1 ቆሮንቶስ 9 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

1 ቆሮንቶስ 9:1-27

የሐዋርያ መብት

1እኔ ነጻ ሰው አይደለሁምን? ሐዋርያስ አይደለሁምን? ጌታችንን ኢየሱስን አላየሁትምን? እናንተስ በጌታ የድካሜ ፍሬዎች አይደላችሁምን? 2ለሌሎች ሐዋርያ ባልሆን እንኳ ለእናንተ ግን በርግጥ ሐዋርያ ነኝ፤ ምክንያቱም በጌታ የሐዋርያነቴ ማኅተም እናንተ ናችሁ።

3ለሚመረምሩኝ የምሰጠው መልስ ይህ ነው። 4ለመሆኑ፣ የመብላትና የመጠጣት መብት የለንምን? 5እንደ ሌሎቹ ሐዋርያት፣ እንደ ጌታ ወንድሞችና እንደ ኬፋ9፥5 ጴጥሮስ ማለት ነው። ሁሉ፣ እኛስ አማኝ ሚስት ይዘን የመዞር መብት የለንምን? 6ወይስ ጥረን ግረን መኖር ያለብን እኔና በርናባስ ብቻ ነን?

7ለመሆኑ በገዛ ገንዘቡ በወታደርነት የሚያገለግል ማን ነው? ወይን ተክሎ ፍሬውን የማይበላ ማን ነው? መንጋ እየጠበቀ የከብቱን ወተት የማይጠጣ ማን ነው? 8ይህን የምናገረው እንደ ሰው አስተሳሰብ ነውን? የኦሪትስ ሕግ ይህንኑ ይል የለምን? 9በሙሴ ሕግ፣ “የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር” ተብሎ ተጽፏልና። ለመሆኑ፣ እግዚአብሔርን ያሳሰበው የበሬ ጕዳይ ነውን?

10ይህን የተናገረው በርግጥ ስለ እኛ አይደለምን? የተጻፈው በትክክል ስለ እኛ ነው፤ ዐራሹ የሚያርሰው፣ አበራዩ የሚያበራየው ከምርቱ ድርሻ እንዳለው ተስፋ በማድረግ ነውና። 11እኛ በእናንተ መካከል መንፈሳዊ ዘር ዘርተን ከሆነ ለሥጋ የሚሆን ነገር ብናጭድ ትልቅ ነገር መሆኑ ነውን? 12ሌሎች ይህን መብት ከእናንተ ማግኘት ከቻሉ፣ እኛ ይበልጥ ማግኘት አይገባንምን?

እኛ ግን በዚህ መብት አልተጠቀምንም፤ ይልቁንም ለክርስቶስ ወንጌል ዕንቅፋት እንዳንሆን ሁሉንም ነገር እንታገሣለን። 13በቤተ መቅደስ የሚያገለግሉ ምግባቸውን ከቤተ መቅደስ እንደሚያገኙ፣ በመሠዊያውም የሚያገለግሉ ከመሥዋዕቱ እንደሚካፈሉ አታውቁምን? 14እንደዚሁም ወንጌልን የሚሰብኩ ለኑሮ የሚያስፈልጋቸውን ከወንጌል እንዲቀበሉ ጌታ አዝዟል።

15እኔ ግን ከእነዚህ መብቶች በአንዱ እንኳ አልተጠቀምሁም፤ አሁንም ይህን የምጽፍላችሁ እንደነዚህ ያሉትን ነገሮች ታደርጉልኛላችሁ በሚል ተስፋ አይደለም፤ ማንም ትምክሕቴን ከንቱ ከሚያደርግብኝ ሞት ይሻለኛልና። 16ወንጌልን መስበኬ አያስመካኝም፤ የምሰብከው ግዴታዬ ስለሆነ ነው፤ ወንጌልን ባልሰብክ ግን ወዮልኝ። 17በፈቃደኝነት ብሰብክ ሽልማት አለኝ፤ በፈቃደኝነት ካልሆነ ግን፣ የምፈጽመው ተግባር የተጣለብኝን ዐደራ መወጣት ብቻ ይሆናል። 18ታዲያ ሽልማቴ ምንድን ነው? ሽልማቴማ ወንጌልን ስሰብክ በመብቴ ሳልጠቀም ወንጌልን ያለ ክፍያ መስበክ ነው።

19እኔ ነጻ ሰው ነኝ፤ የማንም ባሪያ አይደለሁም፤ ነገር ግን ብዙዎችን እመልስ ዘንድ ራሴን ለሰው ሁሉ ባሪያ አደርጋለሁ። 20አይሁድን እመልስ ዘንድ ከአይሁድ ጋር እንደ አይሁዳዊ ሆንሁ፤ እኔ ራሴ ከሕግ በታች ሳልሆን፣ ከሕግ በታች ያሉትን እመልስ ዘንድ ከሕግ በታች እንዳሉት ሆንሁ። 21እኔ ራሴ ከእግዚአብሔር ሕግ ነጻ ያልሆንሁና፣ ለክርስቶስ ሕግ የምገዛ ብሆንም፣ ሕግ የሌላቸውን እመልስ ዘንድ፣ ሕግ እንደሌለው ሰው ሆንሁ። 22ደካሞችን እመልስ ዘንድ፣ ከደካሞች ጋር እንደ ደካማ ሆንሁ። በሚቻለኝ ሁሉ አንዳንዶችን አድን ዘንድ፣ ከሁሉም ጋር ሁሉን ነገር ሆንሁ። 23ይህን ሁሉ የማደርገው፣ ከወንጌል በረከት እካፈል ዘንድ፣ ስለ ወንጌል ብዬ ነው።

24በሩጫ ውድድር የሚሮጡ ብዙዎች እንደ ሆኑ፣ ሽልማቱን የሚቀበለው ግን አንዱ ብቻ እንደ ሆነ አታውቁምን? ስለዚህ ሽልማቱን እንደሚቀበል ሰው ሩጡ። 25ለውድድር የሚዘጋጅ ማንኛውም ሰው በሁሉም ነገር ራሱን ይገዛል፤ እነርሱ ዐላፊ ጠፊ የሆነውን አክሊል ለማግኘት ይደክማሉ፤ እኛ ግን ለዘላለም የማይጠፋውን አክሊል ለማግኘት እንደክማለን። 26ስለዚህ እኔ ግብ እንደሌለው ሰው በከንቱ አልሮጥም፤ ደግሞም ነፋስን እንደሚጐስም ሰው እንዲያው አልታገልም፤ 27ነገር ግን ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ እኔ ራሴ ውድቅ ሆኜ እንዳልቀር፣ ሰውነቴን እየጐሰምሁ እንዲገዛልኝ አደርገዋለሁ።