1በእግዚአብሔር ፈቃድ የክርስቶስ ኢየሱስ ሐዋርያ እንዲሆን ከተጠራው ከጳውሎስ፣ ከወንድማችንም ከሶስቴንስ፤
2በቆሮንቶስ ላለችው የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን፤ በክርስቶስ ኢየሱስ ተቀድሰው፣ የእነርሱና የእኛ ጌታ የሆነውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በየስፍራው ሆነው ከሚጠሩት ሁሉ ጋር ቅዱሳን ለመሆን ለተጠሩት፤
3ከእግዚአብሔር ከአባታችን፣ ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።
ምስጋና
4በክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ተሰጣችሁ ጸጋ ዘወትር ስለ እናንተ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። 5ምክንያቱም በማናቸውም ነገር ይኸውም በንግግር ሁሉ፣ በዕውቀትም ሁሉ በእርሱ በልጽጋችኋል፤ 6ስለ ክርስቶስ የመሰከርንላችሁም በእናንተ ዘንድ ጸንቷል። 7ስለዚህ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን መገለጥ በጕጕት በመጠባበቅ ላይ ሳላችሁ፣ ማንኛውም መንፈሳዊ ስጦታ አይጐድልባችሁም። 8በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ያለ ነቀፋ እንድትገኙ እርሱ እስከ መጨረሻው ድረስ አጽንቶ ይጠብቃችኋል። 9ወደ ልጁ፣ ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኅብረት የጠራችሁ እግዚአብሔር የታመነ ነው።
በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተከሠተ መለያየት
10ወንድሞች ሆይ፤ በመካከላችሁ መለያየት እንዳይኖር፣ አንድ ልብ፣ አንድ ሐሳብ እንዲኖራችሁ፣ እርስ በርሳችሁም እንድትስማሙ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ። 11ወንድሞች ሆይ፤ በመካከላችሁ ክርክር እንዳለ ከቀሎዔ ቤተ ሰብ ሰምቻለሁ፤ 12ነገሩም እንዲህ ነው፤ ከእናንተ አንዱ፣ “እኔ የጳውሎስ ነኝ” ሲል፣ ሌላው፣ “እኔ የአጵሎስ ነኝ” ይላል፤ ደግሞም አንዱ፣ “እኔ የኬፋ1፥12 ጴጥሮስ ማለት ነው ነኝ” ሲል፣ ሌላው ደግሞ፣ “እኔስ የክርስቶስ ነኝ” ይላል።
13ለመሆኑ ክርስቶስ ተከፍሏልን? ጳውሎስስ ለእናንተ ተሰቅሏልን? ወይስ በጳውሎስ1፥13 ወይም ወደ ጳውሎስ፤ እንዲሁም 15 ይመ ስም ተጠምቃችኋልን? 14ከቀርስጶስና ከጋይዮስ በስተቀር ከእናንተ ማንንም ስላላጠመቅሁ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፤ 15ስለዚህ በስሜ መጠመቁን የሚናገር ማንም የለም። 16በርግጥ የእስጢፋኖስንም ቤተ ሰው አጥምቄአለሁ፤ ከእነዚህ ሌላ ግን ማጥመቄ ትዝ አይለኝም። 17ክርስቶስ የላከኝ ወንጌልን እንድሰብክ እንጂ እንዳጠምቅ አይደለም፤ የክርስቶስም መስቀል ከንቱ እንዳይሆን፣ በሰዎች የንግግር ጥበብ አልሰብክም።
ክርስቶስ የእግዚአብሔር ኀይልና ጥበብ
18የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉ ሞኝነት ነው፤ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኀይል ነው፤ 19እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፤
“የጥበበኞችን ጥበብ አጠፋለሁ፤
የዐዋቂዎችንም ዕውቀት ከንቱ አደርጋለሁ።”
20ጠቢብ የት አለ? ሊቅስ የት አለ? የዘመኑስ ፈላስፋ የት አለ? እግዚአብሔር የዓለምን ጥበብ ሞኝነት አላደረገምን? 21ከእግዚአብሔር ጥበብ የተነሣ ዓለም በገዛ ጥበቧ እግዚአብሔርን ማወቅ ስለ ተሳናት፣ በስብከት ሞኝነት የሚያምኑትን ያድን ዘንድ የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ሆኗል። 22መቼም አይሁድ ታምራዊ ምልክትን ይፈልጋሉ፤ የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ፤ 23እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁድ መሰናክል፣ ለአሕዛብ ደግሞ ሞኝነት ነው። 24እግዚአብሔር ለጠራቸው ግን፣ አይሁድም ሆኑ ግሪኮች፣ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ኀይል፣ የእግዚአብሔርም ጥበብ ነው። 25ምክንያቱም ከሰው ጥበብ ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት ይጠበባል፤ ከሰውም ብርታት ይልቅ የእግዚአብሔር ድካም ይበረታል።
26ወንድሞች ሆይ፤ በተጠራችሁ ጊዜ ምን እንደ ነበራችሁ እስቲ አስቡ። በሰው መስፈርት ከእናንተ ብዙዎቻችሁ ዐዋቂዎች አልነበራችሁም፤ ብዙዎቻችሁም ኀያላን አልነበራችሁም፤ ብዙዎቻችሁም ከትልቅ ቤተ ሰብ አልተወለዳችሁም። 27ነገር ግን እግዚአብሔር ጥበበኞችን ያሳፍር ዘንድ የዓለምን ሞኝ ነገር መረጠ፤ እግዚአብሔር ብርቱዎችን ያሳፍር ዘንድ የዓለምን ደካማ ነገር መረጠ። 28እግዚአብሔር የተከበረውን እንደሌለ ለማድረግ፣ በዚህ ዓለም ዝቅ ያለውንና የተናቀውን ነገር፣ ቦታም ያልተሰጠውን ነገር መረጠ፤ 29ይኸውም ማንም ሰው በእርሱ ፊት እንዳይመካ ነው። 30በክርስቶስ ኢየሱስ ለመሆን የበቃችሁት ከእርሱ የተነሣ ነው፤ እርሱ ከእግዚአብሔር ዘንድ ጥበባችን፣ ጽድቃችንና ቅድስናችን፣ ቤዛችንም ሆኗል። 31እንግዲህ፣ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው፤ “የሚመካ በጌታ ይመካ።”