መዝሙር 12 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

መዝሙር 12:1-8

መዝሙር 12

ከክፉ ዓለም ለመዳን የቀረበ ጸሎት

ለመዘምራን አለቃ፤ በስምንተኛው ቅኝት የሚዘመር፤ የዳዊት መዝሙር።

1እግዚአብሔር ሆይ፤ ደግ ሰው የለምና አንተው ድረስልኝ!

ከሰዎችም መካከል አንድ ታማኝ አይገኝም።

2እርስ በርሳቸው ውሸት ይነጋገራሉ፤

በሽንገላ ከንፈርና በሁለት ልብ ይናገራሉ።

3ሸንጋዩን ከንፈር ሁሉ፣

ነገር የምታበዛውንም ምላስ እግዚአብሔር ያጥፋ!

4እነዚህም፣ “በአንደበታችን እንረታለን፤

ከንፈራችን የእኛ ነው፤12፥4 ወይም ከንፈራችን ማረሻ ምላጫችን ነው ጌታችንስ ማነው?”

የሚሉ ናቸው።

5እግዚአብሔር፣ “ስለ ድኾች መከራ፣

ስለ ችግረኞችም ጩኸት፣

አሁን እነሣለሁ፤

በናፈቁትም ሰላም አኖራቸዋለሁ” ይላል።

6የእግዚአብሔር ቃል የጠራ ቃል ነው፤

ሰባት ጊዜ እንደ ተጣራ፣

በምድር ላይ በከውር እንደ ተፈተነ ብር ነው።

7እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ትጠብቀናለህ፤

ከዚህም ትውልድ ለዘላለም ትከልለናለህ።

8በሰዎች ዘንድ ክፋት ከፍ ከፍ ባለ ጊዜ፣

ዐመፀኞች በየአቅጣጫው በዛቻ ይዞራሉ።