ማርቆስ 8 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ማርቆስ 8:1-38

ኢየሱስ አራት ሺሕ ሰዎች መገበ

8፥1-9 ተጓ ምብ – ማቴ 15፥32-39

8፥1-9 ተጓ ምብ – ማር 6፥32-44

8፥11-21 ተጓ ምብ – ማቴ 16፥1-12

1በዚያን ጊዜ፣ እንደ ገና ብዙ ሕዝብ ተሰበሰበ። የሚበሉት ምንም ምግብ ስላልነበራቸው ደቀ መዛሙርቱን ወደ እርሱ ጠርቶ፣ እንዲህ አላቸው፤ 2“ከእኔ ጋር ሦስት ቀን ስለ ቈዩና የሚበሉትም ስለሌላቸው እነዚህ ሰዎች ያሳዝኑኛል፤ 3እንዲህ እንደ ተራቡ ወደ ቤታቸው ብሰድዳቸው አንዳንዶቹ ከሩቅ የመጡ ስለ ሆኑ በመንገድ ላይ ዝለው ይወድቃሉ።”

4ደቀ መዛሙርቱም መልሰው፣ “በዚህ ምድረ በዳ እነዚህን ለመመገብ የሚያስችል እንጀራ ከወዴት ይገኛል?” አሉት።

5እርሱም፣ “ስንት እንጀራ አላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው።

እነርሱም፣ “ሰባት” አሉት።

6እርሱም፣ መሬት ላይ እንዲቀመጡ ሕዝቡን አዘዘ፤ ሰባቱን እንጀራ ይዞ ካመሰገነ በኋላ ቈርሶ ለሰዎቹ እንዲያድሉ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው፤ እነርሱም ለሕዝቡ ዐደሉት። 7እንዲሁም ትንንሽ ዓሣዎች ነበሯቸው፤ እርሱም ዓሣዎቹን ባርኮ እንዲያድሏቸው አዘዘ። 8ሕዝቡም በልተው ጠገቡ፤ ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ የተረፈውን ቍርስራሽ ሰባት መሶብ ሙሉ አነሡ። 9በዚያም አራት ሺሕ ያህል ሰዎች ነበሩ፤ ካሰናበታቸውም በኋላ፣ 10ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ዳልማኑታ ወደ ተባለ ስፍራ ሄደ።

11ፈሪሳውያንም ወጥተው ከኢየሱስ ጋር ይከራከሩ ጀመር። ሊፈትኑትም ፈልገው ከሰማይ ምልክት እንዲያሳያቸው ጠየቁት። 12እርሱም በመንፈሱ እጅግ በመቃተት፣ “ይህ ትውልድ ምልክት የሚፈልገው ለምንድን ነው? እውነት እላችኋለሁ፤ ለዚህ ትውልድ ምንም ምልክት አይሰጠውም!” አለ። 13ከዚያም ትቷቸው በጀልባ ወደ ማዶ ተሻገረ።

የፈሪሳውያንና የሄሮድስ እርሾ

14ደቀ መዛሙርቱ እንጀራ መያዝ ስለ ረሱ፣ ከአንድ እንጀራ በቀር በጀልባ ውስጥ ምንም አልነበራቸውም። 15ኢየሱስም፣ “ተጠንቀቁ፤ ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ እርሾ ተጠበቁ” ብሎ አዘዛቸው።

16እነርሱም እርስ በርሳቸው፣ “እንዲህ የሚለን እኮ እንጀራ ስለሌለን ነው” ተባባሉ።

17ኢየሱስም ሐሳባቸውን ዐውቆ፣ እንዲህ አላቸው፤ “እንጀራ ስለሌለን ነው በማለት ምን ያነጋግራችኋል? አሁንም አታስተውሉምን? ልብስ አትሉምን? ወይስ ልባችሁ ደንድኗል? 18ዐይን እያላችሁ አታዩምን? ጆሮ እያላችሁ አትሰሙምን? አታስታውሱምን? 19አምስቱን እንጀራ ለአምስት ሺሕ ሰው በቈረስሁ ጊዜ ስንት መሶብ ሙሉ ትርፍራፊ አነሣችሁ?”

እነርሱም፣ “ዐሥራ ሁለት” አሉት።

20“ሰባቱንስ እንጀራ ለአራት ሺሕ በቈረስሁ ጊዜ ስንት መሶብ ሙሉ ትርፍራፊ አነሣችሁ?” አላቸው።

እነርሱም፣ “ሰባት” አሉት።

21እርሱም፣ “እስከ አሁን አላስተዋላችሁም ማለት ነውን?” አላቸው።

በቤተ ሳይዳ የተፈወሰው ዐይነ ስውር

22ከዚያም ወደ ቤተ ሳይዳ መጡ፤ ጥቂት ሰዎችም አንድ ዐይነ ስውር ወደ ኢየሱስ አምጥተው እንዲዳስሰው ለመኑት። 23እርሱም የዐይነ ስውሩን እጅ ይዞ ከሰፈር ውጭ አወጣው፤ በዐይኖቹም ላይ እንትፍ ብሎበት፣ እጁንም በላዩ ጭኖ፣ “ምን የሚታይህ ነገር አለ?” ሲል ጠየቀው።

24እርሱም ቀና ብሎ አይቶ፣ “ሰዎች እንደ ዛፍ ሲንቀሳቀሱ አያለሁ” አለ።

25ኢየሱስም እንደ ገና እጆቹን በሰውየው ዐይኖች ላይ ጫነ፤ በዚህ ጊዜ ዐይኖቹ በሩ፤ ብርሃኑም ተመለሰለት፤ ሁሉንም ነገር አጥርቶ ማየት ቻለ። 26ከዚያም፣ “ወደ መንደሩ አትግባ! በመንደሩም ለማንም አትናገር8፥26 አንዳንድ ቅጆች በመንደሩም፤ ለማንም አትናገር! የሚለው የላቸውም። ብሎ ወደ ቤቱ ሰደደው።

ጴጥሮስ ስለ ኢየሱስ የነበረው ግንዛቤ

8፥27-29 ተጓ ምብ – ማቴ 16፥13-16ሉቃ 9፥18-20

27ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ፊልጶስ ቂሳርያ መንደሮች ሄደ፤ በመንገድ ላይ ሳሉም ደቀ መዛሙርቱን፣ “ሰዎች እኔን ማን ይሉኛል?” ብሎ ጠየቃቸው።

28እነርሱም፣ “መጥምቁ ዮሐንስ የሚሉህ አሉ፤ ሌሎች ኤልያስ ነው ይሉሃል፤ ሌሎች ደግሞ ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ” ብለው ነገሩት።

29ቀጥሎም፣ “እናንተሳ ማን ትሉኛላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው።

ጴጥሮስም፤ “አንተ ክርስቶስ8፥29 በግሪኩ ክርስቶስ፣ በዕብራይስጡ መሲሕ የሁለቱም ቃላት ትርጕም የተቀባው ማለት ነው። ነህ” አለው።

30ኢየሱስም ስለ እርሱ ለማንም እንዳይናገሩ አስጠነቀቃቸው።

ኢየሱስ ስለ ሞቱ አስቀድሞ ተናገረ

8፥31–9፥1 ተጓ ምብ – ማቴ 16፥21-28ሉቃ 9፥22-27

31ከዚያም የሰው ልጅ ብዙ መከራ እንደሚቀበል፣ በሽማግሌዎች፣ በካህናት አለቆችና በጸሐፍት እንደሚናቅ፣ እንደሚገደል፣ ከሦስት ቀንም በኋላ እንደሚነሣ ያስተምራቸው ጀመር።

32እርሱም ይህን በግልጽ ነገራቸው። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ኢየሱስን ለብቻው ወስዶ ይገሥጸው ጀመር።

33ኢየሱስ ግን ዘወር ብሎ ደቀ መዛሙርቱን እያየ ጴጥሮስን፣ “አንተ ሰይጣን፣ ወደ ኋላዬ ሂድ! አንተ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን ነገር አታስብምና” በማለት ገሠጸው።

34ከዚህ በኋላ፣ ሕዝቡን ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ሊከተለኝ የሚወድድ ቢኖር ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ። 35ነፍሱን8፥35 የግሪኩ ቃል ሕይወት ወይም ነፍስ ማለት ይሆናል። ለማዳን የሚወድድ ሁሉ ያጠፋታል፤ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ነፍሱን የሚያጠፋት ሁሉ ግን ያድናታል። 36ሰው ዓለሙ ሁሉ የእርሱ ቢሆንና ነፍሱን ቢያጣ ምን ይጠቅመዋል? 37ለመሆኑ፣ ሰው ለነፍሱ ምን መተኪያ አለው? 38በዚህ ዘማዊና ኀጢአተኛ ትውልድ መካከል በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ፣ የሰው ልጅም በአባቱ ግርማ፣ ከቅዱሳን መላእክት ጋር ሲመጣ ያፍርበታል።”