New Amharic Standard Version

2 ዜና መዋዕል 31:1-21

1ይህ ሁሉ ከተፈጸመ በኋላ፣ በዚያ የነበሩት እስራኤላውያን ወደ ይሁዳ ከተሞች ወጥተው፣ የማምለኪያ ድንጋዮችን ሰባበሩ፤ የአሼራ ምስል ዐምዶች ቈረጡ፤ እንዲሁም በመላው ይሁዳና በብንያም፣ በኤፍሬምና በምናሴ የነበሩትን የኰረብታ መስገጃዎችና መሠዊያዎች አጠፉ፤ እስራኤላውያን እነዚህን ሁሉ ካጠፉ በኋላ ወደየከተሞቻቸውና ወደየርስታቸው ተመለሱ።

ለካህናት የተደረገ ስጦታ

31፥20-21 ተጓ ምብ – 1ነገ 18፥5-7

2ሕዝቅያስ ካህናቱና ሌዋውያኑ የሚቃጠል መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕት31፥2 በትውፊት፣ የሰላም መሥዋዕት ይባላል። እንዲያቀርቡ፣ እንዲያገለግሉና እንዲያመሰግኑ እንዲሁም በእግዚአብሔር ማደሪያ ደጆች ውዳሴውን እንዲዘምሩ፣ ካህናትንም ሆኑ ሌዋውያንን እያንዳንዳቸውን እንደየተግባራቸው በየክፍሉ መደባቸው። 3በእግዚአብሔር ሕግ እንደ ተጻፈው ንጉሡ ጠዋትና ማታ እንደዚሁም በየሰንበቱ፣ በየወሩ መባቻውና በተወሰኑ በዓላት፣ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ከራሱ ንብረት ሰጠ። 4ካህናቱና ሌዋውያኑም ሙሉ ጊዜአቸውን ለእግዚአብሔር ሕግ አገልግሎት ማዋል ይችሉ ዘንድ፣ በኢየሩሳሌም የሚኖረው ሕዝብ ተገቢውን ድርሻ እንዲሰጣቸው አዘዘ። 5ትእዛዙ እንደ ወጣ እስራኤላውያን ወዲያውኑ የእህሉንና የአዲሱን ወይን ጠጅ፣ የዘይቱንና የማሩን እንዲሁም የዕርሻውን ፍሬ ሁሉ በኵራት በልግሥና ሰጡ፤ ካላቸው ከማንኛውም ነገር ሁሉ ላይ እጅግ ብዙ የሆነ ዐሥራት አውጥተው አመጡ። 6በይሁዳ ከተሞች ይኖሩ የነበሩት የእስራኤልና የይሁዳ ሰዎችም ከከብቶቻቸው፣ ከበግና ከፍየል መንጎቻቸውና ለአምላካቸው ለእግዚአብሔር ከለዩአቸው የተቀደሱ ነገሮች ዐሥራት አውጥተው አመጡ፤ ከመሩትም። 7ይህንም በሦስተኛው ወር ጀምረው፣ በሰባተኛው ወር አጠናቀቁ። 8ሕዝቅያስና ሹማምቱም መጥተው ክምሩን ባዩ ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገኑ፤ ሕዝቡን እስራኤልንም ባረኩ።

9ሕዝቅያስም ካህናቱንና ሌዋውያኑን ስለ ክምሩ ጠየቃቸው፤ 10ከሳዶቅ ቤተ ሰብ የሆነው ሊቀ ካህናቱ ዓዛርያስም፣ “ሕዝቡ ስጦታውን ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ማምጣት ከጀመረበት ጊዜ አንሥቶ በቂ ምግብ አግኝተናል፤ ብዙም ተርፎናል፤ እግዚአብሔር ሕዝቡን ስለባረከም ይህን ያህል ብዛት ያለው ሊተርፍ ችሎአል” አለ።

11ሕዝቅያስም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ ጎተራ እንዲያዘጋጁ አዘዛቸው፤ እነርሱም አዘጋጁ። 12ከዚያም ስጦታውን፣ ዐሥራቱንና የተቀደሱ ስጦታዎቹን በታማኝነት አምጥተው አስገቡ። ሌዋዊው ኮናንያ የእነዚሁ ዕቃዎች ኀላፊ ሲሆን ወንድሙ ስሜኢ ደግሞ በማዕረግ ሁለተኛ ነበር። 13ይሒዒል፣ ዓዛዝያ፣ ናሖት፣ አሣሄል፣ ይሬሞት፣ ዮዛባት፣ ኤሊኤል፣ ሰማኪያ፣ መሐትና በናያስ በንጉሡ ሕዝቅያስና በእግዚአብሔር ቤት ኀላፊ በዓዛርያስ ተሹመው በኮናንያና በወንድሙ በሰሜኢ ሥር ሆነው ተቈጣጣሪዎች ነበሩ።

14የምሥራቁ በር ጠባቂ የሆነው የሌዋዊው የይምና ልጅ፣ ቆሬ ደግሞ በበጎ ፈቃድ፣ ለእግዚአብሔር በቀረበው ስጦታ ላይ የእግዚአብሔርን መባና የተቀደሱትንም ነገሮች ለማከፋፈል፣ ኀላፊ ነበረ። 15ዔድን፣ ሚንያሚን፣ ኢያሱ፣ ሸማያ፣ አማርያና ሴኬንያ በካህናቱ ከተሞች ተገኝተው፣ ለካህናት ወገኖቻቸው ለታላላቆቹም ሆነ ለታናናሾቹ፣ እንደየምድባቸው፣ በማከፋፈሉ ረገድ በታማኝነት ረዱት።

16በተጨማሪም፣ ስማቸው በትውልድ መዝገቡ ውስጥ የነበረና የየዕለቱ ልዩ ልዩ ተግባራቸውን እንደየኀላፊነታቸው መጠንና እንደየምድብ ሥራቸው ለማከናወን ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መግባት ለሚችሉት፣ ዕድሜአቸው ሦስት ዓመትና ከዚያም በላይ ለሆናቸው ወንዶች ልጆች እንደዚሁ አከፋፈሉ። 17በትውልድ መዝገብ በየቤተ ሰባቸው ተቈጥረው ለገቡት ካህናት፣ ዕድሜአቸው ሃያ ዓመትና ከዚያም በላይ ለሆናቸው ሌዋውያን እንደየኀላፊነታቸው መጠንና እንደየምድብ ሥራቸው አካፈሏቸው። 18በዚህ የትውልድ መዝገብ ላይ የተዘረዘሩትን መላውን የማኅበረሰቡን ሕፃናት፣ ሚስቶችን፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ጨመሯቸው፤ ራሳቸውን በመቀደስ ታማኞች ነበሩና።

19በከተሞቻቸው ዙሪያ ባሉት የዕርሻ ቦታዎች፣ ወይም በሌሎች ከተሞች ሁሉ ለሚኖሩት ለካህናቱ ለአሮን ዘሮች፣ በመካከላቸው ላሉት ወንዶችና በሌዋውያን የትውልድ መዝገብ ለተመዘገቡት ሁሉ እንዲያከፋፍሉ በየስማቸው የተጻፉ ሰዎች ነበሩ።

20ሕዝቅያስ በአምላኩ በእግዚአብሔር ፊት መልካም፣ ቅንና ታማኝ ሆኖ በመገኘት በመላው ይሁዳ የፈጸመው ተግባር ይህ ነው። 21የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በማገልገልም ሆነ፣ ለእግዚአብሔር ሕግና ትእዛዝ በመገዛት አንጻር ያደረገውን ሁሉ በፍጹም ልቡ አምላኩን በመፈለግ አከናወነ፤ ተሳካለትም።