2 ነገሥት 4 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

2 ነገሥት 4:1-44

የመበለቲቱ ዘይት

1የነቢያት ማኅበር ወገን ከሆነው የአንደኛው ሚስት፣ “አገልጋይህ ባሌ ሞቷል፤ እርሱም እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው እንደ ነበር አንተ ታውቃለህ፤ አሁን ግን ባለ ዕዳ ሁለት ወንዶች ልጆቼን ባሪያ አድርጎ ሊወስዳቸው መጥቷል” ስትል ወደ ኤልሳዕ ጮኸች።

2ኤልሳዕም፣ “ታዲያ እኔ ምን እንዳደርግልሽ ትፈልጊያለሽ? በቤትሽ ምን እንዳለ ንገሪኝ” አላት።

እርሷም፣ “አገልጋይህ ከጥቂት ዘይት በቀር በቤቷ ምንም ነገር የላትም” አለች።

3ኤልሳዕም እንዲህ አላት፤ “እንግዲያው ሂጂና ከጎረቤቶችሽ ሁሉ ጥቂት ሳይሆን ብዙ ማድጋ ተዋሺ፤ 4ገብተሽም መዝጊያውን በአንቺና በልጆችሽ ላይ የኋሊት ዝጊው፤ ዘይቱንም በማድጋዎቹ ሁሉ ጨምሪ፤ እያንዳንዱ ማድጋ ሲሞላም ወደ አንድ በኩል አኑሪው።”

5ስለዚህ ትታው ሄዳ መዝጊያውን በራሷና በልጆቿ ላይ የኋሊት ዘጋችው፤ ማድጎቹን እያቀረቡላትም እርሷ ትሞላ ጀመር። 6ማድጋዎቹ ሁሉ ከሞሉ በኋላ ልጇን፣ “ሌላ ማድጋ አምጣ” አለችው።

እርሱ ግን፣ “ምንም የቀረ ማድጋ የለም” ሲል መለሰላት። ከዚያም ዘይቱ መውረዱን አቆመ።

7እርሷም ሄዳ ይህንኑ ለእግዚአብሔር ሰው ነገረችው። እርሱም፣ “ሄደሽ ዘይቱን በመሸጥ ዕዳሽን ክፈይ፤ የተረፈውም ለአንቺና ለልጆችሽ መተዳደሪያ ይሁን” አላት።

የሱነማዪቱ ልጅ ከሞት ተነሣ

8አንድ ቀን ኤልሳዕ ወደ ሱነም ሄደ። በዚያም አንዲት ሀብታም ሴት ነበረች፤ እርሷም ምግብ እንዲበላ አጥብቃ ለመነችው፤ በዚያም ባለፈ ቍጥር ምግብ ለመብላት ወደ ቤቷ ይገባ ነበር። 9ሴቲቱም ባልዋን እንዲህ አለችው፤ “ይህ አዘውትሮ በደጃችን የሚያልፍ ሰው፣ ቅዱስ የእግዚአብሔር ሰው መሆኑን ዐውቃለሁ፤ 10ስለዚህ በሰገነቱ ላይ አንዲት ትንሽ ክፍል ቤት ሠርተን ዐልጋና ጠረጴዛ፣ ወንበርና ፋኖስ እናስገባለን፤ ከዚያም ወደ እኛ በሚመጣበት ጊዜ ሁሉ ማረፊያ ትሆነዋለች።”

11አንድ ቀን ኤልሳዕ ወደዚያው መጥቶ ወደ ማረፊያ ክፍሉ በመውጣት ጋደም አለ። 12አገልጋዩን ግያዝንም፣ “ሱነማዪቱን ጥራት” አለው፤ በጠራትም ጊዜ መጥታ በፊቱ ቆመች። 13ኤልሳዕም፣ “ ‘ለእኛ ስትይ በጣም ተቸግረሻል፤ ምን እንዲደረግልሽ ትፈልጊአለሽ? ለንጉሡ ወይስ ለሰራዊቱ አዛዥ የምንነግርልሽ ጕዳይ አለን?’ ብለህ ጠይቃት” አለው።

ሴቲቱም መልሳ፣ “እኔ እኮ የምኖረው በገዛ ወገኖቼ መካከል ነው” አለችው።

14ኤልሳዕም፣ “ታዲያ ምን ይደረግላት” ሲል ጠየቀ።

ግያዝም፣ “ልጅ እኮ የላትም፤ ባሏም ሸምግሏል” አለ።

15ኤልሳዕም፣ “በል እንግዲያው ጥራት” አለው፤ እርሱም ጠርቷት መጥታ በራፉ ላይ ቆመች። 16ኤልሳዕም፣ “የዛሬ ዓመት በዚሁ ጊዜ ወንድ ልጅ ትታቀፊያለሽ” አላት፤

እርሷም፣ “አይደለም ጌታዬ፣ አንተ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፤ ኋላ አገልጋይህን መዋሸት እንዳይሆንብህ!” አለችው።

17ሴትዮዋም ፀነሰች፤ ኤልሳዕ እንደ ነገራትም በተባለው ጊዜ ወንድ ልጅ ወለደች።

18ሕፃኑ አደገ፤ አንድ ቀንም አባቱ ከዐጫጆች ጋር ወደ ነበረበት ቦታ ሄደ። 19አባቱንም፣ “ራሴን! ራሴን!” አለው። አባቱም አገልጋዩን፣ “ተሸክመህ ወደ እናቱ አድርሰው” አለው።

20አገልጋዩም አንሥቶ እናቱ ዘንድ አደረሰው፤ ልጁም እስከ እኩለ ቀን ድረስ በእናቱ ጭን ላይ ተቀመጠ፤ ከዚያም ሞተ። 21ወደ ላይ ወጥታም በእግዚአብሔር ሰው ዐልጋ ላይ አስተኛችው፤ በሩንም ዘግታበት ወጣች።

22ከዚያም ባሏን ጠርታ፣ “ወደ እግዚአብሔር ሰው በፍጥነት ደርሼ እንድመለስ አንድ አገልጋይና አንድ አህያ ላክልኝ” አለችው።

23ባሏም፣ “ዛሬ ወደ እርሱ መሄድ ለምን አስፈለገሽ? መባቻ ወይም ሰንበት አይደለም” አላት።

እርሷም፣ “ምንም አይደል፤ ልሂድ” አለችው።

24ከዚያም አህያውን ጭና አገልጋይዋን፣ “ቶሎ ቶሎ ንዳ፤ እኔ ካልነገርኩህ በቀር ለእኔ ብለህ አታዝግም” አለችው። 25ስለዚህ ተነሥታ የእግዚአብሔር ሰው ወዳለበት ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ሄደች።

የእግዚአብሔር ሰው በሩቁ ሲያያት አገልጋዩን ግያዝን እንዲህ አለው፤ “ሱነማዪቱን አየሃት፤ ያቻትና! 26በል ሩጠህ ሂድና፣ ‘ምነው ደኅና አይደለሽምን? ባልሽ ደኅና አይደለምን? ልጅሽስ ደኅና አይደለምን?’ ብለህ ጠይቃት።”

እርሷ፣ “ሁሉ ነገር ደኅና ነው” አለች።

27የእግዚአብሔር ሰው ወዳለበት ተራራ ስትደርስም እግሩ ላይ ተጠመጠመች፤ ግያዝ ሊያስለቅቃት ሲመጣ፣ የእግዚአብሔር ሰው ግን፣ “እጅግ ዐዝናለችና ተዋት! እግዚአብሔር ይህን ለምን ከእኔ እንደ ሰወረውና እንዳልነገረኝ አልገባኝም” አለ።

28እርሷም፣ “ጌታዬ፤ ለመሆኑ እኔ ልጅ እንድትሰጠኝ ጠይቄህ ነበርን? ‘አጕል ተስፋ እንዳትሰጠኝ’ አላልሁህምን?” አለችው።

29ኤልሳዕም ግያዝን፣ “እንግዲህ ወገብህን ታጠቅ፤ በትሬን ያዝና ሩጥ፤ መንገድ ላይ ሰው ብታገኝ ሰላም አትበል፤ ማንም ሰው ሰላም ቢልህ መልስ አትስጥ፤ በትሬንም በልጁ ፊት ላይ አድርግ” አለው።

30የልጁ እናት ግን፣ “ሕያው እግዚአብሔርን፤ በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፣ ፈጽሞ ትቼህ አልሄድም” አለችው፤ ስለዚህ ተነሥቶ ተከተላት።

31ግያዝም ቀድሟቸው ሄዶ በትሩን በልጁ ፊት ላይ አደረገ፤ ነገር ግን ድምፅም፣ ምላሽም አልነበረም። ስለዚህ ግያዝ ወደ ኤልሳዕ ተመልሶ፣ “ልጁ አልነቃም” አለው።

32ኤልሳዕ ወደ ቤት ሲገባም ልጁ ሞቶ በዐልጋው ላይ ተጋድሞ ነበር። 33ወደ ውስጥም ገባ፤ ከዚያም በሩን በራሱና በልጁ ላይ ዘግቶ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ።

34በዐልጋው ላይ ወጥቶም በልጁ ላይ ተጋደመና አፉን በአፉ፣ ዐይኑን በዐይኑ፣ እጁን በእጁ ላይ አደረገ። ሙሉ በሙሉ እንደተዘረጋበትም፣ የልጁ ሰውነት መሞቅ ጀመረ። 35ኤልሳዕም ተነሥቶ በቤቱ ውስጥ ወዲያና ወዲህ ከሄደ በኋላ ወደ ዐልጋው ወጥቶ እንደ ገና በልጁ ላይ ሙሉ ለሙሉ ተዘረጋበት፤ ልጁም ሰባት ጊዜ አስነጠሰውና ዐይኖቹን ከፈተ።

36ኤልሳዕም ግያዝን ጠርቶ፣ “ሱነማዪቱን ጥራት፤” አለው፤ እርሱም ጠራት። እንደ መጣችም፣ “በይ ልጅሽን ውሰጂ” አላት። 37እርሷም ገብታ በእግሩ ላይ ወደቀች፤ በምድርም ላይ ተደፋች፤ ልጇንም ይዛ ወጣች።

መርዛሙ ወጥ

38ኤልሳዕ ወደ ጌልገላ ተመለሰ፤ በዚያም አገር ራብ ነበረ። የነቢያት ማኅበር በፊቱ ተቀምጠው ሳለ አገልጋዩን፣ “ትልቁን ምንቸት ጣድና ለእነዚህ ሰዎች ወጥ ሥራላቸው” አለው።

39ከእነርሱም አንዱ ቅጠላ ቅጠል ለማምጣት ወደ ሜዳ ወጥቶ፤ ዱር በቀል ሐረግ አገኘ፤ ከሐረጉም ላይ የቅል ፍሬ ለቅሞ በልብሱ ሙሉ ይዞ ተመለሰና ቈራርጦ በወጡ ምንቸት ውስጥ ጨመረው፤ ምን እንደ ሆነ ግን ማንም አላወቀም። 40ሰዎቹ እንዲመገቡትም ወጡ ወጣ፤ ገና አንደ ቀመሱትም፣ “የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፤ በምንቸቱ ውስጥ የሚገድል መርዝ አለ!” ብለው ጮኹ፤ ሊመገቡትም አልቻሉም። 41ኤልሳዕም፣ “እስቲ ዱቄት አምጡልኝ” አለ። ያንንም በምንቸቱ ውስጥ ጨምሮ፣ “እንዲመገቡት ለሰዎቹ አቅርቡላቸው” አለ። በምንቸቱም ውስጥ ጕዳት የሚያስከትል ነገር አልተገኘም።

አንድ መቶ ሰው ተመገበ

42አንድ ሰው ከበኵራቱ ፍሬ የተጋገረ ሃያ የገብስ ሙልሙልና ጥቂት የእሸት ዛላዎች በአቍማዳ ይዞ ከበኣልሻሊሻ ወደ እግዚአብሔር ሰው መጣ። ኤልሳዕም አገልጋዩን፣ “ሰዎቹ እንዲበሉት ስጣቸው” አለው። 43አገልጋዩም፣ “ይህን እንዴት አድርጌ ለመቶ ሰው አቀርባለሁ?” ሲል ጠየቀ፤

ኤልሳዕ ግን፣ “እንዲበሉት ለሰዎቹ ስጣቸው፤ እግዚአብሔር፣ ‘በልተው ይተርፋቸዋል’ ይላልና” አለው። 44ከዚያም አቀረበላቸው፤ እግዚአብሔር እንደ ተናገረውም በልተው ተረፋቸው።