መዝሙር 1 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

መዝሙር 1:1-6

አንደኛ መጽሐፍ

ከመዝሙር 1–41

መዝሙር 1

ሁለቱ መንገዶች

1በክፉዎች ምክር የማይሄድ፣

በኀጢአተኞች መንገድ የማይቆም፣

በፌዘኞችም ወንበር የማይቀመጥ፣

ሰው ብፁዕ ነው፤

2ነገር ግን ደስ የሚሰኘው በእግዚአብሔር ሕግ ነው፤

ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያሰላስለዋል።

3እርሱም በወራጅ ውሃ ዳር እንደ ተተከለች፣

ፍሬዋን በየወቅቱ እንደምትሰጥ፣

ቅጠሏም እንደማይጠወልግ ዛፍ ነው፤

የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል።

4ክፉዎች ግን እንዲህ አይደሉም፤

ነገር ግን ነፋስ ጠራርጎ እንደሚወስደው፣

ገለባ ናቸው።

5ስለዚህ ክፉዎች በፍርድ ፊት፣

ኀጢአተኞችም በጻድቃን ማኅበር መቆም አይችሉም፤

6እግዚአብሔር የጻድቃንን መንገድ ይጠብቃልና፤

የክፉዎች መንገድ ግን ትጠፋለች።