ዘዳግም 24 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ዘዳግም 24:1-22

1አንድ ሰው አንዲት ሴት ካገባ በኋላ፣ አሳፋሪ ነገር አግኝቶባት ባይደሰትባት፣ የፍቺ ወረቀት ጽፎ በመስጠት ከቤቱ አስወጥቶ ይስደዳት። 2ከቤቱ ከወጣች በኋላ ሌላ ባል ብታገባ፣ 3ሁለተኛ ባሏም እንደዚሁ ጠልቷት የፍቺ ወረቀት በመስጠት ከቤቱ አስወጥቶ ቢሰድዳት ወይም ቢሞት፣ 4ከዚያ በኋላ የፈታት የመጀመሪያ ባሏ፣ የረከሰች በመሆኗ እንደ ገና መልሶ ሊያገባት አይችልም፤ ይህ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት አስጸያፊ ነው። አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር ላይ ኀጢአት አታምጣ።

5አዲስ ሚስት በቅርብ ጊዜ ያገባ ሰው፣ ለጦርነት አይሂድ፤ ወይም ሌላ ሥራ እንዲሠራ አይገደድ። ለአንድ ዓመት ነጻ ሆኖ እቤቱ ይቈይ፤ ያገባትን ሚስቱን ደስ ያሰኛት።

6ወፍጮና መጁን ወይም መጁንም እንኳ ቢሆን፣ የብድር መያዣ አድርገህ አትውሰድ፤ የሰውን ነፍስ መያዣ አድርጎ መውሰድ ይሆናልና።

7አንድ ሰው ከእስራኤላውያን ወንድሞቹ አንዱን ፈንግሎ በመውሰድ ባሪያ ሲያደርገው ወይም ሲሸጠው ቢገኝ፣ ፈንጋዩ ይሙት። ክፉውን ከመካከልህ አስወግድ።

8የለምጽ ደዌን24፥8 ዕብራይስጡ ለምጽን ብቻ ሳይሆን ቈዳን የሚያጠቁትን ማናቸውንም ዐይነት በሽታዎች ያመለክታል። በተመለከተ ሌዋውያን ካህናት የሚሰጡህን መመሪያ በትክክል ለመፈጸም ጥንቃቄ አድርግ። እኔ ለእነርሱ የሰጠሁትን ትእዛዝ በጥንቃቄ ተከተል። 9ከግብፅ ከወጣችሁ በኋላ በመንገድ ላይ ሳላችሁ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በማርያም ላይ ያደረገባትን አስታውሱ።

10ማናቸውንም ነገር ለባልንጀራህ ስታበድር መያዣ አድርጎ የሚሰጥህን ለመቀበል ወደ ቤቱ አትግባ። 11አንተ ከውጭ ሆነህ ጠብቅ፤ ያበደርኸውም ሰው መያዣውን ከቤት ያምጣልህ። 12ሰውየው ድኻ ከሆነ፣ መያዣውን ከአንተ ዘንድ አታሳድርበት። 13መደረቢያውን ለብሶት እንዲያድር ፀሓይ ሳትጠልቅ መልስለት። ከዚያም ያመሰግንሃል፤ በአምላክህ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊትም የጽድቅ ሥራ ሆኖ ይቈጠርልሃል።

14ድኻና ችግረኛ የሆነውን የምንዳ ሠራተኛ እስራኤላዊ ወንድምህም ሆነ፣ ከከተሞችህ በአንዲቱ የሚኖረውን መጻተኛ አትበዝብዘው፤ 15የሠራበትን ሒሳብ በዕለቱ፣ ፀሓይ ሳትጠልቅ ክፈለው፤ ድኻ በመሆኑ በጕጕት ይጠባበቀዋልና። አለዚያ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ይጮኽና ኀጢአት ይሆንብሃል።

16አባቶች ስለ ልጆቻቸው፣ ልጆችም ስለ አባቶቻቸው አይገደሉ፤ እያንዳንዱ በራሱ ኀጢአት ይገደል።

17ለመጻተኛው ወይም አባት ለሌለው ልጅ ፍትሕ አትንፈገው፤ የመበለቲቱንም መደረቢያ መያዣ አታድርግ። 18አንተም በግብፅ ባሪያ እንደ ነበርህና አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ከዚያ እንደ ተቤዠህ አስታውስ፤ ይህን እንድታደርግ ያዘዝሁህ ለዚህ ነው።

19የዕርሻህን ሰብል በምታጭድበት ጊዜ፣ ተረስቶ የቀረ ነዶ ቢኖር፣ ያን ለመውሰድ ተመልሰህ አትሂድ። አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በእጅህ ሥራ ሁሉ እንዲባርክህ ነዶውን ለመጻተኛው፣ አባት ለሌለውና ለመበለቲቱ ተወው። 20የወይራ ዛፍህን ፍሬ በምታራግፍበት ጊዜ፣ በየቅርንጫፉ ላይ የቀረውን ለመቃረም ተመልሰህ አትሂድ፤ ለመጻተኛው፣ አባት ለሌለውና ለመበለቲቱ ተወው። 21የወይን ተክልህን ፍሬ ስትሰበስብ ቃርሚያውን ለመሰብሰብ አትመለስበት፤ የቀረውን ለመጻተኛው፣ አባት ለሌለውና ለመበለቲቱ ተወው። 22በግብፅ ባሪያ እንደ ነበርህ አስታውስ፤ ይህን እንድታደርግ ያዘዝሁህ ለዚህ ነው።