ራእይ 13 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ራእይ 13:1-18

1ዘንዶውም13፥1 አንዳንድ የጥንት ቅጆች እኔም በባሕሩ ዳር ቆሜ ነበር ይላሉ። በባሕሩ ዳር ቆሞ ነበር።

ከባሕር የወጣው አውሬ

ከዚያም አንድ አውሬ ከባሕር ሲወጣ አየሁ፤ እርሱም ዐሥር ቀንዶችና ሰባት ራሶች ነበሩት፤ በቀንዶቹም ላይ ዐሥር ዘውዶች፣ በራሶቹም ላይ የስድብ ስሞች ነበሩት። 2ያየሁትም አውሬ ነብር ይመስል ነበር፤ ነገር ግን እግሮቹ የድብ፣ አፉ ደግሞ የአንበሳ አፍ ይመስል ነበር፤ ዘንዶው የራሱን ኀይልና የራሱን ዙፋን እንዲሁም ታላቅ ሥልጣን ለአውሬው ሰጠው። 3ከአውሬው ራሶች አንዱ ለሞት የሚያደርስ ቍስል ያለበት ይመስል ነበር። ነገር ግን ለሞት የሚያደርሰው ቍስሉ ዳነ፤ ዓለም በሙሉ በመደነቅ አውሬውን ተከተለው። 4ሰዎችም ለዘንዶው ሰገዱለት፤ ምክንያቱም ሥልጣኑን ለአውሬው ሰጥቶታል። ደግሞም፣ “አውሬውን የሚመስል ማን ነው? ከእርሱስ ጋር ማን ሊዋጋ ይችላል?” በማለት ለአውሬው ሰገዱለት።

5አውሬው የትዕቢት ቃል የሚናገርበትና የሚሳደብበት አፍ ተሰጠው፤ አርባ ሁለት ወር በሥልጣን እንዲሠራም ተፈቀደለት። 6እርሱም እግዚአብሔርን ለመሳደብ እንዲሁም ስሙንና ማደሪያውን፣ በሰማይም የሚኖሩትን ለመሳደብ አፉን ከፈተ። 7ቅዱሳንን እንዲዋጋና ድልም እንዲነሣቸው ኀይል ተሰጠው። በነገድ፣ በወገን፣ በቋንቋና በሕዝብም ሁሉ ላይ ሥልጣን ተሰጠው። 8ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ13፥8 ወይም ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ስሞቻቸው በታረደው በግ የሕይወት መጽሐፍ ውስጥ የተጻፈው በታረደው በግ የሕይወት መጽሐፍ ላይ ስሞቻቸው ያልተጻፈ የምድር ሰዎች ሁሉ ለአውሬው ይሰግዳሉ።

9ጆሮ ያለው ቢኖር ይስማ።

10ማንም የሚማረክ ቢኖር፣

እርሱ ይማረካል፤

ማንም በሰይፍ የሚገደል13፥10 አንዳንድ የጥንት ቅጆች የሚገድል ይላሉ። ቢኖር፣

እርሱ በሰይፍ ይገደላል።

ይህም የቅዱሳን ትዕግሥትና እምነት የሚታየው በዚህ እንደ ሆነ ያስገነዝባል።

ከምድር የወጣው አውሬ

11ከዚያም ሌላ አውሬ ከምድር ሲወጣ አየሁ፤ እርሱም እንደ በግ ሁለት ቀንዶች ነበሩት፤ ነገር ግን እንደ ዘንዶ ይናገር ነበር። 12በመጀመሪያው አውሬ ስም በሙሉ ሥልጣን ይሠራ ነበር፤ ምድርና በእርሷም የሚኖሩ ሁሉ፣ ለሞት ከሚያደርሰው ቍስል የዳነውን የመጀመሪያውን አውሬ እንዲያመልኩ አደረገ። 13በሰዎቹም ፊት እሳት ከሰማይ ወደ ምድር እስኪያወርድ ድረስ ታላላቅ ምልክቶችን አደረገ። 14በመጀመሪያው አውሬ ስም ምልክቶችን እንዲያደርግ ሥልጣን ስለ ተሰጠው፣ በምድር የሚኖሩ ሰዎችን አሳተ፤ በሰይፍ ቈስሎ ለነበረው፣ ነገር ግን በሕይወት ለሚኖረው አውሬ ምስል እንዲያቆሙም አዘዛቸው። 15ደግሞም የመጀመሪያው አውሬ ምስል መናገር እንዲችል ለምስሉ እስትንፋስ ለመስጠትና ለዚህም ምስል የማይሰግዱ ሁሉ እንዲገደሉ ለማድረግ ሥልጣን ተሰጠው። 16እንዲሁም ታናናሾችና ታላላቆች፣ ሀብታሞችና ድኾች፣ ጌቶችና ባሮች ሁሉ በቀኝ እጃቸው ወይም በግንባራቸው ላይ ምልክት እንዲቀበሉ አስገደዳቸው፤ 17ይህም የሆነው የአውሬው ምልክት፣ ይኸውም ስሙ ወይም የስሙ ቍጥር የሌለው ማንም ሰው ለመግዛትም ሆነ ለመሸጥ እንዳይችል ነው።

18ይህ ጥበብ ይጠይቃል፤ አእምሮ ያለው ማንኛውም ሰው የአውሬውን ቍጥር ያስላው፤ ምክንያቱም ቍጥሩ የሰው ቍጥር ነው። ቍጥሩ ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት ነው።