ሮሜ 1 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ሮሜ 1:1-32

1ጳውሎስ፣ የክርስቶስ ኢየሱስ ባሪያ፣ ሐዋርያ ሊሆን የተጠራና ለእግዚአብሔር ወንጌል የተለየ፤ 2ስለዚህ ወንጌል በነቢያቱ በኩል በቅዱሳት መጻሕፍት አስቀድሞ ተስፋ ተሰጠ። 3ወንጌሉም ስለ ልጁ፣ በሥጋ ከዳዊት ዘር ስለሆነ፣ 4በቅድስና መንፈስ1፥4 ወይም በቅድስናው መንፈስ ደግሞ ከሙታን በመነሣቱ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑ በኀይል ስለ ተገለጠው ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። 5በእርሱ በኩል ስለ ስሙ ከአሕዛብ ሁሉ መካከል ሰዎችን በእምነት አማካይነት ወደሚገኘው መታዘዝ ለመጥራት ጸጋንና ሐዋርያነትን ተቀበልን። 6እናንተ ራሳችሁም ለኢየሱስ ክርስቶስ እንዲሆኑ ከተጠሩት መካከል ናችሁ።

7በእግዚአብሔር ለተወደዳችሁና ቅዱሳን ለመሆን ለተጠራችሁ በሮም ላላችሁ ሁሉ፤

ከአባታችን ከእግዚአብሔር፣ ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።

ሮምን ለማየት የጳውሎስ ናፍቆት

8ከሁሉ አስቀድሜ፣ እምነታችሁ በዓለም ሁሉ በመሰማቱ፣ ስለ ሁላችሁ አምላኬን በኢየሱስ ክርስቶስ አመሰግናለሁ። 9ዘወትር ምን ያህል እንደማስባችሁ፣ የልጁን ወንጌል በመስበክ በሙሉ ልቤ የማገለግለው እግዚአብሔር ምስክሬ ነው፤ 10በጸሎቴ ሁልጊዜ አስባችኋለሁ፤ አሁን ደግሞ በመጨረሻ በእግዚአብሔር ፈቃድ ወደ እናንተ እንድመጣ መንገድ ይከፈትልኝ ዘንድ እጸልያለሁ።

11እንድትጸኑ የሚያስችላችሁን መንፈሳዊ ስጦታ አካፍላችሁ ዘንድ፣ ላያችሁ እናፍቃለሁ። 12ይኸውም እናንተና እኔ በእያንዳንዳችን እምነት እርስ በርሳችን እንድንበረታታ ነው። 13ወንድሞች ሆይ፤ በሌሎች አሕዛብ ዘንድ እንደ ሆነልኝ፣ በእናንተም ዘንድ ፍሬ ለማግኘት ብዙ ጊዜ ወደ እናንተ ልመጣ ዐቅጄ ሳለሁ፣ እስከ አሁን ድረስ ግን መከልከሌን እንድታውቁ እወድዳለሁ።

14ግሪኮች ለሆኑትና ላልሆኑት፣ ለጥበበኞችና ለማያስተውሉ ዕዳ አለብኝ፤ 15በሮም ለምትኖሩ፣ ለእናንተም ወንጌልን ለመስበክ የምጓጓው ለዚህ ነው።

16በወንጌል አላፍርም፤ ምክንያቱም ለሚያምን ሁሉ ለድነት የሚሆን የእግዚአብሔር ኀይል ነው፤ ይህም በመጀመሪያ ለአይሁድ፣ ቀጥሎም ለአሕዛብ ነው። 17በወንጌል የእግዚአብሔር ጽድቅ ተገልጧልና፤ ጽድቁም ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ በእምነት1፥17 ወይም ከእምነት ወደ እምነት የሆነ ነው፣ “ጻድቅ በእምነት ይኖራል” ተብሎ እንደ ተጻፈው።

የእግዚአብሔር ቍጣ በሰዎች ላይ

18በክፋታቸው እውነትን ዐፍነው በሚይዙ፣ በዐመፃቸውና በክፋታቸው ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ቍጣ ከሰማይ ይገለጣል፤ 19ስለ እግዚአብሔር ሊታወቅ የሚቻለው ለእነርሱ ግልጽ ነው፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ለእነርሱ ግልጽ አድርጎታል። 20ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የማይታየው የእግዚአብሔር ባሕርይ፣ ይኸውም ዘላለማዊ ኀይሉና መለኮትነቱ፣ ከፍጥረቱ በግልጽ ይታያል፤ ስለዚህ ሰዎች ማመካኛ የላቸውም።

21እግዚአብሔርን ቢያውቁም እንኳ፣ እንደ አምላክነቱ አላከበሩትም፤ ምስጋናም አላቀረቡለትም፤ ነገር ግን ሐሳባቸው ፍሬ ቢስ ሆነ፤ የማያስተውል ልባቸው ጨለመ። 22ጥበበኞች ነን ቢሉም፣ ሞኞች ሆኑ፤ 23የዘላለም አምላክን ክብር ምዉት በሆነው ሰው፣ በወፎች፣ በእንስሳትና በምድር ላይ በሚሳቡ ፍጥረት መልክ መስለው ለወጡ።

24ስለዚህም እግዚአብሔር በኀጢአት በተሞላው የልባቸው ምኞት እርስ በርሳቸው የገዛ አካላቸውን እንዲያስነውሩ ቅድስና ለሌለው ሩካቤ ሥጋ አሳልፎ ሰጣቸው። 25የእግዚአብሔርን እውነት በሐሰት ለወጡ፤ በፈጣሪ ፈንታ ፍጡር አመለኩ፤ አገለገሉም፤ ፈጣሪም ለዘላለም የተመሰገነ ነው፤ አሜን።

26በዚህም ምክንያት እግዚአብሔር አሳፋሪ ለሆነ ምኞት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ሴቶቻቸውም እንኳ ለባሕርያቸው የሚገባውን ግንኙነት ባሕርያቸው ላልሆነው ግንኙነት ለወጡ። 27እንደዚሁም ወንዶች ለባሕርያቸው የሚገባውን ሴቶችን መገናኘት ትተው እርስ በርሳቸው በፍትወት ተቃጠሉ፤ ወንዶች ከወንዶች ጋር ነውር ፈጸሙ፤ ለክፉ አድራጎታቸውም የሚገባቸውን ቅጣት በገዛ ራሳቸው ላይ አመጡ።

28ከዚህም በላይ በሐሳባቸው እግዚአብሔርን ማወቅ አይጠቅምም በማለታቸው፣ መደረግ የማይገባውን እንዲያደርጉ እግዚአብሔር ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው። 29በሁሉም ዐይነት ዐመፃ፣ ክፋት፣ ስግብግብነትና ምግባረ ብልሹነት ተሞልተዋል፤ ቅናትን፣ ነፍስ ገዳይነትን፣ ጥልን፣ አታላይነትንና ተንኰልን የተሞሉ ናቸው፤ ሐሜተኞች፣ 30ስም አጥፊዎች፣ አምላክን የሚጠሉ፣ ተሳዳቢዎች፣ ትዕቢተኞችና ትምክሕተኞች ናቸው፤ ክፋትን የሚሠሩበትን መንገድ ያውጠነጥናሉ፤ ለወላጆቻቸው አይታዘዙም። 31የማያስተውሉ፣ ውል የሚያፈርሱ፣ ርኅራኄ የሌላቸውና ጨካኞች ናቸው። 32ይህን የሚያደርጉ ሁሉ ሞት ይገባቸዋል የሚለውን ትክክለኛ የሆነውን የእግዚአብሔርን ሕግ ቢያውቁም፣ እነዚህን ነገሮች ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ እንዲህ የሚያደርጉትንም ያበረታታሉ።