ዘሌዋውያን 1 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ዘሌዋውያን 1:1-17

የሚቃጠል መሥዋዕት

1እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን ጠራው፤ ከመገናኛውም ድንኳን እንዲህ ሲል ተናገረው፤ 2“እስራኤላውያንን ተናገራቸው፤ እንዲህም በላቸው፤ ከእናንተ ማንም ሰው ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ከእንስሳ ወገን መባ በሚያቀርብበት ጊዜ ከላሙ፣ ከበጉ ወይም ከፍየሉ መንጋ መካከል ያቅርብ።

3“ ‘መባው በሚቃጠል መሥዋዕትነት ከላሞች መንጋ መካከል የሚቀርብ ከሆነ፣ እንከን የሌለበትን ተባዕቱን መሥዋዕት በእግዚአብሔር (ያህዌ) ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ላይ ያቅርበው። 4የሚቃጠል መሥዋዕት ሆኖ በሚቀርበው እንስሳ ራስ ላይም እጁን ይጫን፤ ይህም ያስተሰርይለት ዘንድ በምትኩ ተቀባይነት ያገኛል። 5ወይፈኑን በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ይረደው፤ ካህናቱ የአሮን ልጆችም ደሙን አምጥተው በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ባለው በመሠዊያው ዙሪያ ሁሉ ይርጩት። 6እርሱም የሚቃጠለውን መሥዋዕት ቈዳ ይግፈፍ፤ ብልቱንም ያውጣው። 7የካህኑ የአሮን ልጆች በመሠዊያው ላይ ዕንጨት ረብርበው እሳት ያንድዱበት። 8ካህናቱ የአሮን ልጆች ጭንቅላቱንና ሥቡን ጨምረው ብልቶቹን በመሠዊያው ላይ በሚነድደው ዕንጨት ላይ ይደርድሩት፤ 9አቅራቢው የሆድ ዕቃውንና እግሮቹን በውሃ ይጠብ፤ ካህኑም መባውን ሁሉ በመሠዊያው ላይ ያቃጥል፤ ይህም በእሳት የሚቀርብ፣ ሽታውም እግዚአብሔርን (ያህዌ) ደስ የሚያሰኝ የሚቃጠል መሥዋዕት ይሆናል።

10“ ‘መባው በሚቃጠል መሥዋዕትነት ከበግ ወይም ከፍየል መንጋ መካከል የሚቀርብ ከሆነ፣ እንከን የሌለበትን ተባዕቱን ያቅርብ። 11የሚቀርበውን መሥዋዕት ከመሠዊያው በስተ ሰሜን በኩል በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ይረደው፤ ካህናቱ የአሮን ልጆችም ደሙን በመሠዊያው ላይ ዙሪያውን ሁሉ ይርጩት። 12አቅራቢው ብልቶቹን ያውጣ፤ ካህኑም ጭንቅላቱንና ሥቡን ጨምሮ በመሠዊያው ላይ በሚነድደው ዕንጨት ላይ ይደርድረው፤ 13አቅራቢው የሆድ ዕቃውንና እግሮቹን በውሃ ይጠብ፤ ካህኑ መባውን ሁሉ አምጥቶ በመሠዊያው ያቃጥል፤ ይህም በእሳት የሚቀርብ፣ ሽታውም እግዚአብሔርን (ያህዌ) ደስ የሚያሰኝ የሚቃጠል መሥዋዕት ይሆናል።

14“ ‘ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በሚቃጠል መሥዋዕትነት የሚቀርበው መባ ከወፎች ወገን ከሆነ፣ ዋኖስ ወይም የርግብ ጫጩት ያቅርብ። 15ካህኑም ወደ መሠዊያው ያምጣው፤ ራሱን ቈልምሞ ይቀንጥሰው፤ የተቈረጠውንም ራስ በመሠዊያው ላይ ያቃጥል፤ ደሙም በመሠዊያው አጠገብ ይንጠፍጠፍ፤ 16ከሆድ ዕቃውም ጥሬ ቤቱን1፥16 ለዚህ ቃል የዕብራይስጡ ትርጓሜ በርግጠኝነት አይታወቅም። ለይቶ ከላባዎቹ ጋር ከመሠዊያው በስተ ምሥራቅ በኩል፣ ዐመድ በሚፈስስበት ስፍራ ይጣለው። 17በክንፎቹ በኩል ለሁለት ይሰንጥቀው፤ ነገር ግን ጨርሶ አያለያየው፤ ካህኑም በመሠዊያው ላይ በሚነድደው ዕንጨት ላይ ያቃጥለው፤ ይህም በእሳት የሚቀርብ፣ ሽታውም እግዚአብሔርን (ያህዌ) ደስ የሚያሰኝ የሚቃጠል መሥዋዕት ይሆናል።