አብድዩ 1 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

አብድዩ 1:1-21

የአብድዩ ራእይ

1ጌታ እግዚአብሔር ስለ ኤዶም እንዲህ ይላል፤

ከእግዚአብሔር ዘንድ መልእክት ሰምተናል፤

መልእክተኛውም ወደ አሕዛብ ተልኮ እንዲህ

ብሏል፤

“ተነሡ፤ እርሷን ለመውጋት እንውጣ።”

2“እነሆ፤ በአሕዛብ መካከል ታናሽ አደርግሃለሁ፤

እጅግ የተናቅህ ትሆናለህ።

3አንተ በሰንጣቃ1፥3 ወይም በሴላ ዐለት ውስጥ

የምትኖር፣

መኖሪያህንም በከፍታ ስፍራ ያደረግህ፣

ለራስህም፣

‘ማን ወደ ምድር ሊያወርደኝ ይችላል?’ የምትል፣

የልብህ ትዕቢት አታልሎሃል።

4እንደ ንስር መጥቀህ ወደ ላይ ብትወጣ፣

ጐጆህንም በከዋክብት መካከል ብታደርግ፣

ከዚያ አወርድሃለሁ”

ይላል እግዚአብሔር

5“ሌቦች ወደ አንተ ቢመጡ፣

ዘራፊዎችም በሌሊት ቢገቡ፣

የሚሰርቁት የሚፈልጉትን ያህል ብቻ አይደለምን?

ወይን ለቃሚዎች ወደ አንተ ቢመጡ፣

ጥቂት ቃርሚያ አይተዉምን?

አንተ ግን ምንኛ ጥፋት ይጠብቅሃል!

6ዔሳው ግን እንዴት ተዘረፈ?

የሸሸገውስ ሀብት ምንኛ ተመዘበረ!

7ወዳጆችህ ሁሉ ወደ ድንበር ይገፉሃል፤

ጓደኞችህ ያታልሉሃል፤ ያሸንፉህማል፤

እንጀራህን የበሉ ወጥመድ ይዘረጉብሃል፤1፥7 የዚህ ሐረግ የዕብራይስጡ ትርጓሜ በርግጠኝነት አይታወቅም።

አንተ ግን አታውቀውም።

8“በዚያ ቀን ጥበበኛ ሰዎችን ከኤዶም፣

አስተዋዮችንም ከዔሳው ተራሮች አልደመስስምን?”

ይላል እግዚአብሔር

9“ቴማን ሆይ፤ ተዋጊዎችህ ይደነግጣሉ፤

በዔሳውም ተራሮች ያለ ሁሉ፣

ተገድሎ ይጠፋል።

10በወንድምህ በያዕቆብ ላይ ስላደረግኸው ግፍ፣

በዕፍረት ትሸፈናለህ፤

ለዘላለምም ትጠፋለህ።

11እንግዶች ሀብቱን ዘርፈው ሲሄዱ፣

ባዕዳንም በበሮቹ ሲገቡ፣

በኢየሩሳሌምም ላይ ዕጣ ሲጣጣሉ፣

በዚያ ቀን ገለልተኛ ሆነህ ተመለከትህ፣

አንተም ከእነርሱ እንደ አንዱ ሆንህ።

12ክፉ ቀን በገጠመው ጊዜ፤

በወንድምህ ሥቃይ መደሰት አልነበረብህም፤

በጥፋታቸው ቀን፣ የይሁዳ ሕዝብ ሲያዝኑ

ሐሤት ማድረግ አልነበረብህም፤

በጭንቀታቸውም ቀን፣

በትዕቢት ልትናገር አይገባህም ነበር።

13በጥፋታቸው ቀን፣

በሕዝቤ በር መግባት የለብህም ነበር፤

በጥፋታቸው ቀን፣

በጭንቀታቸው መደሰት አልነበረብህም፤

በጥፋታቸው ቀን፣

ሀብታቸውን መዝረፍ አይገባህም ነበር።

14ስደተኞቻቸውን ለመግደል፣

በመንታ መንገድ መጠባበቅ አይገባህም ነበር፣

በጭንቀታቸው ቀን፣

የተረፉትን አሳልፈህ መስጠት አልነበረብህም።

15“በአሕዛብ ሁሉ ላይ፣

የእግዚአብሔር ቀን ደርሷል፤

አንተ እንዳደረግኸው፣ በአንተም ላይ ይደረጋል፤

ክፉ ሥራህም በራስህ ላይ ይመለሳል።

16እናንተ በቅዱሱ ተራራዬ እንደ ጠጣችሁ፣

አሕዛብ ሁሉ ዘወትር ይጠጣሉ፤

ይጠጣሉ፤ አብዝተውም ይጠጣሉ፤

ከዚህም በፊት እንዳልሆኑት ይሆናሉ።

17ነገር ግን በጽዮን ተራራ ነጻ መውጣት ይሆናል፤

የያዕቆብ ቤትም እርሷ የተቀደሰች ትሆናለች፤

ርስታቸውን ይወርሳሉ።

18የያዕቆብ ቤት እሳት፣

የዮሴፍም ቤት ነበልባል ይሆናል፤

የዔሳው ቤት ገለባ ይሆናል፤

ያቃጥሉታል፤ ይበሉትማል፤

ከዔሳው ቤት የሚተርፍ አይኖርም።”

እግዚአብሔር ተናግሯል።

19የኔጌብ ሰዎች፣

የዔሳውን ተራራ ይይዛሉ፤

ከተራራው ግርጌ ያሉ ሰዎችም፣

የፍልስጥኤማውያንን ምድር ይወርሳሉ፤

የኤፍሬምንና የሰማርያንም ዕርሻ ይይዛሉ፤

ብንያምም ገለዓድን ይወርሳል።

20በከነዓን ያለው ይህ የእስራኤል ስደተኞች ወገን፣

እስከ ሰራጵታ ያለውን ምድር ይወርሳል፤

በሰፋራድም ያሉ የኢየሩሳሌም ስደተኞች፣

የኔጌብን ከተሞች ይወርሳሉ።

21የዔሳውን ተራሮች ለመግዛት፣

ነጻ አውጪዎች ወደ ጽዮን ተራራ ይወጣሉ፤

መንግሥቱም የእግዚአብሔር ይሆናል።