ሚክያስ 1 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ሚክያስ 1:1-16

1በይሁዳ ነገሥታት በኢዮአታም፣ በአካዝና በሕዝቅያስ ዘመን ወደ ሞሬታዊው ወደ ሚክያስ የመጣው የእግዚአብሔር ቃል፣ ስለ ሰማርያና ስለ ኢየሩሳሌም ያየው ራእይ ይህ ነው፤

2እናንተ አሕዛብ ሆይ፤ ሁላችሁም ስሙ፤

ምድር ሆይ፤ በውስጧም የምትኖሩ ሁሉ አድምጡ፤

ጌታ ከቅዱስ መቅደሱ፣

ልዑል እግዚአብሔር በእናንተ ላይ ይመሰክርባችኋል።

በሰማርያና በኢየሩሳሌም ላይ የተላለፈ ፍርድ

3እነሆ፤ እግዚአብሔር ከመኖሪያ ስፍራው ይመጣል፤

ወርዶም በምድር ከፍታዎች ላይ ይራመዳል።

4ተራሮች ከሥሩ ይቀልጣሉ፤

ሸለቆዎችም ይሰነጠቃሉ፤

በእሳት ፊት እንዳለ ሰም፣

በገደል ላይ እንደሚወርድ ፈሳሽ ይሆናሉ።

5ይህ ሁሉ የሚሆነው ስለ ያዕቆብ በደል፣

ስለ እስራኤልም ቤት ኀጢአት ነው።

የያዕቆብ በደል ምንድን ነው?

ሰማርያ አይደለችምን?

የይሁዳስ የኰረብታ መስገጃ ምንድን ነው?

ኢየሩሳሌም አይደለችምን?

6“ስለዚህ ሰማርያን የፍርስራሽ ክምር፣

ወይን የሚተከልባትም ስፍራ አደርጋታለሁ፤

ድንጋዮቿን ወደ ሸለቆ አወርዳለሁ፤

መሠረቷንም ባዶ አደርጋለሁ።

7ጣዖቶቿ ሁሉ ይሰባበራሉ፤

ለቤተ መቅደሷ የቀረበው ገጸ በረከት በእሳት ይቃጠላል፤

ምስሎቿን ሁሉ እደመስሳለሁ፤

ገጸ በረከቷን በዝሙት ዐዳሪነት እንደ ሰበሰበች ሁሉ፣

አሁንም ገጸ በረከቷ የዝሙት ዐዳሪነት ዋጋ መቀበያ ይሆናል።”

ልቅሶና ሐዘን

8በዚህ ምክንያት አለቅሳለሁ፤ ዋይ ዋይም እላለሁ፤

ባዶ እግሬንና ዕርቃኔን እሄዳለሁ፤

እንደ ቀበሮ አላዝናለሁ፤

እንደ ጕጕትም አቃስታለሁ።

9ቍስሏ የማይሽር ነውና፤

ለይሁዳ ተርፏል፤

እስከ ሕዝቤ መግቢያ በር፣

እስከ ኢየሩሳሌም እንኳ ደርሷል።

10በጌት1፥10 ጌት የሚለው ቃል በዕብራይስጡ አውራ ከሚለው ጋር ተመሳሳይ አነባበብ አለው። አታውሩት፤

ከቶም አታልቅሱ1፥10 ዕብራይስጡ ከዚህ ጋር ሲስማማ፣ የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም ግን በአኮ ላይ አታልቅሱ ይላል። በአኮ የሚለው የዕብራይስጡ ቃል አለቀሰ ከሚለው የዕብራይስጡ ቃል ጋር ተመሳሳይ አነባበብ አለው።

በቤትዓፍራ1፥10 ቤትዓፍራ ትርጕሙ የትቢያ ቤት ማለት ነው።

በትቢያ ላይ ተንከባለሉ።

11እናንት በሻፊር1፥11 ሻፊር ትርጕሙ አስደሳች ማለት ነው። የምትኖሩ፣

ዕርቃናችሁን ሆናችሁ በኀፍረት ዕለፉ፤

በጸዓናን1፥11 ጸዓናን የሚለው ቃል በዕብራይስጡ ውጣ ከሚለው ጋር ተመሳሳይ አነባበብ አለው። የሚኖሩ

ከዚያ አይወጡም፤

ቤትዔጼል በሐዘን ላይ ናት፤

ለእናንተም መጠጊያ ልትሆን አትችልም።

12ከመከራው መገላገልን በመሻት፣

በማሮት1፥12 ማሮት የሚለው ቃል በዕብራይስጡ መራራ ከሚለው ጋር ተመሳሳይ አነባበብ አለው። የሚኖሩ በሥቃይ

ይወራጫሉ፤

እስከ ኢየሩሳሌም በር ሳይቀር፣

ክፉ ነገር ከእግዚአብሔር ዘንድ መጥቷልና።

13እናንት በለኪሶ1፥13 ለኪሶ የሚለው ቃል በዕብራይስጡ ቡድን ከሚለው ጋር ተመሳሳይ አነባበብ አለው። የምትኖሩ፣

ፈረሶችን ከሠረገላው ጋር አያይዙ፤

ለጽዮን ሴት ልጅ፣

የኀጢአት መጀመሪያ እናንት ነበራችሁ፤

የእስራኤል በደል

በእናንተ ዘንድ ተገኝቷልና።

14ስለዚህ እናንተ ለሞሬሼትጌት፣

ማጫ ትሰጣላችሁ፤

የአክዚብ1፥14 አክዚብ ትርጕሙ አታላይ ወይም ማታለል ማለት ነው። ከተማ፣

ለእስራኤል ነገሥታት መታለያ ትሆናለች።

15እናንት በመሪሳ1፥15 መሪሳ የሚለው ቃል በዕብራይስጡ ድል አድራጊ ከሚለው ጋር ተመሳሳይ አነባበብ አለው። የምትኖሩ

ድል አድራጊ አመጣባችኋለሁ፤

ያ የእስራኤል ክብር የሆነው

ወደ ዓዶላም ይመጣል።

16ደስ ለምትሰኙባቸው ልጆቻችሁ፣

በሐዘን ራሳችሁን ተላጩ፤

ራሳችሁን እንደ አሞራ ራስ ተመለጡት፤

ከእናንተ በምርኮ ይወሰዳሉና።