ኢዮብ 22 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ኢዮብ 22:1-30

ኤልፋዝ

1ቴማናዊውም ኤልፋዝ እንዲህ ሲል መለሰ፤

2“ሰው እግዚአብሔርን ሊጠቅም ይችላልን?

ጠቢብ እንኳ ቢሆን ምን ይጠቅመዋል?

3አንተ ጻድቅ ብትሆን ሁሉን የሚችለውን አምላክ ምን ደስ ታሰኘዋለህ?

መንገድህ ያለ ነቀፋ ቢሆንስ የሚተርፈው ምንድን ነው?

4“እርሱ የሚገሥጽህ፣

ፍርድ ቤትም የሚያቀርብህ ስለምትፈራው ነውን?

5ክፋትህ ታላቅ፣

ኀጢአትህ ፍጻሜ የሌለው አይደለምን?

6ያለ አንዳች ምክንያት ከወንድሞችህ መያዣ ወስደሃል፤

ሰዎችን ገፍፈህ፣ ያለ ልብስ ዕራቍታቸውን አስቀርተሃል።

7የዛሉትን ውሃ አላጠጣህም፤

የተራቡትንም ምግብ ከልክለሃል።

8ባለ ርስትና ኀያል፣

በእርሱም የምትኖር ክቡር ሰው ብትሆንም፣

9መበለቶችን ባዶ እጃቸውን ሰድደሃል፤

የድኻ ዐደጎችንም ክንድ ሰብረሃል።

10ድንገተኛ አደጋ ያናወጠህ፣

ወጥመድም ዙሪያህን የከበበህ ለዚህ ነው።

11እንዳታይ ጨለማ የሆነብህ፣

ጐርፍም ያጥለቀለቀህ ለዚህ ነው።

12“እግዚአብሔር ከፍ ባለው ሰማይ የሚኖር አይደለምን?

በሩቅ ከፍታ ያሉትን ከዋክብት ያያል!

13ይህም ሆኖ ሳለ እንዲህ አልህ፤ ‘እግዚአብሔር ምን ያውቃል?

በእንዲህ ያለ ጨለማ ውስጥስ ይፈርዳልን?

14በሰማይ ክበብ ላይ ሲራመድ፣

እንዳያየን ጥቅጥቅ ያለ ደመና ይሸፍነዋል።’

15ኀጢአተኞች በሄዱባት፣

በጥንቷ መንገድ እንደ ተመላለስህ ትቀራለህን?

16ጊዜያቸው ሳይደርስ ተነጠቁ፤

መሠረታቸውም በጐርፍ ተወሰደ።

17እግዚአብሔርንም ‘አትድረስብን!

ሁሉን የሚችል አምላክም ምን ያደርግልናል?’ አሉ።

18ቤታቸውን በመልካም ነገር የሞላው ግን እርሱ ነው፤

ስለዚህ ከኀጢአተኞች ምድር እርቃለሁ።

19“ጻድቃንም የእነዚያን ጥፋት አይተው ይደሰታሉ፤

ንጹሓንም እንዲህ ብለው ያፌዙባቸዋል፤

20‘በርግጥ ጠላቶቻችን ጠፍተዋል፤

ሀብታቸውም በእሳት ተበልቷል።’

21“ለእግዚአብሔር ተገዛ፤ ከእርሱም ጋር ሰላም ይኑርህ፤

በረከትም ታገኛለህ።

22ምክርን ከአፉ ተቀበል፤

ቃሉንም በልብህ አኑር።

23ሁሉን ወደሚችል አምላክ ብትመለስ ትጠገናለህ፤

ክፋትን ከድንኳንህ ብታርቅ፣

24የወርቅህን አንኳር ትቢያ ላይ፣

የኦፊር ወርቅህንም ጥልቅ ሸለቆ ውስጥ ብትጥለው፣

25ሁሉን ቻዩ አምላክ ወርቅ ይሆንልሃል፤

ምርጥ ብር ይሆንልሃል።

26በዚያ ጊዜ ሁሉን በሚችል አምላክ ደስ ይልሃል፤

ፊትህንም ወደ እግዚአብሔር ታቀናለህ።

27ወደ እርሱ ትጸልያለህ፤ እርሱም ይሰማሃል፤

አንተም ስእለትህን ትሰጣለህ።

28ያሰብኸው ይከናወንልሃል፤

በመንገድህም ላይ ብርሃን ይበራል።

29ሰዎች ቢዋረዱና አንተ፣ ‘ከፍ አድርጋቸው’ ብትል፣

እርሱ ዝቅ ያሉትን ያድናል፤

30በጎ ያልሆነውን ሰው እንኳ፣

ከአንተ እጅ ንጽሕና የተነሣ ያድነዋል።”