መዝሙር 8 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

መዝሙር 8:1-9

መዝሙር 8

የፈጣሪ ግርማ በፍጥረቱ ላይ

ለመዘምራን አለቃ፤ በዋሽንት የሚዜም፤ የዳዊት መዝሙር።

1እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ፤

ስምህ በምድር ሁሉ ላይ ምንኛ ግርማዊ ነው!

ክብርህ ከሰማያት በላይ፣

ከፍ ከፍ ብሏል።

2ከልጆችና ጡት ከሚጠቡ ሕፃናት አፍ፣

ምስጋናን8፥2 ወይም ብርታትን አዘጋጀህ፤

ከጠላትህ የተነሣ፣

ባላንጣንና ቂመኛን ጸጥ ታሰኝ ዘንድ።

3የጣቶችህን ሥራ፣

ሰማያትህን ስመለከት፣

በስፍራቸው ያኖርሃቸውን፣

ጨረቃንና ከዋክብትን ሳይ፣

4በዐሳብህ ስፍራ ትሰጠው ዘንድ ሰው ምንድን ነው?

ትጠነቀቅለትም ዘንድ የሰው ልጅ ምንድን ነው?

5ከመላእክት በጥቂት አሳነስኸው፤

የክብርንና የሞገስን ዘውድ አቀዳጀኸው።

6በእጆችህ ሥራ ላይ ሾምኸው፤

ሁሉንም ከእግሩ በታች አስገዛህለት፤

7በጎችንና ላሞችን ሁሉ፣

የዱር አራዊትንም፣

8የሰማይ ወፎችንና

የባሕር ዓሦችን፣

በባሕር ውስጥ የሚርመሰመሱትንም ሁሉ አስገዛህለት።

9እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ፤

ስምህ በምድር ሁሉ ላይ ምንኛ ግርማዊ ነው!