ዘፀአት 10 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ዘፀአት 10:1-29

የአንበጣ መንጋ መቅሠፍት

1ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ተመልሰህ ወደ ፈርዖን ሂድ፤ እነዚህን ታምራዊ ምልክቶች በመካከላቸው ለማድረግ የፈርዖንንና የሹማምቱን ልብ አደንድኛለሁና፤ 2ይኸውም ግብፃውያንን እንዴት አድርጌ እንደ ቀጣኋቸውና በመካከላቸውም ምልክቶቼን እንዴት እንዳደረግሁ ለልጆቻችሁና ለልጅ ልጆቻችሁ እንድትነግሩና እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) መሆኔንም እንድታውቁ ነው።”

3ሙሴና አሮን ወደ ፈርዖን ሄደው እንዲህ አሉት፤ “የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) እንዲህ ይላል፤ ‘ራስህን በፊቴ ለማዋረድ እስከ መቼ እንቢ ትላለህ? ሕዝቤ ያመልኩኝ ዘንድ ልቀቃቸው። 4እንዳይሄዱ ብትከለክላቸው ነገ በአገርህ ላይ አንበጣዎችን አመጣለሁ። 5አንበጣዎቹም ምድሪቱ እስከማትታይ ድረስ ይሸፍኗታል፤ በመስክህ ላይ እያቈጠቈጠ ያለውን ዛፍ ሁሉ ሳይቀር ከበረዶ የተረፈውንም ጥቂቱን ሁሉ ይበሉታል። 6የአንተን፣ የሹማምትህንና የግብፃውያንን ቤቶች ሁሉ ይሞሏቸዋል፤ ይህም አባቶችህም ሆኑ ቅድመ አያቶችህ በዚህች ምድር ከሰፈሩበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከቶ አይተውት የማያውቁት ነው።’ ” ሙሴም ተመለሰና ከፈርዖን ተለይቶ ሄደ።

7የፈርዖንም ሹማምት፣ “ይህ ሰው እስከ መቼ ወጥመድ ይሆንብናል? አምላካቸውን እግዚአብሔርን (ያህዌ) እንዲያመልኩ ሰዎቹን ልቀቃቸውና ይሂዱ። ግብፅ መጥፋቷን እስካሁን አልተገነዘብህምን?” አሉት።

8ከዚያም ሙሴና አሮን ወደ ፈርዖን እንዲመጡ ተደረገ፤ “ሂዱ አምላካችሁን እግዚአብሔርን (ያህዌ) አምልኩ፤ ነገር ግን መሄድ የሚገባቸው የትኞቹ ናቸው?” አለ።

9ሙሴም፣ “ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በዓል ልናከብር ስለሆነ ወጣቶቻችንንና ሽማግሌዎቻችንን፣ ወንድና ሴት ልጆቻችንን፣ የበግና የፍየል መንጋዎቻችንን እንዲሁም የቀንድ ከብቶቻችንን ይዘን እንሄዳለን” አለ።

10ፈርዖንም እንዲህ አለ፤ “ከሴቶቻችሁና ከልጆቻችሁ ጋር እንድትሄዱ እለቅቃችኋለሁ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ከእናንተ ጋር ይሁን፤ ነገር ግን ተንኰል አስባችኋል።10፥10 ወይም፣ ተጠንቀቁ፤ ችግር ተዘጋጅቶላችኋል 11አይሆንም፤ ወንዶቹ ብቻ እንዲሄዱና እግዚአብሔርን (ያህዌ) እንዲያመልኩ አድርጉ፤ የጠየቃችሁት ይህንኑ ነው።” ከዚያም ሙሴና አሮን ከፈርዖን ፊት እንዲወጡ ተደረገ።

12እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን፣ “የአንበጣ መንጋ ምድሪቱን እንዲወርር ከበረዶ የተረፈውን ሁሉና በማሳም ላይ የበቀለውን ሁሉ ጠርጎ እንዲበላ እጅህን በግብፅ አገር ላይ ዘርጋ” አለው።

13ስለዚህ ሙሴ በግብፅ አገር ላይ በትሩን ዘረጋ፤ እግዚአብሔርም (ያህዌ) በዚያን ቀንና ሌሊት በሙሉ በምድሪቱ ላይ የምሥራቅ ነፋስ እንዲነፍስ አደረገ፤ በማግሥቱም ነፋሱ አንበጣዎችን አመጣ። 14እነርሱም ግብፅን በሙሉ ወረሩ፤ ስፍር ቍጥር የሌላቸው ሆነው የሀገሪቱን ዳር ድንበር ሁሉ አለበሱ። እንዲህ ያለ የአንበጣ መዓት ከዚህ ቀደም አልነበረም፤ ወደ ፊትም ደግሞ አይኖርም። 15ምድሩ ሁሉ ጠቍሮ እስኪጨልም ድረስ አለበሱት። ከበረዶ የተረፈውን፣ በመስክ ላይ የበቀለውንና በዛፍ ላይ ያለውን ፍሬ ሁሉ ጠርገው በሉ። በግብፅ ምድር ሁሉ በዛፍ ላይ ወይም በተክል ላይ አንዳች ቅጠል አልተረፈም ነበር።

16ከዚያም ፈርዖን ሙሴንና አሮንን በፍጥነት አስጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “በአምላካችሁ በእግዚአብሔር (ያህዌ) በእናንተም ላይ ኀጢአት ሠርቻለሁ፤ 17እንግዲህ አሁን አንድ ጊዜ ደግሞ ኀጢአቴን ይቅር በሉኝና ይህን ቀሣፊ መዓት እንዲያስወግድልኝ አምላካችሁን እግዚአብሔርን (ያህዌ) ለምኑልኝ።”

18ሙሴም ከፈርዖን ዘንድ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጸለየ። 19ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ነፋሱን ወደ ብርቱ የምዕራብ ነፋስ ለወጠው፤ ያም ነፋስ አንበጣዎቹን እየነዳ ወደ ቀይ ባሕር10፥19 ዕብራይስጡ “ያም ሱፍ” ይለዋል የሸንበቆ ባሕር ማለት ነው። ከተታቸው፤ በግብፅ ምድር በየትኛውም ቦታ አንድም አንበጣ አልቀረም። 20እግዚአብሔር (ያህዌ) ግን የፈርዖንን ልብ አደነደነ፤ ፈርዖንም እስራኤላውያን እንዲሄዱ አልፈቀደም።

የጨለማ መቅሠፍት

21ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን፣ “በግብፅ ላይ ድቅድቅ ጨለማ እንዲወርድ እጅህን ወደ ሰማይ ዘርጋ” አለው። 22ሙሴም እጁን ወደ ሰማይ ዘረጋ፤ በመላው ግብፅ ላይ ለሦስት ቀናት ድቅድቅ ያለ ጨለማ ሆነ። 23በእነዚያ ሦስት ቀናት ውስጥ አንዱ ሌላውን ማየት ወይም ከነበረበት ቦታ መንቀሳቀስ አይችልም ነበር። ይሁን እንጂ እስራኤላውያን በሚኖሩበት ስፍራ ሁሉ ብርሃን ነበር።

24ከዚያም ፈርዖን ሙሴን አስጠርቶ፣ “ሄዳችሁ እግዚአብሔርን (ያህዌ) አምልኩ፤ ሴቶቻችሁና ልጆቻችሁ ሳይቀሩ አብረዋችሁ ይሂዱ፤ በጎቻችሁ፣ ፍየሎቻችሁና የጋማ ከብቶቻችሁ ብቻ እዚሁ ይቅሩ” አለው።

25ሙሴም እንዲህ አለው፤ “ለአምላካችን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መሥዋዕትና የሚቃጠል መሥዋዕት እንድንሠዋ ፍቀድልን፤ 26እንስሶቻችን ሁሉ አብረው መሄድ አለባቸው። አንድ ሰኰና እንኳ አይቀርም። ከእንስሶቻችን መካከል ለአምላካችን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አምልኮ የምናቀርባቸው ይኖራሉ፤ ሆኖም እዚያ ከመድረሳችን በፊት እግዚአብሔርን (ያህዌ) ለማምለክ የምናቀርባቸው እንስሳት የትኞቹ እንደ ሆኑ አስቀድመን ለይተን ማወቅ አንችልም።”

27ነገር ግን እግዚአብሔር (ያህዌ) የፈርዖንን ልብ አደነደነ፤ ፈርዖንም ሕዝቡን መልቀቅ አልፈቀደም። 28ፈርዖን ሙሴን፣ “ከፊቴ ጥፋ! ሁለተኛ እኔ ዘንድ እንዳትደርስ! ፊቴን ባየህበት በዚያ ቀን ፈጽመህ እንደምትሞት ዕወቅ” አለው።

29ሙሴም፣ “እንዳልከው ይሁን፤ እኔም ዳግመኛ ከፊትህ አልደርስም” አለው።