ዘሌዋውያን 17 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ዘሌዋውያን 17:1-16

ደም መብላት ስለ መከልከሉ

1እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ 2“ለአሮንና ለልጆቹ፣ ለእስራኤላውያንም ሁሉ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘እግዚአብሔር (ያህዌ) ያዘዘው ይህ ነው፤ 3ማንኛውም እስራኤላዊ በሰፈር ውስጥ ወይም ከሰፈር ውጭ በሬ፣17፥3 የዕብራይስጡ ቃል ተባዕትና እንስትን ሊያጠቃልል ይችላል። በግ ወይም ፍየል ቢያርድ፣ 4በእግዚአብሔር (ያህዌ) ማደሪያ ፊት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መሥዋዕት አድርጎ ለማቅረብ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ባያመጣው፣ ያ ሰው በከንቱ ደም እንዳፈሰሰ ይቈጠራል፤ ደም በማፍሰሱም ከወገኖቹ ተለይቶ ይጥፋ። 5እስራኤላውያን የሚሠዉትን መሥዋዕት ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚያመጡበት ምክንያት ይህ ነው። ይህንም ካህኑ ዘንድ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ አምጥተው ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የኅብረት መሥዋዕት17፥5 በትውፊት የሰላም መሥዋዕት ይባላል በማድረግ ያቅርቡ። 6ካህኑም ደሙን በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ባለው በእግዚአብሔር (ያህዌ) መሠዊያ ላይ ይርጭ፤ ሥቡንም እግዚአብሔርን (ያህዌ) ደስ የሚያሰኝ ሽታ እንዲሆን ያቃጥል። 7ከዚህ በፊት ላመነዘሩባቸው አጋንንት17፥7 ወይም የፍየል ጣዖታት ከእንግዲህ ወዲህ ማንኛውንም መሥዋዕት ሊሠዉ አይገባም። ይህ ለእነርሱና ከእነርሱ በኋላ ለሚነሣው ትውልድ ሁሉ የዘላለም ሥርዐት ይሁን።’

8“እንዲህም በላቸው፤ ‘የሚቃጠል መሥዋዕት ወይም ሌላ መሥዋዕት የሚያቀርብ ማንኛውም እስራኤላዊ ወይም በመካከላቸው የሚኖር ማንኛውም መጻተኛ፣ 9ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ባያቀርብ፣ ያ ሰው ከወገኖቹ ተለይቶ ይጥፋ።

10“ ‘ማንኛውም እስራኤላዊ ወይም በመካከላቸው የሚኖር ማንኛውም መጻተኛ ደም ቢበላ፣ ደም በሚበላው በዚያ ሰው ላይ ፊቴን አከብድበታለሁ፤ ከወገኖቹም ለይቼ አጠፋዋለሁ፤ 11የፍጡር ሕይወት በደሙ ውስጥ ነውና፤ በመሠዊያ ላይ ለሕይወታችሁ ማስተስረያ እንዲሆን ደሙን ሰጥቻችኋለሁ፤ ለሰውም ሕይወት ስርየት የሚያስገኝ ደም ነው። 12ስለዚህ እስራኤላውያንን፣ “ከእናንተ ማንም ደም አይብላ፤ በመካከላችሁ የሚኖር መጻተኛም ቢሆን ደም አይብላ” አልሁ።

13“ ‘እንዲበላ የተፈቀደውን ማንኛውንም እንስሳ ወይም ወፍ ዐድኖ የያዘ ማንኛውም እስራኤላዊ ወይም በመካከላችሁ የሚኖር ማንኛውም መጻተኛ ደሙን ከውስጡ ያፍስስ፤ ዐፈርም ያልብሰው፤ 14የማንኛውም ፍጡር ሕይወት ደሙ ነውና። ስለዚህ እስራኤላውያንን፣ “የፍጡር ሁሉ ሕይወት ደሙ ነውና የማንኛውንም ፍጡር ደም አትብሉ፤ የበላው ሰው ሁሉ ተለይቶ ይጥፋ” አልኋቸው።

15“ ‘ሞቶ የተገኘውን ወይም አውሬ የዘነጠለውን የበላ ማንኛውም የአገር ተወላጅ ወይም መጻተኛ ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱንም በውሃ ይታጠብ፤ በሥርዐቱ መሠረት እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ ከዚያም በኋላ ንጹሕ ይሆናል። 16ልብሱን ባያጥብ፣ ሰውነቱንም ባይታጠብ ግን ኀጢአት ሠርቷልና ይጠየቅበታል።’ ”