1 ነገሥት 5 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

1 ነገሥት 5:1-18

ቤተ መቅደሱን ለመሥራት የተደረገ ዝግጅት

5፥1-16 ተጓ ምብ – 2ዜና 2፥1-18

1የጢሮስ ንጉሥ ኪራም በዘመኑ ሁሉ ለዳዊት ወዳጅ ስለ ነበር፣ ሰሎሞን በአባቱ እግር ለመተካት መቀባቱን በሰማ ጊዜ፣ መልእክተኞቹን ወደ ሰሎሞን ላከ። 2ሰሎሞንም እንዲህ የሚል መልእክት ወደ ኪራም መልሶ ላከ፤

3“አባቴ ዳዊት በዙሪያው ሁሉ ከገጠመው ጦርነት የተነሣ፣ እግዚአብሔር ጠላቶቹን ከእግሩ በታች እስኪጥልለት ድረስ ለአምላኩ ለእግዚአብሔር ስም ቤተ መቅደስ መሥራት እንዳልቻለ ታውቃለህ። 4አሁን ግን አምላኬ እግዚአብሔር በዙሪያዬ ሁሉ ሰላም ሰጥቶኛል፤ ጠላትም የለብኝም። 5እነሆ፣ እግዚአብሔር ለአባቴ ለዳዊት፣ ‘ለስሜ ቤተ መቅደስ የሚሠራልኝ ከአንተ ቀጥሎ በዙፋንህ የማስቀምጠው ልጅህ ነው’ ብሎ እንደ ነገረው፣ ለአምላኬ ለእግዚአብሔር ስም ቤተ መቅደስ ለመሥራት ዐስቤአለሁ።

6“ስለዚህ የሊባኖስ ዝግባ እንዲቈረጥልኝ ትእዛዝ ስጥ፤ ሰዎቼ ከሰዎችህ ጋር አብረው ይሠራሉ፤ የሰዎችህንም ደመወዝ አንተ በወሰንኸው እከፍልሃለሁ፤ ከሰዎቼ መካከል እንደ ሲዶናውያን ዕንጨት በመቍረጥ እስከዚህ የሠለጠነ ሰው አለመኖሩን ራስህም ታውቃለህና።”

7ኪራም የሰሎሞን መልእክት በደረሰው ጊዜ እጅግ ደስ ስላለው፣ “ይህን ታላቅ ሕዝብ እንዲመራ ለዳዊት ጥበበኛ ልጅ ሰጥቶታልና ዛሬ ምስጋና ለእግዚአብሔር ይግባው” አለ።

8ስለዚህ ኪራም፣ ለሰሎሞን እንዲህ ሲል ላከበት፤

“የላክኸው መልእክት ደርሶኛል፤ የዝግባውንና የጥዱን ግንድ በማቅረብ ረገድ የምትፈልገውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ፤ 9ሰዎቼ ግንዱን ከሊባኖስ እስከ ባሕሩ ድረስ ጐትተው ያወርዳሉ፤ እኔም ግንዱ ሁሉ ታስሮ አንተ እስከ ወሰንኸው ስፍራ በባሕር ተንሳፍፎ እንዲደርስ አደርጋለሁ፤ እዚያም እኔ እፈታዋለሁ፤ አንተም ትወስደዋለህ፤ አንተም ለቤተ ሰቤ ቀለብ በመስጠት ፍላጎቴን ታሟላለህ።”

10በዚህ ሁኔታ ኪራም ለሰሎሞን የሚያስፈልገውን የዝግባና የጥድ ግንድ በሙሉ ያቀርብለት ጀመር፤ 11ሰሎሞን ደግሞ ለኪራም ቤተ ሰው ቀለብ እንዲሆን ሃያ ሺሕ የቆሮስ መስፈሪያ5፥11 4400000 ኪሎ ሊትር ያህል ነው። ስንዴ፣ ሃያ ሺሕ ኮር5፥11 ዕብራይስጡና የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም ሃያ ኮር ይላሉ (2ዜና 2፥10 ይመ) ንጹሕ5፥11 440 ኪሎ ሊትር ያህል ነው። የወይራ ዘይት ሰጠው፤ ይህን ባለማቋረጥ በየዓመቱ ለኪራም ይሰጥ ነበር። 12እግዚአብሔርም በገባለት ተስፋ መሠረት ለሰሎሞን ጥበብን ሰጠው፤ በኪራምና በሰሎሞን መካከልም መልካም ግንኙነት ነበር፤ ሁለቱም ቃል ኪዳን አደረጉ።

13ንጉሥ ሰሎሞን ከመላው እስራኤል የጕልበት ሠራተኞችን መለመለ፤ ቍጥራቸውም ሠላሳ ሺሕ ነበር። 14እነዚህንም አንድ ወር በሊባኖስ እንዲሠሩ፣ ሁለት ወር በቤታቸው እንዲያርፉ በማድረግ፣ ዐሥር ዐሥር ሺዉን ወር ተራ አግብቶ ላካቸው። የጕልበት ሠራተኞቹም አለቃ አዶኒራም ነበር። 15ሰሎሞንም በኰረብታማው አገር ሰባ ሺሕ ተሸካሚዎችና ሰማንያ ሺሕ ድንጋይ ጠራቢዎች ነበሩት፤ 16እንዲሁም ሥራውን የሚቈጣጠሩ ሦስት ሺሕ ሦስት መቶ5፥16 ዕብራይስጡና አንዳንድ የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም ሦስት ሺሕ ስድስት መቶ ይላሉ። ኀላፊዎች ነበሩ። 17እነርሱም በንጉሡ ትእዛዝ ለቤተ መቅደሱ መሠረት የሚሆን ታላላቅና ምርጥ ድንጋይ ፈልፍለው በማውጣት የተጠረበ ድንጋይ አዘጋጁ። 18የሰሎሞንና የኪራም የእጅ ባለሙያዎች እንዲሁም የጌባል ሰዎች5፥18 ይኸውም ቢብሎስ ነው። ለቤተ መቅደሱ የሚያስፈልገውን ዕንጨትና ድንጋይ ፈልጠው አዘጋጁ።