2 ነገሥት 18 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

2 ነገሥት 18:1-37

የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ

18፥2-4 ተጓ ምብ – 2ዜና 29፥1-231፥1

18፥5-7 ተጓ ምብ – 2ዜና 31፥20-21

18፥9-12 ተጓ ምብ – 2ነገ 17፥3-7

1የእስራኤል ንጉሥ የኤላ ልጅ ሆሴዕ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የአካዝ ልጅ ሕዝቅያስ ነገሠ። 2በነገሠም ጊዜ ዕድሜው ሃያ አምስት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ሃያ ዘጠኝ ዓመት ገዛ። እናቱ የዘካርያስ ልጅ ስትሆን ስሟ አቢያ18፥2 በዕብራይስጡ አብያ ማለት አብግያ ማለት ነው። ይባል ነበር። 3አባቱ ዳዊት እንዳደረገው ሁሉ፣ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት መልካም ነገር አደረገ። 4በየኰረብታው ላይ ያሉትን ማምለኪያዎች አስወገደ፤ አዕማደ ጣዖታትን ሰባበረ፤ የአሼራን ምስል ዐምዶች ቈራረጠ፤ ሙሴ የሠራውን የናስ እባብ፣ እስራኤላውያን እስከዚያች ጊዜ ድረስ ዕጣን ያጤሱለት ስለ ነበር ሰባበረው፤ ይህም ነሑሽታን18፥4 ነሑሽታን የሚለው ቃል ድምፅ ነሖስ፣ እባብ እንዲሁም ርኩስ ነገር ከሚለው የቃል ድምፅ ጋር አንድ ዐይነት ነው። ይባል ነበር።

5ሕዝቅያስም በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ታመነ፤ ከእርሱ በፊትም ሆነ ከእርሱ በኋላ ከይሁዳ ነገሥታት ሁሉ፣ እንደ እርሱ ያለ አልነበረም። 6ከእግዚአብሔር ጋር ተጣበቀ፤ እርሱን ከመከተል ወደ ኋላ አላለም፤ እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጠውንም ትእዛዞች ጠበቀ። 7እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለ ነበር የሚያደርገው ሁሉ ተከናወነለት። በአሦር ንጉሥ ላይ ዐመፀ፤ ግብር መገበሩንም ተወ። 8እስከ ጋዛና እስከ ግዛቷ ዳርቻ በመዝለቅ ፍልስጥኤማውያንን ከመጠበቂያ ማማ እስከ ተመሸገችው ከተማ ድረስ ድል አደረጋቸው።

9ሕዝቅያስ በነገሠ በአራተኛው ዓመት፣ የእስራኤልም ንጉሥ የኤላ ልጅ ሆሴዕ በነገሠ በሰባተኛው ዓመት፣ የአሦር ንጉሥ ስልምናሶር ወደ ሰማርያ ገሥግሦ ከተማዪቱን ከበባት፤ 10በሦስተኛውም ዓመት መጨረሻ ያዛት። ሰማርያ የተያዘችውም ሕዝቅያስ በነገሠ በስድስተኛው ዓመት፣ ሆሴዕ በእስራኤል ላይ በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት ነበር። 11የአሦር ንጉሥ እስራኤልን ማርኮ ወደ አሦር በማፍለስ በአላሔ፣ በጎዛን ውስጥ በአቦር ወንዝ አጠገብና በሜዶን ከተሞች አሰፈራቸው። 12ይህ የደረሰባቸውም የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ያዘዘውን የአምላካቸውን የእግዚአብሔርን ቃል ሁሉ ከመስማት ይልቅ ኪዳኑን ስላፈረሱ ነበር፤ ትእዛዞቹን አላደመጡም፤ ደግሞም አልፈጸሙም።

13ሕዝቅያስ በነገሠ በዐሥራ አራተኛው ዓመት፣ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም የተመሸጉትን የይሁዳን ከተሞች ሁሉ አደጋ ጥሎ ያዛቸው። 14ስለዚህ የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ፣ “በደለኛው እኔ ነኝ፤ ተመለስልኝ፤ እኔም የምትጠይቀኝን ሁሉ እከፍላለሁ፤” ሲል በለኪሶ ወደ ሰፈረው ወደ አሦር ንጉሥ ይህን መልእክት ላከ። የአሦርም ንጉሥ፣ የይሁዳን ንጉሥ ሕዝቅያስን ሦስት መቶ መክሊት18፥14 10 ሜትሪክ ቶን ያህል ነው። ብርና ሠላሳ መክሊት18፥14 ሜትሪክ ቶን ያህል ነው። ወርቅ እንዲያገባለት ጠየቀው።

15ስለዚህ ሕዝቅያስ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥቱ ግምጃ ቤቶች የሚገኘውን ብር ሁሉ ሰጠው።

16በዚህ ጊዜም የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ፣ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መዝጊያዎችና መቃኖች ላይ የለበጠውን ወርቅ ነቃቅሎ ለአሦር ንጉሥ ሰጠው።

ሰናክሬም ኢየሩሳሌምን አስፈራራ

18፥1317-37 ተጓ ምብ – ኢሳ 36፥1-22

18፥17-35 ተጓ ምብ – 2ዜና 32፥9-19

17የአሦርም ንጉሥ ከለኪሶ የጦሩን ጠቅላይ አዛዥ፣ ዋና አዛዡንና የጦር መሪውን ከታላቅ ሰራዊት ጋር የይሁዳ ንጉሥ ወዳለበት ወደ ኢየሩሳሌም ላከ፤ እነርሱም ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው፣ ወደ ልብስ ዐጣቢው ዕርሻ በሚወስደው መንገድ ላይ የሚገኘው የላይኛው ኵሬ ውሃ በመስኖ የሚወርድበትን ስፍራ ያዙ። 18ወደ ንጉሡም ላኩበት፤ ከዚያም የቤተ መንግሥቱ አዛዥ የሆነው የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም፣ ጸሓፊው ሳምናስ እንዲሁም ታሪክ ጸሐፊው የአሳፍ ልጅ ዮአስ ወደ እነርሱ ሄዱ።

19የጦር መሪውም እንዲህ አላቸው፤ “ሕዝቅያስን እንዲህ በሉት፤

“ ‘ታላቁ የአሦር ንጉሥ የሚለው ይህ ነው፤ “ለመሆኑ እንዲህ የልብ ልብ እንድታገኝ ያደረገህ ምንድን ነው? 20የጦር ስልትና ኀይል አለኝ ትላለህ፣ ነገር ግን ወሬ ብቻ ነው። በእኔ ላይ እንዲህ ያመፅኸውስ በማን ተመክተህ ነው? 21እነሆ፤ እንዲህ የምትመካባት ግብፅ የሚደገፍባትን ሰው እጅ ወግታ የምታቈስል የተቀጠቀጠች ሸንበቆ ናት። የግብፅ ንጉሥ ፈርዖንም ለሚመኩበት ሁሉ እንደዚሁ ነው።” 22ደግሞም፣ “የምንመካው በአምላካችን በእግዚአብሔር ነው” የምትለኝ ከሆነም፣ ሕዝቅያስ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን፣ “ማምለክ ያለባችሁ ኢየሩሳሌም ባለው በዚህ መሠዊያ ፊት ነው” ብሎ የኰረብታ ላይ መመለኪያዎቹንና መሠዊያዎቹን ያስፈረሰበት እርሱ አይደለምን? 23ከሆነልህ ከጌታዬ ከአሦር ንጉሥ ጋር ውርርድ ግጠም፤ የሚጋልቧቸው ሰዎች ማግኘት የምትችል ከሆነ፣ ሁለት ሺሕ ፈረሶች እሰጥሃለሁ። 24የምትመካው በግብፅ ሠረገሎችና18፥24 ወይም፣ ሠረገለኞች ፈረሶች ሆኖ ሳለ ከጌታዬ የበታች የጦር ሹማምት እንኳ አንዱን እንዴት መመለስ ትችላለህ? 25ከዚህም በቀር አደጋ ጥዬ ይህችን ስፍራ ለማጥፋት የመጣሁት፣ ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ ይመስልሃል? በዚህች አገር ላይ ዘምቼ እንዳጠፋት የነገረኝ ራሱ እግዚአብሔር ነው።’ ”

26ከዚያም የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም ሳምናስና ዮአስ የጦር መሪውን፣ “እኛ አገልጋዮችህ ስለምንሰማ፣ እባክህን በሶርያ ቋንቋ ተናገር፤ በቅጥሩ ላይ ያሉት ሰዎች በሚሰሙት በዕብራይስጥ አትናገረን” አሉት።

27የጦር አዛዡም፣ “ለመሆኑ ጌታዬ ይህን እንድናገር የላከኝ፣ ለጌታችሁና ለእናንተ ብቻ ነውን? እነርሱም እንደ እናንተው ገና ኵሳቸውን ይበሉ ዘንድ፣ ሽንታቸውንም ይጠጡ ዘንድ በቅጥሩ ላይ ለተቀመጡት ጭምር አይደለምን?”

28ከዚያም የጦር አዛዡ ቆሞ ድምፁን ከፍ በማድረግ በዕብራውያን ቋንቋ እንዲህ ሲል ተናገረ፤ “እንግዲህ የታላቁን የአሦርን ንጉሥ ቃል ስሙ! 29ንጉሡ የሚለውም ይህ ነው፤ ‘ከእጄ ሊያድናችሁ አይችልምና ሕዝቅያስ እንዳያታልላችሁ፤ 30ደግሞም ሕዝቅያስ፣ “እግዚአብሔር ያለ ጥርጥር ያድነናል፤ ይህችም ከተማ ለአሦር ንጉሥ ዐልፋ አትሰጥም” በማለት በእግዚአብሔር እንድትታመኑ የሚነግራችሁን አትቀበሉ።’

31“ሕዝቅያስንም አትስሙት፤ የአሦር ንጉሥ የሚለው ይህ ነው፤ ‘ከእኔ ጋር ሰላም መሥርቱ፤ እጃችሁን ስጡ፤ ከዚያም ከእናንተ እያንዳንዱ ከገዛ ወይኑና ከገዛ በለሱ ይበላል፤ ከገዛ ጕድጓዱም ውሃ ይጠጣል፤ 32ይህም የሚሆነው የእናንተኑ ወደምትመስለው ምድር እህልና የወይን ጠጅ፣ ዳቦና የወይን ተክል፣ የወይራ ዛፍና ማር ወዳለባት እስካገባችሁ ድረስ ነው፤ እናንተም ሞትን ሳይሆን ሕይወትን ምረጡ።’

“ሕዝቅያስ፣ ‘እግዚአብሔር ይታደገናል’ በማለት ስለሚያሳስታችሁ አትስሙት። 33ለመሆኑ ከአሕዛብ አማልክት ምድሩን ከአሦር ንጉሥ እጅ የታደገ ማን አለ? 34የሐማትና የአርፋድ አማልክት እስቲ የት አሉ? የሴፈርዋይም፣ የሄናና የዒዋም አማልክት ታዲያ የት ደረሱ? ሰማርያን ከእጄ አድነዋታልን? 35ከእነዚህ አገሮች አማልክት ሁሉ አገሩን ከእኔ ለማዳን የቻለ ማን አለ? ታዲያ እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ከእጄ ሊታደጋት እንዴት ይችላል?”

36ነገር ግን ሕዝቡ ዝም አለ፤ ምንም መልስ አልሰጠም፤ ንጉሡ፣ “መልስ እንዳትሰጡ” ሲል አዝዞ ነበርና።

37ከዚያም የቤተ መንግሥቱ አዛዥ የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም፣ ጸሓፊው ሳምናስ እንዲሁም ታሪክ ጸሓፊው የአሳፍ ልጅ ዮአስ ልብሳቸውን ቀደዱ፤ ወደ ሕዝቅያስም መጥተው የጦር አዛዡ ያላቸውን ነገሩት።