ዘፀአት 8 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ዘፀአት 8:1-32

የጓጕንቸር መቅሠፍት

1ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን አለው፤ “ወደ ፈርዖን ዘንድ ሄደህ፣ እንዲህ በለው፤ ‘እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚለው ይህ ነው፤ “እኔን ያመልኩኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ። 2እነርሱን ለመልቀቅ እንቢ ብትል አገርህን ሁሉ በጓጕንቸር መቅሠፍት እመታዋለሁ። 3አባይ በጓጕንቸሮች ይሞላል፤ ወጥተውም ወደ ቤተ መንግሥትህና ወደ መኝታ ክፍልህ፣ ወደ ዐልጋህም ወደ ሹማምቶችህና ወደ ሕዝብህ ቤቶች፣ ወደ ምድጆችህና ወደ ቡሃቃዎችህ ይገባሉ። 4ጓጕንቸሮቹ ወደ አንተና ወደ ሕዝብህ ወደ ሹማምትህም ሁሉ ይመጡባችኋል።” ’ ”

5ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን አለው፣ “አሮንን፣ ‘በትርህን ይዘህ በምንጮች፣ በቦዮችና በኵሬዎች ላይ እጅህን ዘርጋ፤ ጓጕንቸሮችም በግብፅ ምድር ላይ እንዲወጡ አድርግ’ ” በለው።

6አሮንም በግብፅ ውሆች ላይ እጁን ዘረጋ፤ ጓጕንቸሮችም ወጥተው ምድሪቱን ሸፈኑ። 7ሆኖም ግን አስማተኞቹ በድብቅ ጥበባቸው ተመሳሳይ ነገር ሠሩ፤ እነርሱም በግብፅ ምድር ላይ ጓጕንቸሮች እንዲወጡ አደረጉ።

8ፈርዖንም ሙሴንና አሮንን አስጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ ጓጕንቸሮቹን ከእኔና ከሕዝቤ ያርቅ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጸልዩልኝ፤ ከዚያም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መሥዋዕትን ትሠዉ ዘንድ ሕዝቡ እንዲሄዱ እፈቅዳለሁ።

9ሙሴም ፈርዖንን፣ “በአባይ ወንዝ ካሉት በቀር ከአንተና ከቤቶችህ ጓጕንቸሮቹ እንዲወገዱ ለአንተ፣ ለሹማምትህና ለሕዝብህ የምንጸልይበትን ጊዜ እንድትወስን ለአንተ ትቸዋለሁ” አለው።

10ፈርዖንም፣ “ነገ ይሁን” አለው። ሙሴም እንዲህ ብሎ መለሰ፤ “እንደ አምላካችን እንደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ያለ ማንም እንደሌለ ታውቅ ዘንድ አንተ እንዳልኸው ይሆናል። 11ጓጕንቸሮቹም ከአንተና ከቤቶችህ፣ ከሹማምትህና ከሕዝብህ ተወግደው በአባይ ወንዝ ብቻ ይወሰናሉ።”

12ሙሴና አሮን ከፈርዖን ዘንድ ከተመለሱ በኋላ፣ በፈርዖን ላይ እግዚአብሔር (ያህዌ) ስላመጣቸው ጓጕንቸሮች ሙሴ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጮኸ። 13እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴ እንደ ለመነው አደረገ፤ ጓጕንቸሮቹም በየቤቱ ውስጥ፣ በየዐጥር ግቢውና በየሜዳው ሞቱ። 14በአንድ ላይ ሰብስበው ከመሯቸው፤ ምድሪቱም ከረፋች። 15ፈርዖን ችግሩ ጋብ ማለቱን ባየ ጊዜ ግን ልክ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ ተናገረው ልቡን በማደንደን ሙሴንና አሮንን አልሰማቸውም።

የተባይ መቅሠፍት

16ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን፣ “አሮንን ‘በትርህን ሰንዝረህ የምድርን ትቢያ ምታ’ በለው፤ ከዚያም በግብፅ ምድር ያለው ትቢያ ሁሉ ተናካሽ ትንኝ ይሆናል” አለው። 17እነርሱም እንዲሁ አደረጉ፣ አሮን በትሩን እንደ ያዘ እጁን ሲዘረጋና የምድሩን ትቢያ ሲመታ፣ በግብፅ ምድር ያለው ትቢያ ሁሉ ተናካሽ ትንኝ ሆነ። ሰውንም ሆነ እንስሳውን ተናካሽ ትንኝ ወረረው። 18ነገር ግን አስማተኞቹ በድብቅ ጥበባቸው ተናካሽ ትንኞችን ለመፍጠር ሲሞክሩ አልቻሉም። ተናካሽ ትንኞቹም ከሰውና ከእንስሳው ላይ አልወረዱም ነበር። 19አስማተኞቹም ፈርዖንን፣ “ይህ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ጣት ነው” አሉት፤ ነገር ግን የፈርዖን ልብ ደንድኖ ስለ ነበር፣ ልክ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ ተናገረው አልሰማቸው አለ።

የዝንብ መቅሠፍት

20ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “በጧት ተነሥተህ ፈርዖን ወደ ውሃ በሚወርድበት ጊዜ ከፊቱ ቀርበህ እንዲህ በለው፤ ‘እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚለው ይህ ነው፤ ያመልኩኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ። 21ሕዝቤ እንዲሄዱ ባትለቅቃቸው፣ በአንተና በሹማምትህ ላይ፣ በሕዝብህና በቤቶችህ ላይ የዝንብ መንጋ እሰድዳለሁ። ያረፉበት መሬት እንኳ ሳይቀር፣ የግብፃውያን ቤቶች ሁሉ ዝንብ ብቻ ይሆናሉ።

22“ ‘በዚያች ዕለት ግን ሕዝቤ የሚኖርባትን የጌሤምን ምድር የተለየች አደርጋታለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) በዚህች ምድር እንዳለሁ ታውቅ ዘንድ የዝንብ መንጋ በዚያ አይኖርም። 23በሕዝቤና በሕዝብህ መካከል ልዩነት አደርጋለሁ፤ ይህ ታምራዊ ምልክት ነገ ይሆናል8፥23 የሰብዓ ሊቃናቱና የቫልጌቱ ትርጕም እንዲሁ ሲሉ፣ ዕብራይስጡ ግን ነገ ዐርነት ይሆናል ይላል።።’ ”

24እግዚአብሔርም (ያህዌ) እንዲሁ አደረገ፤ አስጨናቂ የዝንብ መንጋ በፈርዖን ቤተ መንግሥትና በሹማምቱ ቤቶች ላይ ወረደ፤ መላው የግብፅ ምድር ከዝንቡ የተነሣ ተበላሽቶ ነበር።

25ከዚያም ፈርዖን ሙሴንና አሮንን አስጠርቶ፣ “ሂዱና በዚሁ ምድር ለአምላካችሁ ሠዉ” አላቸው።

26ሙሴ ግን እንዲህ አለ፤ “ይህ ትክክል አይሆንም፤ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የምናቀርበው መሥዋዕት በግብፃውያን ዘንድ አስጸያፊ ነው፤ ታዲያ በእነርሱ ዐይን አስጸያፊ የሆነውን መሥዋዕት ብናቀርብ አይወግሩንምን? 27ለአምላካችን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) እርሱ እንዳዘዘን መሥዋዕት ለመሠዋት ወደ ምድረ በዳ የሦስት ቀን መንገድ መሄድ አለብን።”

28ፈርዖንም፣ “ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በምድረ በዳ መሥዋዕት እንድትሠዉ እፈቅድላችኋለሁ፤ ነገር ግን ርቃችሁ እንዳትሄዱ። ለእኔም ጸልዩልኝ” አላቸው።

29ሙሴም እንዲህ አለ፤ “ከአንተ እንደ ተለየሁ ወዲያውኑ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) እጸልያለሁ፤ ነገም ዝንቡ ሁሉ ከፈርዖን፣ ከሹማምቱና ከሕዝቡ ይወገዳል። ብቻ ሕዝቡ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መሥዋዕት እንዲሠዉ ባለመፍቀድ ከዚህ ቀደም ፈርዖን አታልሎ እንዳደረገው አሁንም እንዳያደርግ ርግጠኛ ይሁን።”

30ከዚያም ሙሴ ከፈርዖን ተለይቶ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጸለየ። 31እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴ የለመነውን አደረገ። የዝንቡም መንጋ ከፈርዖን፣ ከሹማምቱና ከሕዝቡ ተወገደ፤ አንድም ዝንብ እንኳ አልቀረም። 32በዚህም ጊዜ እንኳ ፈርዖን ልቡን አደነደነ እንጂ፣ ሕዝቡን አልለቀቀም።