1 ዜና መዋዕል 10 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

1 ዜና መዋዕል 10:1-14

ሳኦል ራሱን ገደለ

10፥1-12 ተጓ ምብ – 1ሳሙ 31፥1-132ሳሙ 1፥4-12

1ከዚህ በኋላ ፍልስጥኤማውያን እስራኤልን መውጋት ጀመሩ፤ እስራኤላውያንም ከፊታቸው ሸሹ፤ ብዙዎች በጊልቦዓ ተራራ ላይ ሞቱ። 2ፍልስጥኤማውያን ሳኦልንና ልጆቹን ይበልጥ አሳደዷቸው፤ የሳኦልንም ልጆች ዮናታንን፣ አሚናዳብንና ሜልኪሳን ገደሉ፤ 3ሳኦል በተሰለፈበት ግንባር ውጊያው በረታ፤ ቀስተኞችም አግኝተው አቈሰሉት።

4ሳኦል ጋሻ ጃግሬውን፣ “እነዚህ ሸለፈታሞች መሳለቂያ እንዳያደርጉኝ ሰይፍህን መዝዘህ ውጋኝ” አለው።

ጋሻ ጃግሬው ግን እጅግ ፈርቶ ስለ ነበር አልደፈረም፤ ስለዚህ ሳኦል በገዛ ሰይፉ ላይ ወድቆ ሞተ። 5ጋሻ ጃግሬውም ሳኦል መሞቱን ሲያይ፣ እርሱም በሰይፉ ላይ ወድቆ ሞተ። 6ስለዚህ ሳዖልና ሦስት ልጆቹ ሞቱ፤ ቤተ ሰዎቹም ሁሉ አብረው ሞቱ።

7በሸለቆው ውስጥ የነበሩት እስራኤላውያን ሁሉ ሰራዊቱ እንደ ሸሸ፣ ሳኦልና ልጆቹም እንደ ሞቱ ባዩ ጊዜ ከተሞቻቸውን ለቅቀው ሸሹ፤ ፍልስጥኤማውያንም መጥተው ከተሞቹን ያዙ።

8በማግስቱ ፍልስጥኤማውያን የሞቱትን ለመግፈፍ ሲመጡ፣ ሳኦልና ልጆቹ በጊልቦዓ ተራራ ላይ ወድቀው አገኟቸው። 9ሳኦልን ከገፈፉ፣ ራሱን ከቈረጡና መሣሪያውንም ከወሰዱ በኋላ፣ ለአማልክቶቻቸውና ለሕዝቡ የምሥራቹን እንዲነግሩ ወደ መላው የፍልስጥኤም ምድር መልክተኞችን ላኩ። 10ከዚያም መሣሪያውን በአማልክታቸው ቤተ ጣዖት አኖሩ፤ ራሱንም በዳጎን ቤተ ጣዖት ውስጥ አንጠለጠሉት።

11የኢያቢስ ገለዓድ ነዋሪዎች ሁሉ ፍልስጥኤማውያን በሳኦል ላይ ያደረጉትን በሰሙ ጊዜ፣ 12ብርቱ የሆኑ ሰዎች ሄደው የሳኦልንና የልጆቹን ሬሳ አንሥተው ወደ ኢያቢስ አመጡ፤ ዐጽማቸውንም ኢያቢስ ውስጥ በሚገኘው ትልቁ ዛፍ ሥር ቀበሩ፤ ከዚያም ሰባት ቀን ጾሙ።

13ሳኦል እግዚአብሔርን ስላልታዘዘ ሞተ፤ የእግዚአብሔርን ቃል አልጠበቀም፤ ይልቁንም ከሙታን ጠሪ ምክርን ጠየቀ፤ 14ይህን ከእግዚአብሔር አልጠየቀም፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ገደለው፤ መንግሥቱንም ወደ እሴይ ልጅ ወደ ዳዊት እንዲተላለፍ አደረገ።