ቈላስይስ 1 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ቈላስይስ 1:1-29

1በእግዚአብሔር ፈቃድ የክርስቶስ ኢየሱስ ሐዋርያ ከሆነው ከጳውሎስና ከወንድማችን ከጢሞቴዎስ፤

2በቈላስይስ ለሚኖሩ፣ በክርስቶስ ለሆኑ ቅዱሳንና ታማኝ1፥2 ወይም የሚያምኑ ወንድሞች፤

ከእግዚአብሔር ከአባታችን1፥2 አንዳንድ የጥንት ቅጆች ከአባትና ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።

ምስጋናና ጸሎት

3ስለ እናንተ በምንጸልይበት ጊዜ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን አባት እግዚአብሔርን ሁልጊዜ እናመሰግናለን፤ 4ምክንያቱም በክርስቶስ ኢየሱስ ስላላችሁ እምነትና ለቅዱሳን ሁሉ ስላላችሁ ፍቅር ሰምተናል፤ 5ይህም የሆነው በሰማይ ተዘጋጅቶ ከተቀመጠላችሁ ተስፋ የተነሣ ነው፤ ስለዚህ ተስፋ በወንጌል የእውነት ቃል አስቀድማችሁ ሰማችሁ፤ 6ይህም ወደ እናንተ ደርሷል። ይህንም ወንጌል ከሰማችሁበትና የእግዚአብሔርን ጸጋ በእውነት ከተረዳችሁበት ቀን ጀምሮ በዓለም ዙሪያ እየሠራ እንዳለ ሁሉ በእናንተም ዘንድ ፍሬ እያፈራና እያደገ ነው። 7ይህንም ስለ እኛ1፥7 አንዳንድ የጥንት ቅጆች እናንተ ይላሉ። የክርስቶስ ታማኝ አገልጋይ የሆነው፣ አብሮንም በአገልግሎት የተጠመደው ተወዳጁ ኤጳፍራ አስተማራችሁ፤ 8ደግሞም በመንፈስ ስላላችሁ ፍቅር ነገረን።

9ከዚህ የተነሣ እኛ ደግሞ ይህን ከሰማንበት ቀን ጀምሮ እግዚአብሔር የፈቃዱን ዕውቀት በመንፈሳዊ ጥበብና መረዳት ሁሉ ይሞላችሁ ዘንድ ስለ እናንተ መጸለይና መለመን አላቋረጥንም፤ 10የምንጸልየውም ለጌታ እንደሚገባ እንድትኖሩና በሁሉም ደስ እንድታሰኙት ነው፤ ይኸውም በመልካም ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁ እግዚአብሔርን በማወቅ እያደጋችሁ፣ 11ታላቅ ጽናትና ትዕግሥት ይኖራችሁ ዘንድ፣ እንደ ክቡር ጕልበቱ መጠን በኀይል ሁሉ እየበረታችሁ፣ ደስ እየተሰኛችሁ፣ 12በቅዱሳን ርስት በብርሃን ተካፋዮች ለመሆን ያበቃንን1፥12 ወይም ያበቃችሁን አብን እንድታመሰግኑ ነው። 13እርሱ ከጨለማ አገዛዝ ታደገን፤ ወደሚወድደው ልጁ መንግሥትም አሻገረን፤ 14በእርሱም መዋጀትን በደሙ1፥14 አንዳንድ ቅጆች በደሙ የሚለው ቃል የላቸውም። አግኝተናል፤ ይህም የኀጢአት ይቅርታ ነው።

ክርስቶስ ከሁሉ በላይ

15እርሱ የማይታየው አምላክ አምሳል ነው፤ ከፍጥረት ሁሉ በፊት1፥15 ወይም በላይ በኵር ነው፤ 16ሁሉ ነገር በእርሱ ተፈጥሯል፤ በሰማይና በምድር ያሉ፣ የሚታዩና የማይታዩ፣ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ኀይላት፣ ገዦች ቢሆኑ ወይም ባለሥልጣናት፣ ሁሉም ነገር በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሯል። 17እርሱ ከሁሉ በፊት ነው፤ ሁሉም ነገር በአንድ ላይ ተያይዞ የጸናው በእርሱ ነው። 18እርሱ አካሉ የሆነችው የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው፤ በሁሉ ነገር የበላይነት ይኖረው ዘንድ እርሱ የመጀመሪያ፣ ከሙታን መካከልም በኵር ነው። 19እግዚአብሔርም ሙላቱ ሁሉ በእርሱ ይሆን ዘንድ ወድዷልና፤ 20በመስቀሉ ላይ በፈሰሰው ደሙ ሰላምን በማድረግ በምድርም ሆነ በሰማይ ያለውን ነገር ሁሉ በእርሱ በኩል ከራሱ ጋር አስታረቀ።

21ከክፉ ባሕርያችሁ የተነሣ1፥21 ወይም በክፉ ባሕርያችሁ እንደሚታየው ቀድሞ ከእግዚአብሔር የተለያችሁ በዐሳባችሁም ጠላቶች ነበራችሁ። 22አሁን ግን ነውርና ነቀፋ የሌለባችሁ ቅዱሳን አድርጎ በእርሱ ፊት ሊያቀርባችሁ፣ በክርስቶስ ሥጋ በሞቱ በኩል አስታረቃችሁ፤ 23ይህም የሚሆነው በእምነታችሁ ተመሥርታችሁና ተደላድላችሁ በመቆም ከሰማችሁት የወንጌል ተስፋ ሳትናወጡ ጸንታችሁ ብትኖሩ ነው። እናንተ የሰማችሁትና ከሰማይ በታች ላለ ፍጥረት ሁሉ የተሰበከውም ወንጌል ይኸው ነው፤ እኔም ጳውሎስ ለዚህ ወንጌል አገልጋይ ሆንሁ።

ጳውሎስ ስለ ቤተ ክርስቲያን ያሳየው ትጋት

24ስለ እናንተ በተቀበልሁት መከራ አሁንም ደስ ይለኛል፤ ክርስቶስ ስለ አካሉ ስለ ቤተ ክርስቲያን ከተቀበለው መከራ የጐደለውን በሥጋዬ አሟላለሁ። 25የእግዚአብሔርን ቃል በሙላት እንዳቀርብላችሁ ከእግዚአብሔር በተሰጠኝ ዐደራ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ሆኛለሁ፤ 26ይህም ቃል ከዘመናትና ከትውልዶች ተሰውሮ ምስጢር ሆኖ ቈይቶ ነበር፤ አሁን ግን ለቅዱሳኑ ተገልጧል። 27ለእነርሱም እግዚአብሔር የዚህ ምስጢር ክብር ባለጠግነት በአሕዛብ መካከል ምን ያህል እንደ ሆነ ለማሳወቅ መረጠ፤ እርሱም የክብር ተስፋ የሆነው በእናንተ ውስጥ ያለው ክርስቶስ ነው።

28እኛም እያንዳንዱን ሰው በክርስቶስ ፍጹም አድርገን ማቅረብ እንችል ዘንድ፣ ሰውን ሁሉ በጥበብ ሁሉ እየመከርንና እያስተማርን እርሱን እንሰብካለን። 29እኔም በብርታት በውስጤ በሚሠራው በእርሱ ኀይል ሁሉ እየታገልሁ ለዚህ ዐላማ እጥራለሁ።