዐጥንት በመሠዊያዎቻቸው ላይ አቃጠለ፤ በዚህ ዐይነትም ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን አነጻ። 6እስከ ንፍታሌም ባሉ በምናሴ፣ በኤፍሬምና በስምዖን ከተሞች እንዲሁም በዙሪያቸው ባሉ የፈራረሱ አካባቢዎች፣ 7መሠዊያዎችንና የአሼራ ምስል ዐምዶችን አፈራረሰ፤ ጣዖታቱን እንደ ዱቄት አደቀቀ፤ በመላው እስራኤል የሚገኙትንም የዕጣን መሠዊያዎች አነካከተ፤ ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ።

8ኢዮስያስ በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት፣ ምድሪቱንና ቤተ መቅደሱን ካነጻ በኋላ፣ የኤዜልያስን ልጅ ሳፋንን፣ የከተማዪቱን ገዥ መዕሤያንና የጸሓፊውን የኢዮአካዝን ልጅ ኢዮአክን የአምላኩን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ይጠግኑ ዘንድ ላካቸው።

9እነርሱም ወደ ሊቀ ካህኑ ወደ ኬልቅያስ ሄደው፣ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የመጣውን ገንዘብ ሰጡት፤ ገንዘቡም በር ጠባቂዎች የነበሩት ሌዋውያን፣ ከምናሴ፣ ከኤፍሬምና ከመላው የእስራኤል ቅሬታዎች እንደዚሁም ከመላው ይሁዳና ከብንያም፣ ከኢየሩሳሌምም ነዋሪዎች የሰበሰቡት ነበር። 10እነርሱም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ሥራ እየተቈጣጠሩ እንዲያሠሩ ለተሾሙት ሰዎች ዐደራ ሰጡ፤ እነዚህም ሰዎች ገንዘቡን ቤተ መቅደሱን ለጠገኑትና ላደሱት ሰዎች ከፈሉ። 11እንዲሁም የይሁዳ ነገሥታት እንዲፈርሱ ላደረጓቸው ሕንጻዎች ጥርብ ድንጋዮችን፣ ሠረገላዎችንና ማገጣጠሚያ ዕንጨቶችን እንዲገዙ ለዐናጢዎችና ለግንበኞች ገንዘብ ሰጡ።

12ሰዎቹም ሥራውን በታማኝነት አከናወኑ። የበላይ ሆነው አመራር የሚሰጧቸውም ከሜራሪ ጐሣ የሆኑት ሌዋውያን፣ ኢኤትና አብድዩ፣ ከቀዓት ጐሣ ዘካርያስና ሜሱላም ነበሩ። በዜማ ዕቃ የላቀ ችሎታ የነበራቸው ሌዋውያን ሁሉ፣ 13የጒልበት ሠራተኞች ኀላፊ በመሆን፣ በየሥራው ላይ የተመደቡትን ሠራተኞች ይቈጣጠሩ ነበር። ጥቂቶቹ ሌዋውያን ደግሞ ኀላፊዎች፣ ጸሓፊዎችና በር ጠባቂዎች ነበሩ።

የሙሴ ሕግ መጽሐፍ መገኘት

34፥14-28 ተጓ ምብ – 2ነገ 22፥8-20

34፥29-32 ተጓ ምብ – 2ነገ 23፥1-3

14ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የገባውን ገንዘብ በሚያወጡበት ጊዜ፣ ካህኑ ኬልቅያስ በሙሴ አማካይነት የተሰጠውን የእግዚአብሔርን ሕግ መጽሐፍ አገኘ። 15ኬልቅያስም ጸሓፊውን ሳፋንን፣ “የሕጉን መጽሐፍ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ አገኘሁት” አለው፤ ከዚያም መጽሐፉን ለሳፋን ሰጠው።

16ሳፋንም መጽሐፉን ወደ ንጉሡ ወስዶ እንዲህ አለው፤ “ሹማምትህ የታዘዙትን ሁሉ በመፈጸም ላይ ናቸው፤ 17በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የነበረውንም ገንዘብ አውጥተው ለተቈጣጣሪዎቹና ለሠራተኞቹ አስረክበዋል።”

18ከዚያም ጸሓፊው ሳፋን ንጉሡን፣ “ካህኑ ኬልቅያስ መጽሐፍ ሰጥቶኛል” አለው። ሳፋንም መጽሐፉን ለንጉሡ አነበበለት።

19ንጉሡም የሕጉን ቃል በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀደደ። 20እርሱም ለኬልቅያስ፣ ለሳፋን ልጅ ለአኪቃም፣ ለሚክያስ ልጅ ለዓብዶን፣ ለጸሓፊው ለሳፋንና ለንጉሡ የቅርብ አገልጋይ ለዓሳያ ይህን ትእዛዝ ሰጠ፤ 21“ሄዳችሁ ስለ እኔ እንደዚሁም በእስራኤልና በይሁዳ ስላሉት ቅሬታዎች በተገኘው መጽሓፍ ውስጥ ስለ ተጻፈው ነገር እግዚአብሔርን ጠይቁ። አባቶቻችን የእግዚአብሔርን ቃል ስላልጠበቁ በላያችን ላይ ታላቅ የእግዚአብሔር ቊጣ ፈስሶአል፤ በዚህ መጽሐፍ በተጻፈው መሠረት አልተመላለሱምና።”

22ኬልቅያስና ንጉሡ ከእርሱ ጋር የላካቸው34፥22 አንድ የዕብራይስጥ ቅጅ እንዲሁም ቩልጌትና የሱርስት ትርጒሞች በዚህ ሲስማሙ አብዛኞቹ የዕብራይስጥ ቅጆች ግን ከእርሱ ጋር የላካቸው የሚለውን አይጨምሩም። ሰዎች የአልባሳት ጠባቂ የነበረው የሐስራ ልጅ፣ የቲቁዋ ልጅ የሴሌም ሚስት ወደሆነችው ወደ ነቢይቱ ወደ ሕልዳና ሄደው ነገሯት። እርሷም በኢየሩሳሌም ውስጥ በሁለተኛው ክፍለ ከተማ ትኖር ነበር።

23ነቢይቱም እንዲህ አለቻቸው፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ወደ እኔ ለላካችሁ ሰው እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፤ 24እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በይሁዳ ንጉሥ ፊት በተነበበው መጽሐፍ በተጻፈው ርግማን ሁሉ መሠረት፣ በዚህ ስፍራና በሕዝቡ ላይ ጥፋትን አመጣለሁ። 25እኔን ትተውኝ ለሌሎች አማልክት ዕጣን ስላጠኑና እጃቸው በሠራው ነገር ሁሉ34፥25 ወይም ባደረጉት ነገር ሁሉ ለቊጣ ስላነሣሡኝ፣ ቊጣዬ በዚህ ስፍራ ይነድ ዳል፤ አይጠፋምም።’ 26እግዚአብሔርን ለመጠየቅ የላካችሁን የይሁዳን ንጉሥ እንዲህ በሉት፤ ‘ስለ ሰማኸው ቃል የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ 27በዚህ ስፍራና በሕዝቡ ላይ የተናገረውን በሰማህ ጊዜ፣ ልብህ ስለ ተነካና በእግዚአብሔርም ፊት ራስህን ስለአዋረድህ፣ እንዲሁም በእኔ ፊት ራስህን ዝቅ ስላደረግህ፣ ልብስህንም በመቅደድ በፊቴ ስለአለቀስህ፣ ሰምቼሃለሁ ይላል እግዚአብሔር28እነሆ፤ ወደ አባቶችህ እሰበስብሃለሁ፤ በሰላምም ትቀበራለህ፤ በዚህ ቦታና በነዋሪዎቹ ላይ የማመጣውን መከራ ሁሉ በዓይንህ አታይም።’ ” መልሷንም ይዘው ወደ ንጉሡ ሄዱ።

29ከዚያም ንጉሡ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ሽማግሌዎች ሁሉ በአንድ ላይ ሰበሰበ። 30እርሱም ከትንሽ እስከ ትልቅ ካሉት ከይሁዳ ሰዎች፣ ከኢየሩሳሌም ሕዝብ፣ ከካህናትና ከሌዋውያን ጋር ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ወጣ። በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የተገኘውንም የኪዳኑን መጽሐፍ ቃል ሁሉ ለሕዝቡ አነበበላቸው 31ንጉሡም በዐምዱ አጠገብ ቆሞ፣ እግዚአብሔርን ይከተል ዘንድ በፍጹም ልቡና በፍጹም ነፍሱ ትእዛዛቱን፣ ሕግጋቱንና ሥርዐቱን ለመጠበቅ፣ በዚህ መጽሐፍ ለተጻፈውም የኪዳን ቃል ለመታዘዝ በእግዚአብሔር ፊት ኪዳኑን አደሰ።

32ከዚህ በኋላ በኢየሩሳሌምና በብንያም የሚኖረው ሁሉ በዚህ ነገር ቃል እንዲገባ አደረገ፤ የኢየሩሳሌምም ሕዝብ የአባቶቹ አምላክ ባዘዘው የአምላክ ቃል ኪዳን መሠረት ፈጸሙ።

33ኢዮስያስም አስጸያፊ ጣዖታትን ሁሉ ከመላው የእስራኤል ግዛት አስወገደ፤ በእስራኤል የነበሩትም ሁሉ አምላካቸውን እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ አደረገ፤ እርሱ በሕይወት እያለም የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ከመከተል ወደ ኋላ አላሉም።