ምሳሌ 30 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ምሳሌ 30:1-33

አጉር የተናገራቸው ምሳሌዎች

1የያቄ ልጅ የአጉር ቃል ይህ ነው፤30፥1 ወይም የማሳው ያቄ

ይህ ሰው ለኢቲኤል፣

ለኢቲኤልና ለኡካል ተናገረ፤30፥1 የማስሬቲክ ጽሑፍ ከዚህ ጋር ይስማማል፤ የዕብራይስጡ ግን ተናገረ፤ አቤቱ እግዚአብሔር፤ እኔ ደክሜአለሁ፣ ነገር ግን እጸናለሁ ይላል።

2“እኔ ከሰው ሁሉ ይልቅ ጅል ነኝ፤

ሰው ያለው ማስተዋል የለኝም።

3ጥበብን አልተማርሁም፤

ስለ ቅዱሱም ዕውቀት የለኝም።

4ወደ ሰማይ የወጣ፣ የወረደስ ማነው?

ነፋስን በእጁ ሰብስቦ የያዘ ማነው?

ውሆችንስ በመጐናጸፊያው የጠቀለለ ማነው?

የምድርን ዳርቻዎች ሁሉ የወሰነ ማነው?

ስሙ ማን ነው? የልጁስ ስም ማን ይባላል?

የምታውቅ ከሆነ እስቲ ንገረኝ!

5“የእግዚአብሔር ቃል ሁሉ እንከን የለበትም፤

እርሱ ለሚታመኑበት ሁሉ ጋሻቸው ነው።

6በእርሱ ቃል ላይ አንዳች አትጨምር፤

አለዚያ ይዘልፍሃል፤ ሐሰተኛም ያደርግሃል።

7እግዚአብሔር ሆይ፤ ሁለት ነገር እለምንሃለሁ፤

እነዚህንም ከመሞቴ በፊት አትከልክለኝ፤

8ሐሰትንና ሐሰት መናገርን ከእኔ አርቅልኝ፤

ድኽነትንም ሆነ ብልጽግናን አትስጠኝ፤

ብቻ የዕለት እንጀራዬን ስጠኝ።

9አለዚያ ግን ያለ ልክ እጠግብና እክድሃለሁ፤

እግዚአብሔር ማን ነው?’ እላለሁ፤

ወይም ድኻ እሆንና እሰርቃለሁ፤

የአምላኬንም ስም አሰድባለሁ።

10“አገልጋይን በጌታው ፊት በክፉ አታንሣው፤

አለዚያ ይረግምህና ጕዳት ያገኝሃል።

11“አባቱን የሚረግም፣

እናቱን የማይባርክ ትውልድ አለ፤

12ራሳቸውን ንጹሓን አድርገው የሚቈጥሩ፣

ሆኖም ከርኩሰታቸው ያልነጹ አሉ፤

13ዐይናቸው ትዕቢተኛ የሆነ፣ አስተያያቸው ንቀት የሞላበት፣

14ድኾችን ከምድር፣

ችግረኞችንም ከሰው ዘር መካከል ለማጥፋት፣

ጥርሳቸው ሰይፍ የሆነ፣

መንጋጋቸውም ካራ የሆነ አሉ።

15“አልቅት ሁለት ሴት ልጆች አሉት፤

‘ስጡን! ስጡን!’ እያሉ ይጮኻሉ፤

“ፈጽሞ የማይጠግቡ ሦስት ነገሮች አሉ፤

‘በቃኝን’ ከቶ የማያውቁ አራት ናቸው፤

16እነርሱም መቃብር፣30፥16 ዕብራይስጡ ሲኦል ይላል። መካን ማሕፀን፣

ውሃ ጠጥታ የማትረካ ምድር፣

‘በቃኝ’ የማይል እሳት ናቸው።

17“በአባት ላይ የምታፌዝ ዐይን፣

የእናትንም ትእዛዝ የምትንቅ፣

የሸለቆ ቍራዎች ይጐጠጕጧታል፤

ጆፌ አሞሮችም ይበሏታል።

18“እጅግ የሚያስደንቁኝ ሦስት ነገሮች አሉ፤

የማላስተውላቸውም አራት ናቸው፤

19የንስር መንገድ በሰማይ፣

የእባብ መንገድ በቋጥኝ፣

የመርከብ መንገድ በባሕር፣

የሰውም መንገድ ከሴት ልጅ ጋር ናቸው።

20“የአመንዝራዪቱ መንገድ ይህ ነው፤

በልታ አፏን በማበስ፣

‘ምንም የሠራሁት ጥፋት የለም’ ትላለች።

21“ምድር በሦስት ነገር ትናወጣለች፤

እንዲያውም መሸከም የማትችላቸው አራት ነገሮች ናቸው፤

22ባሪያ ሲነግሥ፣

ሰነፍ እንጀራ ሲጠግብ፣

23የተጠላች ሴት ባል ስታገባ፣

ሴት ባሪያ በእመቤቷ እግር ስትተካ።

24“በምድር ላይ አራት ነገሮች ትንንሽ ናቸው፤

ሆኖም እጅግ ጠቢባን ናቸው፤

25ጕንዳኖች ደካማ ፍጡራን ናቸው፤

ሆኖም ምግባቸውን በበጋ ያከማቻሉ።

26ሽኮኮዎች ዐቅመ ደካማ ናቸው፤

ሆኖም መኖሪያቸውን በቋጥኞች መካከል ይሠራሉ፤

27አንበጦች ንጉሥ የላቸውም፤

ሆኖም ቅደም ተከተል ይዘው ይጓዛሉ፤

28እንሽላሊት በእጅ ትያዛለች፤

ሆኖም በቤተ መንግሥት ትገኛለች።

29“አረማመዳቸው ግርማዊ የሆነ ሦስት ነገሮች አሉ፤

እንዲያውም በሞገስ የሚጐማለሉ አራት ናቸው፤

30ከአራዊት መካከል ኀይለኛ የሆነው፣

ከምንም ነገር ፊት ግንባሩን የማያጥፈው አንበሳ፤

31ጐርደድ ጐርደድ የሚል አውራ ዶሮ፣ አውራ ፍየል፣

እንዲሁም በሰራዊቱ የታጀበ ንጉሥ ናቸው።30፥31 ወይም ከተቃውሞ የተጠበቀ ንጉሥ

32“ተላላ ሆነህ ራስህን ከፍ ከፍ ካደረግህ፣

ወይም ክፉ ነገር ካቀድህ፣

እጅህን በአፍህ ላይ አድርግ።

33ወተት ሲናጥ ቅቤ እንደሚወጣው፣

አፍንጫን ሲያሹት እንደሚደማ፣

ቍጣን ማነሣሣትም ጥልን ይፈጥራል።”