1 ቆሮንቶስ 7 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

1 ቆሮንቶስ 7:1-40

ጋብቻን በተመለከተ

1ስለ ጻፋችሁልኝ ጕዳይ፣ ሰው ወደ ሴት ባይደርስ መልካም ነው7፥1 ወይም ሰው ከሴት ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት ባያደርግ መልካም ነው2ነገር ግን ከዝሙት ለመጠበቅ፣ እያንዳንዱ ሰው የራሱ ሚስት ትኑረው፤ እያንዳንዷም ሴት የራሷ ባል ይኑራት። 3ባል ለሚስቱ የሚገባትን ሁሉ ያድርግላት፤ ሚስትም እንዲሁ ለባሏ የሚገባውን ሁሉ ታድርግለት። 4ሚስት አካሏ የራሷ አይደለም፤ የባሏ ነው፤ እንዲሁም ባል አካሉ የራሱ አይደለም፣ የሚስቱ ነው። 5በጸሎት ለመትጋት ተስማምታችሁ ለተወሰነ ጊዜ ካልሆነ በስተቀር፣ እርስ በርሳችሁ አትከላከሉ፤ ራሳችሁን ባለመግዛት ሰይጣን እንዳይፈታተናችሁ እንደ ገና አብራችሁ ሁኑ። 6ይህን የምለው ግን እንደ ትእዛዝ ሳይሆን እንደ ምክር ነው። 7ሰው ሁሉ እንደ እኔ ቢሆን ምኞቴ ነው። ነገር ግን እያንዳንዱ ሰው ከእግዚአብሔር የተቀበለው የራሱ የሆነ ስጦታ አለው፤ አንዱ አንድ ዐይነት ስጦታ ሲኖረው፣ ሌላው ደግሞ ሌላ ዐይነት ስጦታ አለው።

8ላላገቡና ባሎቻቸው ለሞቱባቸው ሴቶች ግን እንዲህ እላለሁ፤ ሳያገቡ እንደ እኔ ቢኖሩ ለእነርሱ መልካም ነው። 9ነገር ግን ራሳቸውን መግዛት ካልቻሉ ያግቡ፤ በምኞት ከመቃጠል ማግባት ይሻላልና።

10ላገቡት ይህን ትእዛዝ እሰጣለሁ፤ ይህም ትእዛዝ የጌታ እንጂ የእኔ አይደለም። ሚስት ከባሏ አትለያይ፤ 11ብትለያይ ግን ሳታገባ ትኑር፤ አለዚያ ከባሏ ጋር ትታረቅ፤ ባልም ሚስቱን አይፍታት።

12ለሌሎች ደግሞ እንዲህ እላለሁ፤ ይህንም የምለው እኔ እንጂ ጌታ አይደለም። ያላመነች ሚስት ያለው ወንድም ቢኖርና ሚስቱ አብራው ለመኖር የምትፈቅድ ከሆነ፣ ሊፈታት አይገባውም። 13ያላመነ ባል ያላት ሴት ብትኖርና እርሱም አብሯት ለመኖር የሚፈቅድ ከሆነ፣ ልትፈታው አይገባትም። 14ያላመነ ባል በሚስቱ ተቀድሷልና፤ ያላመነችም ሚስት በሚያምን ባሏ ተቀድሳለች፤ አለዚያማ ልጆቻችሁ ርኩሳን በሆኑ ነበር፤ አሁን ግን የተቀደሱ ናቸው።

15ነገር ግን የማያምነው ወገን መለየት ከፈለገ ይለይ፤ አንድ ወንድም ወይም እኅት በዚህ ሁኔታ የታሰሩ አይደሉም፤ እግዚአብሔር የጠራን በሰላም እንድንኖር ነው። 16አንቺ ሴት፤ ባልሽን ታድኚው እንደ ሆነ ምን ታውቂያለሽ? ወይስ አንተ ሰው፤ ሚስትህን ታድናት እንደ ሆነ ምን ታውቃለህ?

17ብቻ እያንዳንዱ ሰው ጌታ እንደ ወሰነለት፣ እያንዳንዱም እግዚአብሔር እንደ ጠራው በዚያው ይመላለስ። በአብያተ ክርስቲያናትም ሁሉ የምንደነግገው ይህንኑ ነው። 18አንድ ሰው ተገርዞ ሳለ ቢጠራ፣ እንዳልተገረዘ ሰው አይሁን፤ ሳይገረዝም ተጠርቶ ከሆነ አይገረዝ። 19መገረዝም ሆነ አለመገረዝ አይጠቅምም፤ ዋናው ነገር የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መፈጸሙ ነው። 20እያንዳንዱ ሰው በተጠራበት ሁኔታ ጸንቶ ይኑር። 21በተጠራህ ጊዜ ባሪያ ነበርህን? በዚህ አትጨነቅ፤ ነጻነትህን ማግኘት ከቻልህ ግን ነጻነትህን ተቀበል። 22ምክንያቱም ባሪያ ሆኖ ሳለ በጌታ የተጠራ፣ የጌታ ነጻ ሰው ነው፤ እንዲሁም ሲጠራ ነጻ የነበረ ሰው የክርስቶስ ባሪያ ነው። 23በዋጋ ተገዝታችኋል፤ ስለዚህ የሰው ባሪያዎች አትሁኑ። 24ወንድሞች ሆይ፤ እያንዳንዱ ሰው በተጠራበት ሁኔታ ከእግዚአብሔር ጋር ጸንቶ ይኑር።

25ስለ ደናግል፣ ከጌታ የተቀበልሁት ትእዛዝ የለኝም፤ ይሁን እንጂ፣ ከጌታ ምሕረት የተነሣ እንደ ታማኝ ሰው፣ ምክሬን እሰጣለሁ። 26አሁን ካለው ችግር የተነሣ ባላችሁበት ሁኔታ ብትኖሩ መልካም ይመስለኛል። 27አግብተህ ከሆነ መፋታትን አትሻ፤ ካላገባህም ሚስት ለማግባት አትፈልግ። 28ብታገባ ግን ኀጢአት አልሠራህም፤ ድንግሊቱም ብታገባ ኀጢአት አላደረገችም። ነገር ግን የሚያገቡ ሰዎች በዚህ ዓለም ብዙ ችግር ይገጥማቸዋል፤ እኔም ይህ እንዳይደርስባችሁ እወድዳለሁ።

29ወንድሞች ሆይ፤ ሐሳቤ እንዲህ ነው፤ ዘመኑ ዐጭር ነው፤ ከእንግዲህ ሚስት ያላቸው እንደሌላቸው ሆነው ይኑሩ። 30የሚያለቅሱ እንደማያለቅሱ፣ ደስተኞች ደስ እንደማይላቸው ይሁኑ፤ ዕቃ የሚገዙም የገዙት ነገር የእነርሱ እንዳልሆነ ይቍጠሩ፤ 31በዚህ ዓለም ነገር የሚጠቀሙም እንደማይጠቀሙበት ይሁኑ፤ የዚህ ዓለም መልክ ዐላፊ ነውና።

32እኔስ ያለ ጭንቀት እንድትኖሩ እወድዳለሁ። ያላገባ ሰው ጌታን ደስ ለማሰኘት ስለ ጌታ ነገር ያስባል፤ 33ያገባ ሰው ግን ሚስቱን ደስ ለማሰኘት የዚህን ዓለም ነገር ያስባል፤ 34በዚህም ልቡ ተከፍሏል። ያላገባች ሴት ወይም ድንግል ስለ ጌታ ነገር ታስባለች፤ ዐላማዋም በሥጋና በመንፈስ ለጌታ መቀደስ ነው። ያገባች ሴት ግን ባሏን ደስ ለማሰኘት የዚህን ዓለም ነገር ታስባለች። 35ይህንም የምለው ለእናንተ የሚበጃችሁን ነገር በማሰብ እንጂ ላስጨንቃችሁ አይደለም፤ ዐላማዬም ልባችሁ ሳይከፈል በጌታ ጸንታችሁ በአግባብ እንድትኖሩ ነው።

36አንድ ሰው ያጫትን ድንግል በአግባቡ ካልያዘ፣ እርሷም በዕድሜ እየገፋች ከሄደች፣ ሊያገባት ካሰበ የወደደውን ያድርግ፤ ኀጢአት የለበትምና ይጋቡ። 37ነገር ግን በዚህ ጕዳይ ልቡን አረጋግቶ፣ ሳይናወጥ፣ ራሱንም በመግዛት ድንግሊቱን ላለማግባት የወሰነ ሰው መልካም አድርጓል። 38ስለዚህ ድንግሊቱን ያገባ መልካም አደረገ፤ ያላገባም የተሻለ አደረገ7፥36-38 ወይም አንድ ሰው ድንግል የሆነችውን ልጁን በሚገባ እንዳልያዛት ካሰበና እርሷም በዕድሜ እየገፋች ከሄደች፣ ማግባት እንዳለባት ካሰበ የወደደውን ያድርግ፤ ኀጢአት የለበትምና እንድታገባ ሊፈቅድላት ይገባል 38 ስለዚህ ድንግል የሆነችውን ልጁን ለጋብቻ የሰጠ መልካም አደረገ፤ ለጋብቻ ያልሰጣትም የተሻለ አደረገ

39አንዲት ሴት ባሏ በሕይወት እስካለ ድረስ ከእርሱ ጋር የታሰረች ናት፤ ባሏ ቢሞት ግን፣ የፈለገችውን ሰው ለማግባት ነጻነት አላት፤ ሰውየው ግን በጌታ መሆን አለበት። 40እንደ እኔ ከሆነ ግን ሳታገባ እንዲሁ ብትኖር ይበልጥ ደስተኛ ትሆናለች፤ እኔም ደግሞ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ያለ ይመስለኛል።