1 ዜና መዋዕል 20 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

1 ዜና መዋዕል 20:1-8

የራባ ከተማ መያዝ

20፥1-3 ተጓ ምብ – 2ሳሙ 11፥112፥29-31

1ነገሥታት ለጦርነት በሚሄዱበት በጸደይ ወራት፣ ኢዮአብ የጦር ሰራዊቱን እየመራ ሄዶ የአሞናውያንን አገር አጠፋ፤ ወደ ራባትም ሄዶ ከበባት፤ ዳዊት ግን ኢየሩሳሌም ቀርቶ ነበር። ኢዮአብም ራባትን ወግቶ አፈራረሳት። 2ዳዊት የንጉሣቸውን ዘውድ ከራሱ ላይ ወሰደ፤ ክብደቱም አንድ መክሊት20፥2 34 ኪሎ ግራም ያህል ነው ወርቅ ነበረ፤ ይህንም በዳዊት ራስ ላይ ጫኑለት፤ እንዲሁም ከከተማዪቱ እጅግ ብዙ ምርኮ ወሰደ። 3በዚያ የነበረውንም ሕዝብ አውጥቶ መጋዝ፣ ዶማና መጥረቢያ ይዘው እንዲሠሩ አደረጋቸው። ዳዊት በሌሎቹም የአሞን ከተሞች ሁሉ ይህንኑ አደረገ። ከዚያም ዳዊትና መላው ሰራዊቱ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።

ከፍልስጥኤማውያን ጋር የተደረገ ጦርነት

2፥4-8 ተጓ ምብ – 2ሳሙ 21፥15-22

4ከዚያም በኋላ ከፍልስጥኤማውያን ጋር በጌዝር ጦርነት ተደረገ፤ በዚያ ጊዜ ኩሳታዊው ሴቦካይ የራፋይም ዘር የሆነውን ሲፋይን ገደለ፤ ፍልስጥኤማውያንም ድል ተመቱ።

5ከፍልስጥኤማውያን ጋር ሌላ ጦርነት ተደረገ፤ የያዒር ልጅ ኤልያናን የጦሩ የቦ ውፍረቱ እንደ ሸማኔ መጠቅለያ የሚያህለውን የጌት ተወላጅ የሆነውን የጎልያድን ወንድም ላሕሚን ገደለ።

6ደግሞም ጌት ላይ በተደረገ ሌላ ጦርነት፣ በእጆቹና በእግሮቹ ላይ ስድስት ስድስት ጣት በድምሩ ሃያ አራት ጣት የነበሩት አንድ ግዙፍ ሰው ነበረ፤ ይህም እንደዚሁ ከራፋይም ዘር ነበረ። 7እርሱም እስራኤልን በተገዳደረ ጊዜ የዳዊት ወንድም የሳምዓ ልጅ ዮናታን ገደለው።

8በጌት የነበሩ የራፋይም ዘሮች እነዚህ ናቸው፤ እነርሱም በዳዊትና በሰዎቹ እጅ ወደቁ።