ኢሳይያስ 1 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ኢሳይያስ 1:1-31

1በይሁዳ ነገሥታት በዖዝያን፣ በኢዮአታም፣ በአካዝና በሕዝቅያስ ዘመን፣ የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ስለ ይሁዳና ስለ ኢየሩሳሌም ያየው ራእይ፤

እንቢተኛ ሕዝብ

2ሰማያት ሆይ፤ ስሙ! ምድር ሆይ፤ አድምጪ!

እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ተናግሯልና፤

“ልጆች ወለድሁ፣ አሳደግኋቸውም፤

እነርሱ ግን ዐመፁብኝ።

3በሬ ጌታውን፣

አህያ የባለቤቱን ጋጥ ያውቃል፤

እስራኤል ግን አላወቀም፤

ሕዝቤም አላስተዋለም።”

4እናንተ ኀጢአተኛ ሕዝብ፣

በደል የሞላበት ወገን፣

የክፉ አድራጊ ዘር፣

ምግባረ ብልሹ ልጆች ወዮላችሁ!

እግዚአብሔርን ትተዋል፤

የእስራኤልን ቅዱስ አቃልለዋል፤

ጀርባቸውንም በእርሱ ላይ አዙረዋል።

5ለምን ዳግመኛ ትመታላችሁ?

ለምንስ በዐመፅ ትጸናላችሁ?

ራሳችሁ በሙሉ ታምሟል፤

ልባችሁ ሁሉ ታውኳል።

6ከእግር ጥፍራችሁ እስከ ራስ ጠጕራችሁ

ጤና የላችሁም፤

ቍስልና ዕባጭ እንዲሁም እዥ ብቻ ነው፤

አልታጠበም፤ አልታሰረም፤

በዘይትም አልለዘበም።

7አገራችሁ ባድማ፣

ከተሞቻችሁ በእሳት የተቃጠሉ ይሆናሉ፤

ዐይናችሁ እያየ፣

መሬታችሁ በባዕድ ይነጠቃል፤

ጠፍም ይሆናል።

8የጽዮን ሴት ልጅ

በወይን አትክልት ውስጥ እንዳለ ዳስ፣

በዱባ ተክል ወስጥ እንደሚገኝ ጐጆ፣

እንደ ተከበበም ከተማ ተተወች።

9የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር

ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ፣

እንደ ሰዶም በሆን፣

ገሞራንም በመሰልን ነበር።

10እናንተ የሰዶም ገዦች፤

የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤

እናንተ የገሞራ ሰዎች፤

የእግዚአብሔርን ሕግ አድምጡ።

11“የመሥዋዕታችሁ ብዛት

ለእኔ ምኔ ነው?” ይላል እግዚአብሔር

“የሚቃጠለውን የአውራ በግና

የሠቡ እንስሳትን ሥብ ጠግቤአለሁ፤

በበሬ፣ በበግ ጠቦትና በፍየል ደም ደስ

አልሰኝም።

12በፊቴ ለመቅረብ ስትመጡ፣

ይህን ሁሉ እንድታመጡ፣

የመቅደሴን ደጅ እንድትረግጡ ማን ጠየቃችሁ?

13ከንቱውን መባ አታቅርቡ፤

ዕጣናችሁን እጸየፋለሁ፤

የወር መባቻ በዓላችሁን፣

ሰንበቶቻችሁን፣ ጉባኤያችሁንና

በክፋት የተሞላውን ስብሰባችሁን መታገሥ

አልቻልሁም።

14የወር መባቻችሁንና የተደነገጉ በዓሎቻችሁን

ነፍሴ ጠልታለች፤

ሸክም ሆነውብኛል፤

መታገሥም አልቻልሁም።

15እጆቻቸሁን ለጸሎት ወደ እኔ ስትዘረጉ፣

ዐይኖቼን ከእናንተ እሰውራለሁ፤

አብዝታችሁ ብትጸልዩም እንኳ አልሰማችሁም፤

እጆቻችሁ በደም ተበክለዋል፤

16ታጠቡ፤ ራሳችሁንም አንጹ፤

ክፉ ሥራችሁን ከፊቴ አርቁ፤

ክፉ ማድረጋችሁን ተዉ፤

17መልካም ማድረግን ተማሩ፤

ፍትሕን እሹ፣

የተገፉትን አጽናኑ1፥17 ወይም፣ ጨቋኙን ገሥጹ ማለት ነው።

አባት ለሌላቸው ቁሙላቸው፤

ለመበለቶችም ተሟገቱ።

18“ኑና እንዋቀሥ”

ይላል እግዚአብሔር

“ኀጢአታችሁ እንደ ዐለላ ቢቀላ፣

እንደ በረዶ ይነጣል፤

እንደ ደም ቢቀላም፣

እንደ ባዘቶ ነጭ ይሆናል።

19እሺ ብትሉ፣ ብትታዘዙም

የምድርን በረከት ትበላላችሁ፤

20እንቢ ብላችሁ ብታምፁ ግን

ሰይፍ ይበላችኋል።”

የእግዚአብሔር አፍ ይህን ተናግሯልና።

21ታማኝ የነበረችው ከተማ

እንዴት አመንዝራ እንደ ሆነች ተመልከቱ፤

ቀድሞ ፍትሕ የሞላባት፣

ጽድቅ የሰፈነባት ነበረች፤

አሁን ግን የነፍሰ ገዳዮች ማደሪያ ሆነች

22ብርሽ ዝጓል፣

ምርጥ የወይን ጠጅሽ ውሃ ገባው፤

23ገዥዎችሽ ዐመፀኞችና

የሌባ ግብረ ዐበሮች ናቸው፤

ሁሉም ጕቦን ይወድዳሉ፤

እጅ መንሻንም በብርቱ ይፈልጋሉ፤

አባት ለሌላቸው አይቆሙም፤

የመበለቶችንም አቤቱታ አይሰሙም።

24ስለዚህ ጌታ፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር

የእስራኤል ኀያል እንዲህ ይላል፤

“በባላንጣዎቼ ላይ ቍጣዬን እገልጣለሁ፤

ጠላቶቼንም እበቀላለሁ።

25እጄን በአንቺ ላይ አነሣለሁ፤

ዝገትሽን ፈጽሜ አጠራለሁ፤

ጕድፍሽንም ሁሉ አስወግዳለሁ።

26ፈራጆችሽን እንደ ጥንቱ፣

አማካሪዎችሽንም እንደ ቀድሞው እመልሳለሁ፤

ከዚያም የጽድቅ መዲና፣

የታመነች ከተማ

ተብለሽ ትጠሪያለሽ።”

27ጽዮን በፍትሕ፣

በንስሓ የሚመለሱ ነዋሪዎቿም በጽድቅ ይዋጃሉ።

28ዐመፀኞችና ኀጢአተኞች ግን በአንድነት ይደቅቃሉ፤

እግዚአብሔርንም የሚተዉ ይጠፋሉ።

29“ደስ በተሰኛችሁባቸው የአድባር ዛፎች

ታፍራላችሁ፤

በመረጣችኋቸውም የአትክልት ቦታዎች

ትዋረዳላችሁ።

30ቅጠሉ እንደ ጠወለገ ወርካ፣

ውሃም እንደሌለው የአትክልት ቦታ ትሆናላችሁ።

31ብርቱ ሰው እንደ ገለባ፣

ሥራውም እንደ ብልጭታ ይሆናል፤

ሁለቱም አብረው ይቃጠላሉ፤

እሳቱንም የሚያጠፋው የለም።”