1 ሳሙኤል 7 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

1 ሳሙኤል 7:1-17

1የቂርያትይዓሪም ሰዎችም መጥተው የእግዚአብሔርን ታቦት ይዘው ወጡ፤ ከዚያም በኰረብታው ላይ ወዳለው ወደ አሚናዳብ ቤት ወሰዱት። የእግዚአብሔርን ታቦት እንዲጠብቅም ልጁን አልዓዛርን ቀደሱት።

የፍልስጥኤማውያን መሸነፍ

2ታቦቱ በቂርያትይዓሪም ከተቀመጠ ረዥም ጊዜ ሆነው፤ በአጠቃላይ ሃያ ዓመት ቈየ። የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ አዘነ፤ እግዚአብሔርንም ፈለገ። 3ሳሙኤልም የእስራኤልን ቤት ሁሉ፣ “በፍጹም ልባችሁ ወደ እግዚአብሔር የምትመለሱ ከሆነ፣ ሌሎችን አማልክትና አስታሮትን ከመካከላችሁ አስወግዱ፤ ራሳችሁንም ለእግዚአብሔር አሳልፋችሁ ስጡ፤ እርሱንም ብቻ አምልኩ፤ እርሱም ከፍልስጥኤማውያን እጅ ይታደጋችኋል።” አላቸው። 4ስለዚህ እስራኤላውያን የበኣልንና የአስታሮትን አማልክት አስወግደው፣ እግዚአብሔርን ብቻ አመለኩ።

5ከዚያ በኋላ ሳሙኤል፣ “እስራኤልን ሁሉ በምጽጳ ሰብስቡ፤ እኔም ስለ እናንተ ወደ እግዚአብሔር እጸልያለሁ” አለ። 6እስራኤላውያን በምጽጳ በተሰበሰቡ ጊዜ፣ ውሃ ቀድተው በእግዚአብሔር ፊት አፈሰሱ፤ በዚያች ዕለት ጾሙ፤ በዚያም “እግዚአብሔርን በድለናል” ብለው ተናዘዙ። ሳሙኤልም በምጽጳ እስራኤልን ይፈርድ ነበር።

7እስራኤል በምጽጳ መሰብሰባቸውን ፍልስጥኤማውያን በሰሙ ጊዜ፣ የፍልስጥኤማውያን ገዦች ሊወጓቸው ወጡ፤ እስራኤላውያንም ይህን ሲሰሙ፣ ፍልስጥኤማውያንን ፈሩ፤ 8ሳሙኤልንም፣ “አምላካችን እግዚአብሔር ከፍልስጥኤማውያን እጅ ያድነን ዘንድ ስለ እኛ ወደ እርሱ መጸለይህን አታቋርጥ” አሉት። 9ሳሙኤልም አንድ የሚጠባ የበግ ግልገል ወስዶ ሙሉ ለሙሉ የሚቃጠል መሥዋዕት በማድረግ ለእግዚአብሔር አቀረበው፤ ስለ እስራኤልም ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ እግዚአብሔርም መለሰለት።

10ሳሙኤል የሚቃጠለውን መሥዋዕት በሚያሳርግበት ጊዜ፣ ፍልስጥኤማውያን እስራኤልን ለመውጋት ቀረቡ። ይሁን እንጂ በዚያ ዕለት እግዚአብሔር በፍልስጥኤማውያን ላይ ከባድ የነጐድጓድ ድምፅ ስላንጐዳጐደባቸው እጅግ ተሸበሩ፤ ድልም ተመተው ከእስራኤላውያን ፊት ሸሹ። 11እስራኤላውያንም ከምጽጳ ወጥተው ፍልስጥኤማውያንን በየመንገዱ እየገደሉ ከቤትካር በታች እስካለው ስፍራ ድረስ አሳደዷቸው።

12ከዚህ በኋላ ሳሙኤል አንድ ድንጋይ ወስዶ በምጽጳና በሼን መካከል አቆመው፤ ስሙንም “እግዚአብሔር እስከ አሁን ድረስ ረድቶናል” ሲል “አቤንኤዘር7፥12 አቤኔዘር ማለት የርዳታ ድንጋይ ማለት ነው።” ብሎ ጠራው። 13በዚህ ሁኔታ ፍልስጥኤማውያን ድል ስለ ተመቱ፣ የእስራኤልን ምድር ዳግመኛ አልወረሩም።

ሳሙኤል በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ፣ የእግዚአብሔር እጅ በፍልስጥኤማውያን ላይ ከብዳ ነበር። 14ፍልስጥኤማውያን ከእስራኤል የወሰዷቸው ከአቃሮን እስከ ጌት የነበሩ ከተሞች ለእስራኤል ተመለሱላት፤ ግዛታቸውም ከፍልስጥኤማውያን እጅ ነፃ ወጣች፤ በእስራኤልና በአሞራውያንም መካከል ሰላም ነበረ።

15ሳሙኤል በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ፣ እስራኤልን ይዳኝ ነበር። 16በየዓመቱ በቤቴል፣ በጌልገላና በምጽጳ እየተዘዋወረ፣ በእነዚህ ቦታዎች ሁሉ በእስራኤል ላይ ይፈርድ ነበር። 17ከዚያም በአርማቴም ወዳለው ቤቱ ይመለስ ነበር፤ በዚያም ደግሞ በእስራኤል ላይ ይፈርድ ነበር። በዚያም ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ።