ራእይ 21 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ራእይ 21:1-27

አዲሲቱ ኢየሩሳሌም

1ከዚህ በኋላ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር አየሁ፤ የመጀመሪያው ሰማይና የመጀመሪያዪቱ ምድር ዐልፈዋልና፤ ባሕርም ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። 2ቅድስቲቱ ከተማ፣ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ለባሏ እንደ ተዋበች ሙሽራ ተዘጋጅታ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ። 3ደግሞም እንዲህ የሚል ታላቅ ድምፅ ከዙፋኑ ሲወጣ ሰማሁ፤ “እነሆ፤ የእግዚአብሔር ማደሪያ በሰዎች መካከል ነው፤ እርሱ ከእነርሱ ጋር ይኖራል፤ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ፤ እግዚአብሔር ራሱም ከእነርሱ ጋር ይኖራል፤ አምላካቸውም ይሆናል። 4እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ወይም ሐዘን ወይም ልቅሶ ወይም ሥቃይ አይኖርም፤ የቀድሞው ሥርዐት ዐልፏልና።”

5በዙፋኑ ላይ የተቀመጠውም፣ “እነሆ፤ እኔ ሁሉን ነገር አዲስ አደርጋለሁ” አለ፤ ደግሞም፣ “ይህ ቃል የታመነና እውነት ስለሆነ ጻፍ” አለ።

6እንዲህም አለኝ፤ “ተፈጸመ፤ አልፋና ዖሜጋ፣ የመጀመሪያውና የመጨረሻው እኔ ነኝ፤ ለተጠማ ከሕይወት ውሃ ምንጭ ያለ ዋጋ እሰጣለሁ። 7ድል የሚነሣ ይህን ሁሉ ይወርሳል፤ እኔም አምላክ እሆነዋለሁ፤ እርሱም ልጅ ይሆነኛል። 8ነገር ግን ፈሪዎች፣ የማያምኑ፣ ርኩሶች፣ ነፍሰ ገዳዮች፣ አመንዝሮች፣ አስማተኞች፣ ጣዖት አምላኪዎች፣ ውሸተኞች ሁሉ ዕጣ ፈንታቸው በዲንና በእሳት ባሕር ውስጥ መጣል ይሆናል። ይህም ሁለተኛው ሞት ነው።”

9ሰባቱ የመጨረሻ መቅሠፍቶች የሞሉባቸውን ሰባቱን ጽዋዎች ከያዙት ከሰባቱ መላእክት አንዱ መጥቶ፣ “ና፤ የበጉ ሚስት የሆነችውን ሙሽራ አሳይሃለሁ” አለኝ። 10በመንፈስም ወደ አንድ ትልቅና ረዥም ተራራ ወስዶኝ፣ ቅድስቲቱ ከተማ ኢየሩሳሌም ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አሳየኝ። 11እርሷም በእግዚአብሔር ክብር ታበራ ነበር፤ የብርሃኗም ድምቀት እጅግ እንደ ከበረ ድንጋይ እንደ ኢያሰጲድ፣ እንደ መስተዋት የጠራ ነበር። 12ዐሥራ ሁለት በሮች የነበሩት ትልቅና ረዥም ቅጥርም ነበራት፤ በበሮቹም ላይ ዐሥራ ሁለት መላእክት ቆመውና የዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ስም ተጽፎ ነበር። 13በምሥራቅ ሦስት በሮች፣ በሰሜን ሦስት በሮች፣ በደቡብ ሦስት በሮች፣ በምዕራብ ሦስት በሮች ነበሩ። 14የከተማዪቱም ቅጥር ዐሥራ ሁለት መሠረቶች ነበሩት፤ በእነርሱም ላይ የዐሥራ ሁለቱ የበጉ ሐዋርያት ስሞች ተጽፈው ነበር።

15ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክ የከተማዪቱን በሮች ቅጥር የሚለካበት የወርቅ ዘንግ ነበረው። 16ከተማዪቱም ርዝመቷና ስፋቷ እኩል ሆኖ አራት ማእዘን ነበረች። እርሱም ከተማዪቱን በዘንጉ ለካ፤ ርዝመቷም ዐሥራ ሁለት ሺሕ ምዕራፍ21፥16 ሁለት ሺሕ ሁለት መቶ ኪሎ ሜትር ያህል ይሆናል። ሆነ፤ ስፋቷና ከፍታዋም እንዲሁ ሆነ። 17ደግሞም የከተማዪቱን ቅጥር ለካ፤ ርዝመቱም የመልአክ መለኪያ በሆነው በሰው መለኪያ መቶ አርባ አራት ክንድ21፥17 ስድሳ አምስት ሜትር ያህል ይሆናል። ነበር። 18ቅጥሩ የተሠራው ከኢያሰጲድ ነበር፤ ከተማዪቱም እንደ መስተዋት ንጹሕ ከሆነ ወርቅ የተሠራች ነበረች። 19የከተማዪቱ ቅጥር መሠረቶች በሁሉም ዐይነት የከበረ ድንጋይ ያጌጡ ነበር፤ የመጀመሪያው መሠረት ኢያሰጲድ፣ ሁለተኛው ሰንፔር፣ ሦስተኛው ኬልቄዶን፣ አራተኛው መረግድ፣ 20አምስተኛው ሰርዶንክስ፣ ስድስተኛው ሰርድዮን፣ ሰባተኛው ክርስቲሎቤ፣ ስምንተኛው ቢረሌ፣ ዘጠነኛው ወራውሬ፣ ዐሥረኛው ክርስጵራስስ፣ ዐሥራ አንደኛው ያክንት፣ ዐሥራ ሁለተኛው አሜቴስጢኖስ21፥20 ከእነዚህ የከበሩ ድንጋዮች መካከል የአንዳንዶቹ ምንነት በውል አይታወቅም። ነበረ። 21ዐሥራ ሁለቱም በሮች ዐሥራ ሁለት ዕንቍዎች ነበሩ፤ እያንዳንዱም በር ከአንድ ዕንየተሠራ ነበረ። የከተማዪቱም አውራ መንገድ እንደ መስተዋት ብርሃን የሚያስተላልፍ ንጹሕ ወርቅ ነበረ።

22ሁሉን ቻይ ጌታ አምላክና በጉ መቅደሷ ስለሆኑ፣ በከተማዪቱ ውስጥ ቤተ መቅደስ አላየሁም። 23የእግዚአብሔር ክብር ብርሃን ስለሚሰጣትና በጉም መብራቷ ስለሆነ፣ ከተማዋ ፀሓይ ወይም ጨረቃ እንዲያበሩላት አያስፈልጋትም። 24ሕዝቦች በብርሃኗ ይመላለሳሉ፤ የምድር ነገሥታትም ክብራቸውን ወደ እርሷ ያመጣሉ። 25በዚያ ሌሊት ስለሌለ፣ በሮቿ በየትኛውም ቀን አይዘጉም። 26የሕዝቦች ግርማና ክብር ወደ እርሷ ይገባል። 27በበጉ የሕይወት መጽሐፍ ከተጻፉት በስተቀር፣ ርኩሰትን የሚያደርግና ውሸትን የሚናገር ሁሉ አይገባባትም።