1 ተሰሎንቄ 1 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

1 ተሰሎንቄ 1:1-10

1ከጳውሎስ፣ ከሲላስና1፥1 ግሪኩ ሲልዋኑስ ይላል። ከጢሞቴዎስ፤

በእግዚአብሔር አብና በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ለሆኑት ለተሰሎንቄ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን፤

ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን1፥1 አንዳንድ ቅጆች ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ የሚለው የላቸውም።

ስለ ተሰሎንቄ ሰዎች እምነት የቀረበ ምስጋና

2በጸሎታችን እያስታወስናችሁ ሁልጊዜ እግዚአብሔርን ስለ ሁላችሁ እናመሰግናለን። 3ከእምነት የሆነውን ሥራችሁን፣ ከፍቅር የመነጨውን ድካማችሁንና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ባላችሁ ተስፋ የተገኘውን ጽናታችሁን በአምላካችንና በአባታችን ፊት ዘወትር እናስባለን።

4በእግዚአብሔር የተወደዳችሁ ወንድሞች ሆይ፤ እርሱ እንደ መረጣችሁ እናውቃለን፤ 5ምክንያቱም ወንጌላችን ወደ እናንተ የመጣው በኀይልና በመንፈስ ቅዱስ፣ በብዙም መረዳት እንጂ በቃል ብቻ አይደለም። ደግሞ ስለ እናንተ ስንል በመካከላችሁ እንዴት እንደ ኖርን ታውቃላችሁ። 6እናንተ እኛንና ጌታን መስላችኋል፤ ምንም እንኳ ብርቱ መከራ ቢደርስባችሁም፣ ቃሉን በመንፈስ ቅዱስ ደስታ ተቀብላችኋል። 7ከዚህም የተነሣ በመቄዶንያና በአካይያ ለሚገኙ ምእመናን መልካም ምሳሌ ሆናችኋል። 8የጌታ ቃል ከእናንተ ወጥቶ በመቄዶንያና በአካይያ መሰማቱ ብቻ ሳይሆን፣ በእግዚአብሔር ያላችሁ እምነት በሁሉ ቦታ ታውቋል፤ ስለዚህ እኛ በዚህ ጕዳይ ላይ ምንም መናገር አያስፈልገንም፤ 9በእንዴት ያለ አቀባበል እንደ ተቀበላችሁንና ሕያውና እውነተኛ የሆነውን አምላክ ለማገልገል ከጣዖታት ወደ እግዚአብሔር እንዴት እንደ ተመለሳችሁ እነርሱ ራሳቸው ይናገራሉ፤ 10ደግሞም ከሙታን ያስነሣውንና ከሰማይ የሚመጣውን ልጁን፣ ከሚመጣውም ቍጣ የሚያድነንን ኢየሱስን እንዴት እንደምትጠባበቁ ይናገራሉ።