1 ነገሥት 2 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

1 ነገሥት 2:1-46

ዳዊት ለሰሎሞን የሰጠው መመሪያ

2፥10-12 ተጓ ምብ – 1ዜና 29፥26-28

1ዳዊት የሚሞትበት ጊዜ እንደ ተቃረበም፣ ልጁን ሰሎሞንን እንዲህ ሲል አዘዘው፤

2“እነሆ፤ እኔ የምድሩን ሁሉ መንገድ ልሄድ ነው፤ እንግዲህ በርታ፤ ሰውም ሁን። 3የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ጠብቅ፤ የምታደርገው ሁሉ እንዲከናወንልህ፣ በምትሄድበትም ሁሉ እንዲሳካልህ፣ በሙሴ ሕግ እንደ ተጻፈው በመንገዶቹ ተመላለስ፣ ሥርዐቶቹንና ትእዛዞቹን፣ ሕግጋቱንና ደንቦቹን ጠብቅ፤ 4እግዚአብሔርም፣ ‘ዘሮችህ መንገዳቸውን ቢጠብቁ፣ እንዲሁም በፍጹም ልባቸው፣ በፍጹም ነፍሳቸው በታማኝነት በፊቴ ቢመላለሱ፣ በእስራኤል ዙፋን የሚቀመጥ ሰው ከዘርህ አላሳጣህም’ ሲል የሰጠኝን ተስፋ ይፈጽምልኛል።

5“የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ በእኔ ላይ ያደረገውን፣ እንዲሁም በእስራኤል ሰራዊት አዛዦች በኔር ልጅ በአበኔርና በዬቴሩ ልጅ በአሜሳይ ላይ የፈጸመውን አንተው ራስህ ታውቃለህ፤ ጦርነት ሳይኖር በሰላሙ ጊዜ ደማቸውን አፍስሷል፤ በዚህም ደም ወገቡ ላይ የታጠቀውን ቀበቶና በእግሩ ላይ ያደረገውን ጫማ በክሏል። 6መደረግ ያለበትን በጥበብህ አድርግ፤ ከነሽበቱ በሰላም ወደ መቃብር2፥6 በዚህ ስፍራና በቍጥር 9 ላይ ዕብራይስጡ ሲኦል ይላል። እንዲወርድ አታድርግ።

7“ከወንድምህ ከአቤሴሎም በሸሸሁ ጊዜ መልካም ነገር አድርገውልኛልና ለገለዓዳዊው ለቤርዜሊ ልጆች ግን በጎ ነገር አድርግላቸው፤ ማእድህን ከሚካፈሉ ሰዎችም ጋር አብረው ይብሉ።

8“ወደ መሃናይም በሄድሁ ጊዜ፣ ክፉኛ የረገመኝ የባሑሪም ሰው የብንያማዊው የጌራ ልጅ ሳሚ እነሆ፤ ከአንተ ዘንድ ይገኛል፤ ሊቀበለኝ ወደ ዮርዳኖስ ሲወርድ፣ ‘በሰይፍ አልገድልህም’ ብዬ በእግዚአብሔር ስም ምዬለታለሁ፤ 9አሁን ግን በደል እንደሌለበት ሰው አትተወው፤ ጥበበኛ ነህና መደረግ ያለበትን ታውቃለህ፤ ሽበቱን በደም ወደ መቃብር አውርድ።”

10ከዚያም ዳዊት ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ ተቀበረ። 11ዳዊት በኬብሮን ሰባት ዓመት፣ በኢየሩሳሌም ሠላሳ ሦስት ዓመት በአጠቃላይ አርባ ዓመት በእስራኤል ላይ ነገሠ። 12ስለዚህ ሰሎሞን በአባቱ በዳዊት ዙፋን ተቀመጠ፤ መንግሥቱም እጅግ የጸና ሆነ።

የሰሎሞን መንግሥት መጽናት

13በዚህ ጊዜ የአጊት ልጅ አዶንያስ ወደ ሰሎሞን እናት ወደ ቤርሳቤህ ሄደ። ቤርሳቤህም፣ “የመጣኸው በሰላም ነውን?” ስትል ጠየቀችው፤

እርሱም፣ “አዎን በሰላም ነው” ብሎ መለሰ። 14ከዚያም፣ “የምነግርሽ ጕዳይ አለኝ” አላት።

እርሷም፣ “እሺ ተናገር” ብላ መለሰች።

15እርሱም፣ “መንግሥቱ የእኔ እንደ ነበረና እስራኤልም ሁሉ እኔ እንድነግሥ ዐይናቸውን ጥለውብኝ እንደ ነበር አንቺ ራስሽ ታውቂአለሽ፤ ሆኖም ነገሩ ከእግዚአብሔር የተቈረጠለት ሆነና ሁኔታዎች ተለዋውጠው፣ መንግሥቱ ለወንድሜ ተላለፈ። 16አሁንም አንዲት ነገር እለምንሻለሁ፤ አታሳፍሪኝ” አላት።

እርሷም፣ “በል እሺ ተናገር” አለችው።

17እርሱም፣ “ንጉሥ ሰሎሞን መቼም እንቢ አይልሽምና ሱነማዊቷን አቢሳን እንዲድርልኝ ለምኚልኝ” አላት።

18ቤርሳቤህም፣ “መልካም ነው፤ ይህንኑ ለንጉሡ እነግርልሃለሁ” ብላ መለሰች።

19ስለዚህም ቤርሳቤህ የአዶንያስን ጕዳይ ልትነግረው ወደ ንጉሥ ሰሎሞን ሄደች፤ ንጉሡም ሊቀበላት ተነሣ፤ እጅ ከነሣትም በኋላ በዙፋኑ ላይ ተቀመጠ፤ ንጉሡም ለእናቱ ሌላ ዙፋን አስመጥቶ በቀኙ አስቀመጣት።

20እርሷም፣ “የምለምንህ አንዲት ነገር አለችኝና እባክህ እሺ በለኝ” አለችው።

ንጉሡም፣ “እናቴ ሆይ፤ አላሳፍርሽምና ንገሪኝ” ሲል መለሰላት።

21ስለዚህም፣ “ሱነማዊቷን አቢሳን ወንድምህ አዶንያስ ቢያገባትስ?” አለችው።

22ንጉሥ ሰሎሞንም እናቱን፣ “ስለ ምን ሱነማዊቷን አቢሳን ብቻ ለአዶንያስ ትጠይቂለታለሽ? ታላቅ ወንድሜ ስለሆነ መንግሥቱንም ጠይቂለት እንጂ፤ ለእርሱ ብቻ ሳይሆን እንዲሁም ለካህኑ ለአብያታርና ለጽሩያ ልጅ ለኢዮአብ ጠይቂላቸው” አላት።

23ከዚያም ንጉሥ ሰሎሞን በእግዚአብሔር ስም እንዲህ ሲል ማለ፤ “አዶንያስ ይህን ስለ ጠየቀ በሞት ሳይቀጣ ቢቀር፣ እግዚአብሔር ይፍረድብኝ፤ ከዚህ የባሰም ያምጣብኝ፤ 24አሁንም በሚገባ ያጸናኝ፤ በአባቴ በዳዊት ዙፋን ያስቀመጠኝና በሰጠውም ተስፋ መሠረት ሥርወ መንግሥትን የመሠረተልኝ ሕያው እግዚአብሔርን አዶንያስ ዛሬ ይሞታል!” 25ስለዚህም አዶንያስን እንዲገድለው ንጉሥ ሰሎሞን፣ የዮዳሄን ልጅ በናያስን አዘዘው፤ በናያስም አዶንያስን መትቶ ገደለው።

26ንጉሡም ካህኑን አብያታርን፣ “ሞት የሚገባህ ሰው ነበርህ፤ ነገር ግን የጌታ እግዚአብሔርን ታቦት በአባቴ በዳዊት ፊት ስለ ተሸከምህ፣ አባቴ የተቀበለውንም መከራ ሁሉ አብረኸው ስለ ተቀበልህ፣ እኔ አሁን አልገድልህም፤ ዓናቶት ወዳለው ዕርሻህ ሂድ” አለው። 27ስለዚህ እግዚአብሔር ስለ ዔሊ ቤት በሴሎ የተናገረውን ቃል ለመፈጸም፣ ሰሎሞን አብያታርን ከእግዚአብሔር ክህነት አስወገደው።

28ከአቤሴሎም ጋር ሳይሆን ከአዶንያስ ጋር አሢሮ የነበረው ኢዮአብም ይህን በሰማ ጊዜ፣ ወደ እግዚአብሔር ድንኳን ሸሽቶ የመሠዊያውን ቀንድ ያዘ። 29ኢዮአብ ወደ እግዚአብሔር ድንኳን ሸሽቶ መሄዱንና በመሠዊያው አጠገብ መሆኑን ንጉሥ ሰሎሞን በሰማ ጊዜ፣ የዮዳሄን ልጅ በናያስን፣ “ሂድና ግደለው!” ብሎ አዘዘው።

30ስለዚህም በናያስ ወደ እግዚአብሔር ድንኳን ገብቶ ኢዮአብን፣ “ንጉሡ፣ ‘ከዚህ ውጣ’ ይልሃል” አለው።

እርሱ ግን “አልወጣም፣ እዚሁ እሞታለሁ” አለው።

በናያስም፣ “ኢዮአብ የሰጠኝ መልስ ይህ ነው” በማለት ለንጉሡ ተናገረ።

31ንጉሡም በናያስን እንዲህ ሲል አዘዘው፤ “በል እንዳለው አድርግ፤ ግደልና ቅበረው፤ ኢዮአብ በከንቱ ካፈሰሰው ንጹሕ ደምም እኔንና የአባቴን ቤት አንጻን። 32አባቴ ዳዊት ሳያውቅ ኢዮአብ በሁለቱ ሰዎች ላይ አደጋ ጥሎ በሰይፍ ገድሏቸዋልና ስላፈሰሰው ደም እግዚአብሔር ይበቀለዋል። የእስራኤል ሰራዊት አዛዥ የኔር ልጅ አበኔርና የይሁዳ ሰራዊት አዛዥ የዬቴሩ ልጅ አሜሳይ ሁለቱም ከእርሱ የተሻሉና ይበልጥ ትክክለኛ ሰዎች ነበሩ። 33የደማቸውም ዕዳ ለዘላለም በኢዮአብና በዘሩ ራስ ላይ ይሁን። ነገር ግን በዳዊትና በዘሩ፣ በቤቱና በዙፋኑ ላይ የእግዚአብሔር ሰላም ለዘላለም ጸንቶ ይኑር።”

34ስለዚህም የዮዳሄ ልጅ በናያስ ወጣ፤ ኢዮአብንም መትቶ ገደለው፤ እርሱም በምድረ በዳ ባለው በገዛ ምድሩ2፥34 ወይም በገዛ መቃብሩ ተብሎ ሊተረጐም ይችላል። ተቀበረ። 35ንጉሡም በኢዮአብ ቦታ የዮዳሄን ልጅ በናያስን በሰራዊቱ ላይ ሾመ፤ በአብያታርም ቦታ ካህኑን ሳዶቅን ተካ።

36ከዚያም ንጉሡ ሳሚን አስጠርቶ እንዲህ አለው፤ “በኢየሩሳሌም ቤት ሠርተህ እዚያው ተቀመጥ፤ ከዚያ ግን የትም እንዳትሄድ፤ 37ነገር ግን ከዚያ ወጥተህ የቄድሮንን ሸለቆ ከተሻገርህ እንደምትሞት ዕወቅ፤ ደምህም በራስህ ላይ ይሆናል።”

38ሳሚም መልሶ ንጉሡን፣ “መልካም፤ ባሪያህ ጌታዬ ንጉሡ ያለውን ይፈጽማል” አለው፤ እርሱም በኢየሩሳሌም ብዙ ጊዜ ተቀመጠ።

39ከሦስት ዓመት በኋላ ግን፣ ከሳሚ አገልጋዮች ሁለቱ ወደ ጌት ንጉሥ፣ ወደ መዓካ ልጅ ወደ አንኩስ ኰበለሉ፤ ለሳሚም፣ “እነሆ፣ አገልጋዮችህ በጌት ናቸው” ተብሎ ተነገረው። 40ሳሚ ይህን ሲሰማም አህዮቹን ጭኖ አገልጋዮቹን ለመፈለግ ጌት ወዳለው ወደ አንኩስ ሄደ፤ አገልጋዮቹንም ከጌት መልሶ አመጣቸው።

41ሳሚ ከኢየሩሳሌም ወደ ጌት ሄዶ መመለሱን ሰሎሞን በሰማ ጊዜ፣ 42ንጉሡ ሳሚን አስጠርቶ እንዲህ አለው፤ “ ‘ወደ ሌላ ቦታ የሄድህ ዕለት እንደምትሞት ዕወቅ’ ብዬ በእግዚአብሔር ስም አስምዬ አስጠንቅቄህ አልነበረምን? በዚያን ጊዜ አንተም፣ ‘መልካም ነው፤ እኔም እታዘዛለሁ’ ብለኸኝ ነበር፤ 43ታዲያ ለእግዚአብሔር የማልኸውን መሐላ ያልጠበቅኸውና እኔም የሰጠሁህን ትእዛዝ ያልፈጸምኸው ለምንድን ነው?”

44ንጉሡም መልሶ ሳሚን እንዲህ አለው፤ “በአባቴ በዳዊት ላይ ያደረግህበትን ክፉ ነገር ሁሉ ልብህ ያውቀዋል፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ስለ ክፉ ሥራህ ብድሩን ይከፍልሃል። 45ንጉሥ ሰሎሞን ግን ይባረካል፤ የዳዊትም ዙፋን በእግዚአብሔር ፊት ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።” 46ከዚያም ንጉሡ የዮዳሄን ልጅ በናያስን አዘዘው፤ በናያስም ወጣ፤ ሳሚንም መትቶ ገደለው።

በዚህ ጊዜም መንግሥቱ በሰሎሞን እጅ ጸና።