ነህምያ 1 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ነህምያ 1:1-11

የነህምያ ጸሎት

1የሐካልያ ልጅ የነህምያ ቃል፤

በሃያኛው ዓመት ካሴሉ በተባለው ወር በሱሳ ግንብ ሳለሁ፣ 2ከወንድሞቼ አንዱ የሆነው አናኒ፣ ከሌሎች ጥቂት ሰዎች ጋር ከይሁዳ መጣ፤ እኔም ከምርኮ ስለ ተረፉት የአይሁድ ቅሬታዎችና ስለ ኢየሩሳሌም ጠየቅኋቸው።

3እነርሱም፣ “በሕይወት ተርፈው ከምርኮ ወደ አገራቸው የተመለሱት ሰዎች በታላቅ መከራና ውርደት ላይ ይገኛሉ፤ የኢየሩሳሌም ቅጥር ፈራርሷል፤ በሮቿም በእሳት ተቃጥለዋል” አሉኝ።

4ይህን ነገር በሰማሁ ጊዜ አያሌ ቀናት ዐዘንሁ፤ ጾምሁ፤ ጸለይሁም። 5ከዚያም እንዲህ አልሁ፤

“ለሚወድዱህና ትእዛዝህን ለሚያከብሩ የፍቅርህን ቃል ኪዳን የምትጠብቅ ታላቅና የተፈራህ አምላክ፣ የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ 6ባሪያህ ስለ አገልጋዮችህ ስለ እስራኤል ሕዝብ ቀንና ሌሊት በፊትህ የሚጸልየውን ጸሎት ለመስማት ጆሮህ ይንቃ፤ ዐይንህም ይከፈት። እኔንና የአባቴን ቤት ጨምሮ እኛ እስራኤላውያን አንተን በመበደል የሠራነውን ኀጢአት እናዘዛለሁ። 7በአንተ ላይ እጅግ ክፉ ሥራ ሠርተናል፤ ለባሪያህም ለሙሴ የሰጠኸውን ትእዛዝ፣ ሥርዐትና ሕግ አልጠበቅንም።

8“ለባሪያህ ለሙሴ እንዲህ ስትል የሰጠኸውን ቃል ዐስብ፤ ‘ታማኞች ካልሆናችሁ፣ በአሕዛብ መካከል እበትናችኋለሁ፤ 9ወደ እኔ ብትመለሱና ትእዛዞቼን ብትፈጽሙ፣ የተሰደዱት ወገኖቻችሁ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ እንኳ ቢበተኑ፣ ከዚያ እሰበስባቸዋለሁ፤ ለስሜም ማደሪያ ወደ መረጥሁት ስፍራ አመጣቸዋለሁ።’

10“እነዚህም በታላቁ ኀይልህና በብርቱ እጅህ የተቤዠሃቸው ባሪያዎችህና ሕዝብህ ናቸው። 11ጌታ ሆይ፤ የባሪያህን ጸሎት፣ ስምህን በመፍራት ደስ የሚሰኙትን የባሪያዎችህንም ጸሎት ጆሮህ ታድምጥ። በዚህ ሰው ፊት ሞገስን አድርገህለት ዛሬ ለባሪያህ መከናወንን ስጠው።”

በዚያን ጊዜ እኔ የንጉሡ ጠጅ አሳላፊ ነበርሁ።