1 ሳሙኤል 8 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

1 ሳሙኤል 8:1-22

እስራኤል ንጉሥ ለማንገሥ መጠየቋ

1ሳሙኤል በሸመገለ ጊዜ፣ ልጆቹን ፈራጆች አድርጎ በእስራኤል ላይ ሾማቸው። 2የበኵር ልጁ ኢዮኤል ሲሆን፣ ሁለተኛው ልጁ አብያ ነበረ፤ እነርሱም በቤርሳቤህ ይፈርዱ ነበር። 3ነገር ግን ልጆቹ የአባታቸውን ፈለግ አልተከተሉም፤ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ከመንገዱ ወጡ፤ ጕቦ ተቀበሉ፤ ፍርድም አጣመሙ።

4ስለዚህ የእስራኤል ሽማግሌዎች ሁሉ በአንድነት ተሰብስበው ሳሙኤል ወዳለበት ወደ አርማቴም መጡ። 5እነርሱም፣ “አንተ አርጅተሃል፤ ልጆችህ ያንተን ፈለግ አይከተሉም፤ ስለዚህ ሌሎች ሕዝቦች እንደሚያደርጉት ሁሉ የሚመራን8፥5 በዚም ሆነ በቍጥር 6 እና 20 ላይ በትውፊት መሳፍንት ይባላል። ንጉሥ አንግሥልን” አሉት።

6ነገር ግን፣ “የሚመራን ንጉሥ አንግሥልን” ማለታቸው ሳሙኤልን አላስደሰተውም፤ ስለዚህ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ 7እግዚአብሔርም ሳሙኤልን እንዲህ አለው፤ “ንጉሣቸው እንዳልሆን የናቁት እኔን እንጂ አንተን አይደለምና ሕዝቡ የሚሉህን ሁሉ አድምጥ። 8ከግብፅ ምድር ካወጣኋቸው ዕለት አንሥቶ እስከ ዛሬ ድረስ እኔን ትተው ሌሎች አማልክትን በማምለክ ያደረጉትን ሁሉ በአንተም ላይ እያደረጉ ነው። አንተ ግን 9የሚሉህን አድምጣቸው፤ በላያቸው የሚነግሠው ንጉሥ ምን እንደሚፈጽምባቸውም አሳውቃቸው፤ በሚገባም አስጠንቅቃቸው።”

10ሳሙኤልም የእግዚአብሔርን ቃል ሁሉ፣ ንጉሥ እንዲነግሥላቸው ለጠየቁት ሕዝብ ተናገረ። 11እንዲህም አለ፤ “በላያችሁ የሚነግሠው ንጉሥ የሚያደርግባችሁ ይህ ነው፤ ወንዶች ልጆቻችሁን ወስዶ ሠረገለኞችና ፈረሰኞች ያደርጋቸዋል፤ በሠረገሎቹም ፊት ይሮጣሉ። 12አንዳንዶቹን ሻለቆችና አምሳ አለቆች ያደርጋቸዋል፤ ሌሎቹን መሬቱን እንዲያርሱና እህሉን እንዲያጭዱ፣ የቀሩትን ደግሞ የጦር መሣሪያና ለሠረገላ የሚሆኑትን ዕቃዎች እንዲሠሩ ያደርጋቸዋል፤ 13ሴቶች ልጆቻችሁን ወስዶ ሽቶ ቀማሚ፣ ወጥ ሠሪዎችና እንጀራ ጋጋሪዎች ያደርጋቸዋል። 14ከዕርሻችሁ፣ ከወይንና ከወይራ ተክል ቦታዎቻችሁ ምርጥ ምርጡን ወስዶ ለባለሟሎቹ ይሰጣቸዋል። 15ከእህላችሁና ከወይናችሁ ከዐሥር አንዱን ወስዶ ለሹማምቱና ለባለሟሎቹ ይሰጣቸዋል። 16ወንድና ሴት አሽከሮቻችሁን እንዲሁም ምርጥ ከብቶቻችሁንና8፥16 የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም ከዚህ ጋር ይስማማል፤ ዕብራይስጡ ግን ወጣቶችን ይላል። አህዮቻችሁን ለራሱ ያደርጋቸዋል። 17ከበግና ከፍየል መንጎቻችሁ አንድ ዐሥረኛውን ለራሱ ይወስዳል፤ እናንተ ራሳችሁም ባሪያዎቹ ትሆናላችሁ። 18ያም ቀን በደረሰ ጊዜ፣ ወዳችሁ ከመረጣችሁት ንጉሥ የተነሣ ትጮኻላችሁ፤ ነገር ግን በዚያ ቀን እግዚአብሔር አይመልስላችሁም።”

19ሕዝቡ ግን ሳሙኤልን መስማት እንቢ በማለት፤ እንዲህ አሉ፤ “አይሆንም፤ ንጉሥ እንዲነግሥልን እንፈልጋለን፤ 20እኛም እንደ ሌሎቹ ሕዝቦች የሚመራንና ከፊታችን የሚሄድ፣ ጦርነታችንንም የሚዋጋልን ንጉሥ ያለን ሕዝቦች እንሆናለን።”

21ሳሙኤልም ሕዝቡ ያለውን ሁሉ ሰማ፤ ያንኑ በእግዚአብሔር ፊት ተናገረው። 22እግዚአብሔርም፣ “አድምጣቸው፤ ንጉሥም አንግሥላቸው” አለው።

ከዚያም ሳሙኤል የእስራኤልን ሰዎች፣ “እያንዳንዳችሁ ወደ ከተማችሁ ተመለሱ” አላቸው።