2 ነገሥት 2 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

2 ነገሥት 2:1-25

ኤልያስ ወደ ሰማይ ዐረገ

1እግዚአብሔር ኤልያስን በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ የሚወስድበት ጊዜ ሲደርስ፣ ኤልያስና ኤልሳዕ ከጌልገላ ተነሥተው ይጓዙ ነበር። 2ኤልያስም ኤልሳዕን፣ “እግዚአብሔር እኔን ወደ ቤቴል ልኮኛልና አንተ በዚሁ ቈይ” አለው።

ኤልሳዕ ግን፣ “ሕያው እግዚአብሔርን፣ በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፤ ከአንተ አልለይም” አለው። ስለዚህ አብረው ወደ ቤቴል ወረዱ።

3በቤቴል የነበሩ የነቢያት ማኅበር ወደ ኤልሳዕ ወጥተው፣ “እግዚአብሔር፣ ጌታህን ኤልያስን ዛሬ ከአንተ ነጥሎ እንደሚወስደው ዐውቀሃልን?” አሉት።

ኤልሳዕም፣ “አዎን ዐውቄአለሁ፤ እናንተ ግን ዝም በሉ” አለ።

4ከዚያም ኤልያስ፣ “ኤልሳዕ ሆይ፤ እግዚአብሔር እኔን ወደ ኢያሪኮ ልኮኛልና አንተ በዚሁ ቈይ” አለው።

እርሱም፤ “ሕያው እግዚአብሔርን፣ በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፤ ከአንተ አልለይም” ሲል መለሰ። ስለዚህ አብረው ወደ ኢያሪኮ ሄዱ።

5በኢያሪኮ የነበሩትም የነቢያት ማኅበር ወደ ኤልሳዕ ወጥተው፣ “ለመሆኑ እግዚአብሔር፣ ጌታህን ኤልያስን ዛሬ ከአንተ ነጥሎ እንደሚወስደው ዐውቀሃልን?” አሉት።

እርሱም፣ “አዎን ዐውቄአለሁ፤ እናንተ ግን ዝም በሉ” ሲል መለሰ።

6ከዚያም ኤልያስ፣ “እግዚአብሔር እኔን ወደ ዮርዳኖስ ልኮኛልና አንተ እዚሁ ቈይ” አለው።

እርሱም፣ “ሕያው እግዚአብሔርን፤ በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፤ ከአንተ አልለይም” ሲል መለሰ። ስለዚህ ሁለቱም አብረው ሄዱ።

7ከነቢያትም ማኅበር አምሳው ሄደው፣ ኤልያስና ኤልሳዕ ከቆሙበት ከዮርዳኖስ ትይዩ ራቅ ብለው ቆሙ። 8ኤልያስም ካባውን አውልቆ ጠቀለለውና ውሃውን መታበት፤ ከዚያም ውሃው ግራና ቀኝ ተከፈለ፤ ሁለቱም በደረቅ ምድር ተሻገሩ።

9ከተሻገሩ በኋላም ኤልያስ ኤልሳዕን፤ “ከአንተ ከመወሰዴ በፊት ምን ላደርግልህ እንደምትፈልግ ንገረኝ” አለው።

ኤልሳዕም፣ “መንፈስህ በዕጥፍ እንዲያድርብኝ እለምንሃለሁ” ብሎ መለሰ።

10ኤልያስም፣ “አስቸጋሪ ነገር ጠይቀሃል፤ ይሁን እንጂ እኔ ከአንተ ስወሰድ ብታየኝ፣ እንዳልከው ይሆንልሃል፤ አለዚያ ግን አይሆንም” አለው።

11እያዘገሙም ሲነጋገሩ ሳለ፣ የእሳት ሠረገላና የእሳት ፈረሶች ድንገት በመካከላቸው ገብተው ሁለቱን ለዩአቸው፤ ኤልያስም በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ ዐረገ። 12ኤልሳዕም ይህን አይቶ፣ “አባቴ አባቴ የእስራኤል ሠረገሎችና ፈረሰኞች!” ብሎ ጮኸ፤ ዳግመኛም ኤልያስን አላየውም፤ ከዚያም የገዛ ልብሱን ይዞ ከሁለት ቦታ ቀደደው። 13እርሱም ከኤልያስ የወደቀውን ካባ አነሣ፤ ተመልሶም በዮርዳኖስ ወንዝ ዳር ቆመ። 14ከኤልያስ፣ የወደቀውንም ካባ ይዞ ውሃውን መታና፣ “የኤልያስ አምላክ እግዚአብሔር ወዴት ነው?” አለ። ውሃውን ሲመታውም በግራና በቀኝ ተከፍሎለት ተሻገረ። 15ከኢያሪኮም መጥተው ይህን ያዩ የነበሩት የነቢያት ወገኖች፣ “የኤልያስ መንፈስ በኤልሳዕ ላይ ዐርፏል” አሉ፤ ሊያገኙትም ሄደው በፊቱ ወደ መሬት ዝቅ ብለው እጅ ነሡ። 16ከዚያም፣ “እነሆ፤ እኛ አገልጋዮችህ እዚህ አምሳ ጠንካራ ሰዎች አሉን፤ ምናልባትም የእግዚአብሔር መንፈስ ጌታህን አንሥቶ ከአንዱ ተራራ ላይ አስቀምጦት ወይም ከአንዱ ሸለቆ አግብቶት ይሆናልና እስቲ ሄደው ይፈልጉት” አሉት። ኤልሳዕም፣ “አይሆንም፤ አትላኳቸው” አለ።

17አይሆንም ለማለት ዕፍረት እስኪሰማው ድረስ ግድ አሉት፤ ስለዚህ፣ “በሉ እንግዲያው ላኳቸው” አለ። እነርሱም አምሳ ሰዎች ላኩ፤ ሰዎቹም ሦስት ቀን ሙሉ ፈልገው ሳያገኙት ቀሩ። 18በኢያሪኮ ቈይቶ ወደ ነበረው ወደ ኤልሳዕ በተመለሱም ጊዜ፣ “ቀድሞውንስ ቢሆን አትሂዱ ብያችሁ አልነበረምን?” አላቸው።

የውሃው መፈወስ

19የከተማዪቱም ሰዎች ኤልሳዕን፣ “እነሆ ጌታችን፤ እንደምታያት ይህች ከተማ ለኑሮ የተመቸች ናት፤ ይሁን እንጂ ውሃው መጥፎ ሲሆን ምድሪቱም ፍሬ የማትሰጥ ናት” አሉት።

20እርሱም፣ “እስቲ በአዲስ ማሰሮ ጨው ጨምራችሁ አምጡልኝ” አለ፤ እንዳለውም አመጡለት። 21ከዚያም ወደ ውሃው ምንጭ ሄዶ ጨው ጣለበትና “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ይህን ውሃ ፈውሸዋለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲያ ለሞት ምክንያት አይሆንም፤ ምድሪቱንም ፍሬ እንዳትሰጥ አያደርጋትም’ አለ።” 22ኤልሳዕ እንደ ተናገረውም ውሃው እስከ ዛሬ ድረስ የተፈወሰ ነው።

በኤልሳዕ ላይ ተፌዘበት

23ኤልሳዕም ከዚያ ተነሥቶ ወደ ቤቴል ወጣ፤ በመንገድ ላይ ሲሄድ ሳለም ልጆች ከከተማ ወጥተው፣ “አንተ መላጣ፤ ውጣ! አንተ መላጣ ውጣ!” እያሉ አፌዙበት። 24ኤልሳዕም ዘወር ብሎ ተመለከታቸውና በእግዚአብሔር ስም ረገማቸው፤ ከዚያም ሁለት እንስት ድቦች ከዱር ወጥተው ከልጆቹ አርባ ሁለቱን ሰባበሯቸው። 25እርሱም ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ሄደ፤ ከዚያም ወደ ሰማርያ ተመለሰ።