ዘሌዋውያን 8 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ዘሌዋውያን 8:1-36

አሮንና ልጆቹ ካህናት ሆነው መሾማቸው

8፥1-36 ተጓ ምብ – ዘፀ 29፥1-37

1እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ 2“አሮንንና ልጆቹን፣ ልብሰ ተክህኖውን፣ የመቅቢያ ዘይቱን፣ ለኀጢአት መሥዋዕት የሚሆነውን ወይፈን፣ ሁለቱን አውራ በጎችና እርሾ ሳይገባበት የተጋገረው ቂጣ ያለበትን መሶብ አምጣ፤ 3ማኅበሩን በሙሉ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ሰብስብ።” 4ሙሴም እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዳዘዘው አደረገ፤ ማኅበሩም በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ተሰበሰበ።

5ሙሴም ማኅበሩን፣ “እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲደረግ ያዘዘው ይህ ነው” አላቸው። 6ሙሴም አሮንንና ልጆቹን ወደ ፊት አወጣቸው፤ በውሃም ዕጠባቸው። 7አሮንን እጀ ጠባብ አለበሰው፤ መቀነት አስታጠቀው፤ ቀሚስ አጠለቀለት፤ ኤፉድ ደረበለት፤ በልዩ ጥበብ በተጠለፈው መታጠቂያ ኤፉዱን አስታጠቀው፤ በላዩም አሰረው፤ 8የደረት ኪሱን በላዩ አደረገለት፤ በደረት ኪሱም ውስጥ ኡሪምንና ቱሚምን አኖረ። 9እግዚአብሔር (ያህዌ) ባዘዘውም መሠረት፣ ሙሴ ጥምጥሙን በአሮን ራስ ላይ አደረገ፤ በጥምጥሙም ላይ በፊት ለፊቱ በኩል የተቀደሰውን የወርቅ አክሊል አደረገለት።

10ሙሴም መቅቢያ ዘይቱን ወሰደ፤ ማደሪያ ድንኳኑንና በውስጡ የሚገኘውን ሁሉ ቀብቶ ቀደሰ። 11ከዘይቱም ጥቂት ወስዶ በመሠዊያው ላይ ሰባት ጊዜ ረጨ፤ ይቀድሳቸውም ዘንድ መሠዊያውን ከነመገልገያ ዕቃው ሁሉ እንዲሁም የመታጠቢያ ሳሕኑን ከነማስቀመጫው በዘይት ቀባ። 12ከመቅቢያ ዘይቱም በአሮን ራስ ላይ አፈሰሰ፤ የተቀደሰ እንዲሆንም ቀባው። 13እግዚአብሔርም (ያህዌ) ባዘዘው መሠረት ሙሴ፣ የአሮንን ልጆች ወደ ፊት አቅርቦ እጀ ጠባብ አለበሳቸው፤ መታጠቂያ አስታጠቃቸው፤ ቆብም ደፋላቸው።

14ሙሴም የኀጢአት መሥዋዕት የሆነውን ወይፈን አመጣ፤ አሮንና ልጆቹም በወይፈኑ ራስ ላይ እጃቸውን ጫኑ። 15ሙሴም ወይፈኑን ዐረደ፤ ደሙንም ወስዶ መሠዊያውን ያነጻ ዘንድ በጣቱ የመሠዊያውን ቀንዶች ሁሉ ቀባ፤ የቀረውንም ደም በመሠዊያው ሥር አፈሰሰው። ለመሠዊያውም እንዲህ አድርጎ ያስተሰርይለት ዘንድ ቀደሰው። 16ሙሴም የሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ሁሉ፣ የጕበቱን ሽፋን፣ ኵላሊቶችንና ሥባቸውን ወስዶ በመሠዊያው ላይ አቃጠለ። 17ሙሴም እግዚአብሔር (ያህዌ) ባዘዘው መሠረት ወይፈኑን፣ ቈዳውን፣ ሥጋውንና ፈርሱን ከሰፈር ውጭ አቃጠለ።

18ሙሴ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውን አውራ በግ አቀረበ፤ አሮንና ልጆቹም እጃቸውን በበጉ ላይ ጫኑ። 19ሙሴም በጉን ዐርዶ ደሙን በመሠዊያው ላይ ዙሪያውን ረጨ። 20በጉንም በየብልቱ ቈራረጠ፤ ጭንቅላቱን፣ ብልቶቹንና ሥቡን አቃጠለ። 21ሆድ ዕቃውንና እግሮቹን በውሃ አጠበ፤ ሙሴም እግዚአብሔር (ያህዌ) ባዘዘው መሠረት፣ በጉን በሙሉ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት የሚቀርብ፣ ሽታውም ደስ የሚያሰኝ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ በመሠዊያው ላይ አቃጠለው።

22ሙሴ ለቅድስና የሚሆነውን ሌላ አውራ በግ አቀረበ፤ አሮንና ልጆቹም እጆቻቸውን በበጉ ራስ ላይ ጫኑ። 23ሙሴ አውራ በጉን ዐረደ፤ ከደሙም ጥቂት ወስዶ የአሮንን ቀኝ ጆሮ ጫፍ፣ የቀኝ እጁን አውራ ጣትና የቀኝ እግሩን አውራ ጣት አስነካ፤ 24የአሮንንም ልጆች ወደ ፊት ጠራ፤ ከደሙም ጥቂት ወስዶ የቀኝ ጆሯቸውን ጫፍ፣ የቀኝ እጃቸውን አውራ ጣትና የቀኝ እግራቸውን አውራ ጣት አስነካ፤ የቀረውንም ደም በመሠዊያው ላይ ዙሪያውን ረጨ። 25ሥቡን፣ ላቱን፣ ሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ሥብ ሁሉ፣ የጕበቱን ሽፋን፣ ሁለቱን ኵላሊቶችና ሥባቸውን እንዲሁም ቀኝ ወርቹን ወሰደ፤ 26በእግዚአብሔርም (ያህዌ) ፊት ካለው፣ ያለ እርሾ የተጋገረ ዳቦ ካለበት መሶብ ላይ አንድ ኅብስት፣ አንድ በዘይት የተጋገረ ዳቦ እንዲሁም ስስ ቂጣ ወስዶ በሥቦቹና በቀኝ ወርቹ ላይ አኖረ። 27እነዚህንም ሁሉ ለአሮንና ለልጆቹ በእጃቸው ሰጣቸው፤ እነርሱም የሚወዘወዝ መሥዋዕት አድርገው በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ወዘወዙት። 28ሙሴም ከእጃቸው ተቀብሎ፣ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት የሚቀርብ፣ ሽታውም ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት አድርጎ በመሠዊያው ላይ በሚቃጠለው መሥዋዕት ላይ አቃጠለው። 29ሙሴም እግዚአብሔር (ያህዌ) ባዘዘው መሠረት፣ ድርሻው የሆነውን ክህነት የመስጫውን አውራ በግ ፍርምባ ወስዶ የሚወዘወዝ መሥዋዕት በማድረግ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ወዘወዘው።

30ቀጥሎም ሙሴ በመቅቢያው ዘይትና በመሠዊያው ላይ ካለው ደም ጥቂት ወስዶ፣ በአሮንና በልብሱ እንዲሁም በአሮን ልጆችና በልብሳቸው ላይ ረጨ፤ በዚህም ሁኔታ አሮንንና ልብሱን፣ ልጆቹንና ልብሳቸውን ቀደሰ።

31ሙሴም አሮንና ልጆቹን እንዲህ አላቸው፤ “ሥጋውን በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ቀቅሉት፤ በዚያም፣ ‘አሮንና ልጆቹ ይብሉት’ ተብዬ በታዘዝሁት8፥31 ወይም ብዬ ባዘዝሁት መሠረት፣ በክህነት መስጫው መሥዋዕት መሶብ ውስጥ ካለው ኅብስት ጋር ብሉት፤ 32የተረፈውንም ሥጋና ኅብስት በእሳት አቃጥሉ። 33የክህነት መቀበያችሁ ሥርዐት እስከሚፈጸምበት እስከ ሰባት ቀን ድረስ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ቈዩ፤ ሥርዐቱንም ለመፈጸም ሰባት ቀን ይወስዳልና። 34ዛሬ የተፈጸመው ይህ ሥርዐት ለእናንተ ማስተስረያ እግዚአብሔር (ያህዌ) ያዘዘው ነው። 35እንዳትሞቱ ሰባቱን ቀንና ሌሊት ከመገናኛው ድንኳን ደጃፍ አትለዩ፤ የእግዚአብሔርንም (ያህዌ) ሥርዐት ጠብቁ፤ የታዘዝሁት እንዲህ ነውና።” 36አሮንና ልጆቹም እግዚአብሔር (ያህዌ) በሙሴ አማካይነት ያዘዘውን ሁሉ አደረጉ።