2 ቆሮንቶስ 11 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

2 ቆሮንቶስ 11:1-33

ጳውሎስና ሐሰተኞች ሐዋርያት

1ጥቂቱን ሞኝነቴን እንደምትታገሡኝ ተስፋ አደርጋለሁ፤ በርግጥም እየታገሣችሁኝ ነው። 2በእግዚአብሔር ቅናት እቀናላችኋለሁ፤ እናንተን እንደ ንጽሕት ድንግል ለክርስቶስ ለማቅረብ ለአንድ ባል ዐጭቻችኋለሁና። 3ነገር ግን እባብ ሔዋንን በተንኰል እንዳሳታት ምናልባት የእናንተም ልቡና ተበላሽቶ ለክርስቶስ ካላችሁ ቅንነትና ንጽሕና እንዳትወሰዱ እሠጋለሁ። 4ምክንያቱም አንድ ሰው ወደ እናንተ መጥቶ እኛ ከሰበክንላችሁ ኢየሱስ ሌላ ኢየሱስ ቢሰብክላችሁ፣ ወይም ከተቀበላችሁት መንፈስ የተለየ መንፈስ ብትቀበሉ፣ ወይም ከተቀበላችሁት ወንጌል የተለየ ወንጌል ብትቀበሉ፣ ነገሩን በዝምታ ታልፉታላችሁ ማለት ነው። 5እኔ ግን “ታላላቅ ሐዋርያት” ከሚባሉት በምንም የማንስ አይመስለኝም። 6የንግግር ችሎታ ባይኖረኝም እንኳ፣ ዕውቀት ግን አለኝ፤ ይህንም በሁሉ መንገድ በሚገባ ግልጽ አድርገንላችኋል።

7እናንተ ከፍ እንድትሉ ራሴን ዝቅ አድርጌ የእግዚአብሔርን ወንጌል ያለ ዋጋ ለእናንተ መስበኬ እንደ ኀጢአት ተቈጥሮብኝ ይሆን? 8እናንተን ለማገልገል ስል ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ርዳታ በመቀበሌ እነርሱን ዘርፌአቸዋለሁ። 9ከእናንተም ጋር ሳለሁ አንዳች ባስፈለገኝ ጊዜ፣ ከመቄዶንያ የመጡ ወንድሞች የሚያስፈልገኝን ስለ ሰጡኝ ለማንም ሸክም አልሆንሁም። በእናንተ ላይ በምንም ነገር ሸክም እንዳልሆን ተጠንቅቄአለሁ፤ ወደ ፊትም እጠነቀቃለሁ። 10የክርስቶስ እውነት በውስጤ እስካለ ድረስ፣ በአካይያ አውራጃ ይህን ትምክሕቴን ማንም ሊገታው አይችልም። 11ይህን የምለው ለምንድን ነው? ስለማልወድዳችሁ ነውን? እንደምወድዳችሁ እግዚአብሔር ያውቃል። 12ከእኛ ጋር እኩል ለመሆን በሥራቸው እየተመኩ ቀን የሚጠብቁትን ሰዎች ምክንያት ለማሳጣት አሁን የማደርገውን ወደ ፊትም አደርጋለሁ።

13እንደነዚህ ያሉ ሰዎች የክርስቶስን ሐዋርያት ለመምሰል ራሳቸውን የሚለዋውጡ፣ ሐሰተኞች ሐዋርያትና አታላዮች ሠራተኞች ናቸው። 14ይህም የሚያስደንቅ ነገር አይደለም፤ ምክንያቱም ሰይጣን ራሱ የብርሃን መልአክ ለመምሰል ራሱን ይለዋውጣል። 15እንግዲህ የእርሱ አገልጋዮች፣ የጽድቅ አገልጋዮች ለመምሰል ራሳቸውን ቢለውጡ የሚያስገርም አይደለም፤ ፍጻሜአቸውም እንደ ሥራቸው ይሆናል።

ጳውሎስ በደረሰበት መከራ ይመካል

16እንደ ገና ይህን እላለሁ፤ ማንም ሰው እንደ ሞኝ አይቍጠረኝ፤ እናንተም የምትቈጥሩኝ ከሆነ፣ እኔም በጥቂቱ እንድመካ እንደ ሞኝ ተቀበሉኝ። 17እንደዚህ ልበ ሙሉ ሆኜ የምናገረው እንደ ሞኝ እንጂ እንደ ጌታ ፈቃድ አይደለም። 18ብዙዎች በዓለማዊ ነገር ስለሚመኩ እኔም ደግሞ እመካለሁ። 19እናንተም ብልኆች ስለ ሆናችሁ ሞኞችን በደስታ ትታገሣላችሁ፤ 20ማንም ተነሥቶ ባሪያ ቢያደርጋችሁ፣ ቢበዘብዛችሁ፣ ለጥቅሙ ሲል ቢጠጋችሁ፣ ቢንቀባረርባችሁ ወይም ፊታችሁን በጥፊ ቢመታችሁ ትታገሣላችሁ። 21እኛ ግን ለዚያ እጅግ ደካሞች መሆናችንን እያፈርሁ እናገራለሁ።

ማንም በድፍረት በሚመካበት ነገር ሁሉ እኔም ደፍሬ መመካት እንደምችል እንደ ሞኝ እናገራለሁ። 22እነርሱ ዕብራውያን ናቸውን? እኔም ነኝ፤ እስራኤላውያን ናቸውን? እኔም ነኝ፤ የአብርሃም ዘር ናቸውን? እኔም ነኝ። 23የክርስቶስ አገልጋዮች ናቸውን? አእምሮውን እንደ ጣለ ሰው ልናገርና እኔ እበልጣቸዋለሁ፤ ደግሞም ብዙ ጊዜ በሥራ ደክሜአለሁ፤ ብዙ ጊዜ ታስሬአለሁ፤ ብዙ ጊዜ ተገርፌአለሁ፤ ብዙ ጊዜ ለሞት ተቃርቤአለሁ። 24አይሁድ ለአርባ ጅራፍ አንድ የቀረው አምስት ጊዜ ገርፈውኛል። 25ሦስት ጊዜ በዱላ ተደብድቤአለሁ፤ አንድ ጊዜ በድንጋይ ተወግሬአለሁ፤ ሦስት ጊዜ የመርከብ አደጋ ደርሶብኛል፤ አንድ ሌሊትና ቀን በባሕር ላይ ዐድሬአለሁ፤ 26ብዙ ጊዜ በጕዞ ተንከራትቻለሁ፤ ደግሞም ለወንዝ ሙላት አደጋ፣ ለወንበዴዎች አደጋ፣ ለገዛ ወገኖቼ አደጋ፣ ለአሕዛብ አደጋ፣ ለከተማ አደጋ፣ ለገጠር አደጋ፣ ለባሕር አደጋ እንዲሁም ለሐሰተኞች ወንድሞች አደጋ ተጋልጬ ነበር። 27ብዙ ጥሬአለሁ፤ ብዙ ደክሜአለሁ፤ ብዙ ጊዜ እንቅልፍ አጥቻለሁ፤ ተርቤአለሁ፤ ተጠምቻለሁ፤ ብዙ ጊዜ ምግብ ሳልቀምስ ኖሬአለሁ፤ በብርድና በዕራቍትነት ተቈራምጃለሁ። 28ሌላውን ነገር ሳልቈጥር፣ ዕለት ዕለት የሚያስጨንቀኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ሐሳብ ነው። 29ደካማ ማን ነው? እኔስ አብሬ አልደክምምን? በኀጢአት የሚሰናከል ማን ነው? እኔስ አልቈጭምን?

30መመካት ካለብኝ፣ ደካማነቴን በሚያሳዩ ነገሮች እመካለሁ። 31ለዘላለም የተመሰገነው የጌታ የኢየሱስ አምላክና አባት እንደማልዋሽ ያውቃል። 32ደማስቆ ሳለሁ ከንጉሥ አርስጦስዮስ በታች የሆነው ገዥ ሊያስይዘኝ ፈልጎ፣ የደማስቆ ሰዎችን ከተማ ያስጠብቅ ነበር። 33ነገር ግን በግንቡ መስኮት በኩል በቅርጫት አውርደውኝ ከእጁ አመለጥሁ።