መዝሙር 143 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

መዝሙር 143:1-12

መዝሙር 143

ትሑት ልመና

የዳዊት መዝሙር።

1እግዚአብሔር ሆይ፤ ጸሎቴን ስማ፤

ልመናዬን አድምጥ፤

በታማኝነትህና በጽድቅህም፣

ሰምተህ መልስልኝ።

2ሰው ሆኖ በፊትህ ጻድቅ የለምና፣

ባሪያህን ወደ ፍርድ አታቅርበው።

3ጠላት እስከ ሞት አሳድዶኛል፤

ሕይወቴንም አድቅቆ ከዐፈር ቀላቅሏል፤

ቀደም ብለው እንደ ሞቱትም፣

በጨለማ ውስጥ አኑሮኛል።

4ስለዚህ መንፈሴ በውስጤ ዝላለች፤

ልቤም በውስጤ ደንግጧል።

5የቀድሞውን ዘመን አስታወስሁ፤

ሥራህንም ሁሉ አሰላሰልሁ፤

የእጅህንም ሥራ አውጠነጠንሁ።

6እጆቼን ወደ አንተ ዘረጋሁ፤

ነፍሴም እንደ ምድረ በዳ አንተን ተጠማች። ሴላ

7እግዚአብሔር ሆይ፤ ፈጥነህ መልስልኝ፤

መንፈሴ ደከመች፤

ወደ ጕድጓድ እንደሚወርዱት እንዳልሆን፣

ፊትህን ከእኔ አትሰውር።

8በአንተ ታምኛለሁና፣

በማለዳ ምሕረትህን አሰማኝ፤

ነፍሴን ወደ አንተ አንሥቻለሁና፣

የምሄድበትን መንገድ አሳየኝ።

9እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተን መሰወሪያ አድርጌአለሁና፣

ከጠላቶቼ አድነኝ።

10አንተ አምላኬ ነህና፣

ፈቃድህን እንድፈጽም አስተምረኝ፤

መልካሙ መንፈስህም፣

በቀናችው መንገድ ይምራኝ።

11እግዚአብሔር ሆይ፤ ስለ ስምህ ሕያው አድርገኝ፤

በጽድቅህም ነፍሴን ከመከራ አውጣት።

12ጠላቶቼንም ለእኔ ስላለህ ምሕረት ደምስሳቸው፤

እኔ ባሪያህ ነኝና፣

ነፍሴን የሚያስጨንቋትን ሁሉ አጥፋቸው።