1 ነገሥት 9 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

1 ነገሥት 9:1-28

እግዚአብሔር ለሰሎሞን ዳግመኛ ተገለጠ

9፥1-9 ተጓ ምብ – 2ዜና 7፥11-22

1ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስና የራሱን ቤተ መንግሥት ሠርቶ ከጨረሰና ለመሥራት የፈለገውንም ሁሉ ካከናወነ በኋላ፣ 2እግዚአብሔር ለሰሎሞን በገባዖን ተገልጦለት እንደ ነበረ ሁሉ ዳግም ተገለጠለት። 3እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፤

“በፊቴ ያቀረብኸውን ጸሎትና ልመና ሰምቻለሁ፤ ይህን የሠራኸውንም ቤተ መቅደስ ስሜን በዚያ ለዘላለም እንዲኖር በማድረግ ቀድሼዋለሁ፤ ዐይኖቼና ልቤ ምንጊዜም በዚያ ይሆናሉ።

4“አንተም አባትህ ዳዊት እንዳደረገው፣ በልበ ቅንነትና በትክክለኛነት ብትሄድ፣ የማዝህን ሁሉ ብትፈጽም፣ ሥርዐቴንና ሕጌን ብትጠብቅ፣ 5ለአባትህ ለዳዊት፣ ‘በእስራኤል ዙፋን ላይ የሚቀመጥ ከዘርህ ሰው አታጣም’ በማለት በሰጠሁት ተስፋ መሠረት ዙፋንህን በእስራኤል ላይ ለዘላለም አጸናለሁ።

6“ነገር ግን አንተም9፥6 የዕብራይስጡ ትርጕም የብዙ ቍጥርን ያመለክታል። ሆንህ ልጆችህ እኔን ከመከተል ወደ ኋላ ብትመለሱ፣ የሰጠኋችሁን ትእዛዞችና ሥርዐቶች ሳትጠብቁ ብትቀሩ፣ ሄዳችሁም ሌሎችን አማልክት ብታመልኩና ብትሰግዱላቸው፣ 7እኔም እስራኤልን ከሰጠኋቸው ምድር እነቅላቸዋለሁ፤ ስለ ስሜ የቀደስሁትን ይህን ቤተ መቅደስም እተወዋለሁ፤ ከዚያም እስራኤል በሕዝቦች ሁሉ ዘንድ መተረቻና መዘባበቻ ይሆናሉ፤ 8ይህ ቤተ መቅደስ አሁን የሚያስገርም ቢሆንም እንኳ፣ የፍርስራሽ ክምር ይሆናል፤ ዐላፊ አግዳሚውም ሁሉ ይገረማል፤ እያፌዘም፣ ‘እግዚአብሔር በዚህች ምድርና በዚህ ቤተ መቅደስ ላይ እንዲህ ያለውን ነገር ያደረገው ስለ ምን ይሆን?’ ይላል፤ 9ራሱ መልሶም፣ ‘አዎን እግዚአብሔር ይህን ሁሉ ጥፋት ያመጣባቸው አባቶቻቸውን ከግብፅ ምድር ያወጣውን አምላካቸውን እግዚአብሔርን ትተው ሌሎች አማልክትን በመከተል ስለ ሰገዱላቸውና ስላመለኳቸው ነው’ ይላል።”

ሰሎሞን ያከናወናቸው ሌሎች ሥራዎች

9፥10-28 ተጓ ምብ – 2ዜና 8፥1-18

10ሰሎሞን ሁለቱን ሕንጻዎች፣ ማለትም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስና የንጉሡን ቤተ መንግሥት ሠርቶ በፈጸመ በሃያኛው ዓመት መጨረሻ፣ 11ንጉሥ ሰሎሞን በገሊላ የሚገኙትን ሃያ ከተሞች ለጢሮስ ንጉሥ ለኪራም ሰጠው፤ ንጉሡ ይህን ያደረገውም፣ የሚያስፈልገውን ሁሉ ዝግባ፣ ጥድና ወርቅ ኪራም ሰጥቶት ስለ ነበር ነው፤ 12ይሁን እንጂ ኪራም ከጢሮስ ተነሥቶ ሰሎሞን የሰጠውን ከተሞች ለማየት በሄደ ጊዜ አልተደሰተባቸውም፤ 13እርሱም፣ “ወንድሜ ሆይ፤ እነዚህ የሰጠኸኝ ከተሞች ምንድን ናቸው?” አለ፤ እነዚህንም “ከቡል9፥13 ከቡል የሚለው የዕብራይስጥ ቃል፣ የመልካም ነገር ተምሳሌት ከሚለው የዕብራይስጥ ቃል ጋር ተመሳሳይ የሆነ ድምፅ አለው። ምድር” አላቸው፤ እስከ ዛሬም በዚሁ ስም ይጠራሉ። 14በዚያን ጊዜ ኪራም ለንጉሡ መቶ ሃያ መክሊት9፥14 4 ሜትሪክ ቶን ያህል ነው። ወርቅ ልኮለት ነበር።

15ንጉሥ ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ፣ የራሱን ቤተ መንግሥት፣ ሚሎን፣ የኢየሩሳሌምን ቅጥር፣ ሐጾርን፣ መጊዶንና ጌዝርን ለመሥራት የጕልበት ሠራተኞች መልምሎ ነበር። 16የግብፅ ንጉሥ ፈርዖን ወጥቶ በጌዝር ላይ አደጋ ጥሎ ያዛት፤ አቃጠላትም፤ ነዋሪዎቿን ከነዓናውያንን ገድሎ ለልጁ ለሰሎሞን ሚስት መዳሪያ አድርጎ ሰጥቷት ነበር፤ 17ሰሎሞንም ጌዝርን መልሶ ሠራት፤ እንዲሁም የታችኛውን ቤትሖሮንን፣ 18ባዕላትን፣ በይሁዳ ምድር በምድረ በዳው የምትገኘውን ተድሞርን9፥18 በዕብራይስጥ ታማር ተብሎ ይነበባል። ሠራ፤ 19ደግሞም ማናቸውንም በኢየሩሳሌም፣ በሊባኖስና በሌሎች ግዛቶቹ ሁሉ ለመሥራት የፈለገውን፣ ሥንቅ የሚከማችባቸውን፣ ሠረገሎች9፥19 ወይም ሠረገለኞች ተብሎ መተርጐም ይችላል። የሚጠበቁባቸውን እንዲሁም ፈረሰኞች የሚቀመጡባቸውን ከተሞችና መንደሮች ሁሉ ሠራ።

20ከእስራኤል ሕዝብ ያልሆኑትን ከአሞራውያን፣ ከኬጢያውያን፣ ከፌርዛውያን፣ ከኤውያውንና ከኢያቡሳውያን ሕዝቦች ሁሉ የተረፉትን፣ 21እስራኤላውያን ዘሮቻቸውን ለማጥፋት9፥21 የዕብራይስጡ ቃል ሰውን ወይም ቍስን ፈጽሞ በማጥፋት ለእግዚአብሔር መስጠት የሚለውን ያመለክታል። ያልቻሉትንና በምድሪቱ የቀሩትን እነዚህን እስከ ዛሬ እንደሚደረገው ሁሉ፣ ሰሎሞን ለግዳጅ ሥራ መለመላቸው። 22ይሁን እንጂ ሰሎሞን ከእስራኤላውያን ማንንም ባሪያ አላደረገም፤ እነርሱ ወታደሮቹ፣ ሹማምቱ፣ የጦር አለቆቹ፣ ሻምበሎቹ፣ ባልደራሶቹ ነበሩ። 23እነዚህም ሰሎሞን የሚያሠራውን የሕንጻ ሥራ የሚያከናውኑትን ሠራተኞች የሚቈጣጠሩ ናቸው፤ ቍጥራቸውም አምስት መቶ አምሳ ነበር።

24የፈርዖን ልጅ ከዳዊት ከተማ ሰሎሞን ወዳሠራላት ቤተ መንግሥት ከመጣች በኋላ ሰሎሞን ሚሎንን ሠራ።

25ሰሎሞንም ለእግዚአብሔር ባሠራው መሠዊያ ላይ በዓመት ሦስት ጊዜ የሚቃጠል መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕት9፥25 በትውፊት የሰላም መሥዋዕት ይባላል። በማቅረብ፣ ከዚሁ ጋር በእግዚአብሔር ፊት ዕጣን ያሳርግ ነበር፤ በዚህ ሁኔታም የቤተ መቅደሱን ግዳጅ ተወጣ።

26እንዲሁም ንጉሡ ሰሎሞን በኤዶምያስ ምድር፣ በኤሎት አጠገብ፣ በቀይ ባሕር9፥26 የዕብራይስጡ ያም ስውፍ ይለዋል፤ ይኸውም የደንገል ባሕር ማለት ነው ዳርቻ ላይ ባለችው በዔጽዮንጋብር መርከቦችን ሠራ። 27በመርከቦቹም ላይ ከሰሎሞን ሰዎች ጋር አብረው እንዲሠሩ፣ ኪራም ባሕሩን የሚያውቁ የራሱን መርከበኞች ላከ። 28እነዚያም ወደ ኦፊር ሄደው አራት መቶ ሃያ መክሊት9፥28 14.5 ሜትሪክ ቶን ያህል ነው። ወርቅ ይዘው ተመለሱ፤ ይህንም ለንጉሥ ሰሎሞን ሰጡት።