1 ዮሐንስ 2 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

1 ዮሐንስ 2:1-29

1ልጆቼ ሆይ፤ ይህን የምጽፍላችሁ ኀጢአት እንዳትሠሩ ነው፤ ነገር ግን ማንም ኀጢአት ቢሠራ፣ በአብ ዘንድ ጠበቃ አለን፤ እርሱም ጻድቁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። 2እርሱም የኀጢአታችን ማስተስረያ ነው፤ ይኸውም2፥2 ኀጢአታችንን አስወግዶ የእግዚአብሔርን ቍጣ ከእኛ የሚያርቅ እርሱ ነው፤ ይኸውም የእኛን ኀጢአት ብቻ ሳይሆን ማለትም ነው። ለዓለም ሁሉ ኀጢአት እንጂ ለእኛ ብቻ አይደለም።

3ትእዛዞቹን ብንፈጽም እርሱን ማወቃችንን በዚህ ርግጠኞች እንሆናለን። 4“እርሱን ዐውቃለሁ” እያለ ትእዛዙን የማይፈጽም ግን ሐሰተኛ ነው፤ እውነትም በእርሱ ውስጥ የለም። 5ነገር ግን ማንም ቃሉን ቢጠብቅ፣ በእውነት የእግዚአብሔር ፍቅር2፥5 ወይም ለእግዚአብሔር ያለው ፍቅር ማለት ነው። በእርሱ ፍጹም ሆኗል። በእርሱ መሆናችንን የምናውቀው በዚህ ነው፤ 6ማንም በእርሱ እኖራለሁ የሚል፣ ኢየሱስ እንደ ተመላለሰ ሊመላለስ ይገባዋል።

7ወዳጆች ሆይ፤ የምጽፍላችሁ፣ ከመጀመሪያ የነበራችሁን የቈየውን ትእዛዝ እንጂ አዲስ ትእዛዝ አይደለም፤ የቈየው ትእዛዝ የሰማችሁት ቃል ነው። 8በሌላ በኩል የምጽፍላችሁ ጨለማው እያለፈና እውነተኛው ብርሃን እየበራ ስለሆነ፣ በእርሱም፣ በእናንተም ዘንድ እውነት የሆነውን አዲስ ትእዛዝ ነው።

9በብርሃን አለሁ የሚል፣ ወንድሙን ግን የሚጠላ አሁንም በጨለማ ውስጥ አለ። 10ወንድሙን የሚወድድ በብርሃን ይኖራል፤ በእርሱም ዘንድ የመሰናከያ ምክንያት የለውም። 11ነገር ግን ወንድሙን የሚጠላ በጨለማ ውስጥ ነው፤ በጨለማ ይመላለሳል፤ ጨለማው ስላሳወረውም የት እንደሚሄድ አያውቅም።

12ልጆች ሆይ፤

ኀጢአታችሁ ስለ ስሙ ተሰርዮላችኋልና፣

እጽፍላችኋለሁ።

13አባቶች ሆይ፤

ከመጀመሪያ ያለውን እርሱን ዐውቃችሁታልና፣ እጽፍላችኋለሁ።

ጐበዛዝት ሆይ፤ ክፉውን አሸንፋችኋልና፣ እጽፍላችኋለሁ።

ልጆች ሆይ፤ አብን ዐውቃችሁታልና፣ እጽፍላችኋለሁ።

14አባቶች ሆይ፤

ከመጀመሪያ ያለውን እርሱን ዐውቃችሁታልና፣

እጽፍላችኋለሁ።

ጐበዛዝት ሆይ፤

ብርቱዎች ስለ ሆናችሁ፣

የእግዚአብሔር ቃል በእናንተ ስለሚኖር፣

ክፉውንም ስላሸነፋችሁ፣

እጽፍላችኋለሁ።

ዓለምን አትውደዱ

15ዓለምን ወይም በዓለም ያለውን ማናቸውንም ነገር አትውደዱ፤ ማንም ዓለምን ቢወድድ የአብ ፍቅር በእርሱ ዘንድ የለም፤ 16ምክንያቱም በዓለም ያለው ሁሉ፦ የሥጋ ምኞት፣ የዐይን አምሮትና የኑሮ ትምክሕት ከዓለም እንጂ ከአብ የሚመጣ አይደለም። 17ዓለምና ምኞቱ ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈጽም ግን ለዘላለም ይኖራል።

ከክርስቶስ ተቃዋሚዎች መጠንቀቅ

18ልጆች ሆይ፤ ይህ የመጨረሻው ሰዓት ነው፤ እንደ ሰማችሁትም የክርስቶስ ተቃዋሚ ይመጣል፤ አሁን እንኳ ብዙ የክርስቶስ ተቃዋሚዎች መጥተዋል፤ የመጨረሻው ሰዓት እንደ ሆነ የምናውቀውም በዚህ ነው።

19ከእኛ መካከል ወጡ፤ ይሁን እንጂ ከእኛ ወገን አልነበሩም፤ ከእኛ ወገን ቢሆኑማ ኖሮ ከእኛ ጋር ጸንተው በኖሩ ነበር። ነገር ግን ሁሉም ከእኛ ወገን እንዳልነበሩ ይታወቅ ዘንድ ከእኛ ተለዩ።

20እናንተ ግን ከእርሱ፣ ከቅዱሱ ቅባት አላችሁና፣ ሁላችሁም እውነትን2፥20 አንዳንድ ቅጆች፣ እናንተ ሁሉንም ነገር ታውቃላችሁ ይላሉ። ታውቃላችሁ። 21እኔ የምጽፍላችሁ እውነትን ስለማታውቁ አይደለም፤ ነገር ግን እውነትን ስለምታውቁትና ከእውነት ምንም ውሸት ስለማይወጣ ነው። 22ክርስቶስ አይደለም ብሎ ኢየሱስን ከሚክድ በቀር ሐሰተኛ ማነው? ይህ አብንና ወልድን የሚክደው የክርስቶስ ተቃዋሚ ነው። 23ወልድን የሚክድ ሁሉ አብ የለውም፤ ወልድን የሚያምን ሁሉ አብም አለው።

24ከመጀመሪያ የሰማችሁት በእናንተ ውስጥ ይኑር፤ ከመጀመሪያ የሰማችሁት በእናንተ ውስጥ ቢኖር፣ እናንተም በወልድና በአብ ትኖራላችሁ። 25ይህ እርሱ የሰጠን ተስፋ የዘላለም ሕይወት ነው።

26ስለሚያስቷችሁ ሰዎች ይህን ጽፌላችኋለሁ። 27እናንተ ግን ከእርሱ የተቀበላችሁት ቅባት በውስጣችሁ ይኖራልና ማንም እንዲያስተምራችሁ አያስፈልግም፤ ነገር ግን እውነት እንጂ ሐሰት ያልሆነው የእርሱ ቅባት ስለ ሁሉም ነገር እንደሚያስተምራችሁ፣ ያም እውነት እንጂ ሐሰት እንዳልሆነ፣ እናንተንም እንዳስተማራችሁ በእርሱ ኑሩ።

የእግዚአብሔር ልጆች

28እንግዲህ ልጆች ሆይ፤ እርሱ ሲገለጥ ድፍረት እንዲኖረን፣ በሚመጣበትም ጊዜ በፊቱ እንዳናፍር በእርሱ ኑሩ።

29እርሱ ጻድቅ መሆኑን ካወቃችሁ፣ ጽድቅን የሚያደርግ ሁሉ ከእርሱ እንደ ተወለደ ታውቃላችሁ።