መሳፍንት 1 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

መሳፍንት 1:1-36

እስራኤላውያን ከቀሩት ከነዓናውያን ጋር ያደረጉት ውጊያ

1ጕኢያሱ ከሞተ በኋላ እስራኤላውያን፣ “ከነዓናውያንን ለመውጋት ማን ቀድሞ ይውጣልን?” ብለው እግዚአብሔርን ጠየቁ።

2እግዚአብሔርም፣ “ይሁዳ ቀድሞ ይውጣ፤ እነሆ ምድሪቱን በእጁ አሳልፌ ሰጥቼዋለሁ” በማለት መለሰ።

3የይሁዳም ሰዎች ወንድሞቻቸውን የስምዖንን ልጆች፣ “ከነዓናውያንን ለመውጋት ድርሻችን ወደ ሆነው ምድር አብረን እንውጣ፤ እኛም እንደዚሁ ድርሻችሁ ወደ ሆነው ምድር አብረናችሁ እንወጣለን” አሏቸው፤ ስለዚህም የስምዖን ሰዎች አብረዋቸው ሄዱ።

4ይሁዳ በከነዓናውያንና በፌርዛውያን ላይ ወጣ፤ እግዚአብሔርም በእጃቸው አሳልፎ ሰጣቸው፤ ቤዜቅ በተባለውም ስፍራ ዐሥር ሺሕ ሰው ገደሉ። 5በዚህም ኦዶኒቤዜቅን አግኝተው ተዋጉት፤ ከነዓናውያንንና ፌርዛውያንን ድል አደረጉ። 6አዶኒቤዜቅም ከዚያ ሸሸ፤ እነርሱ ግን አሳድደው ያዙት፤ የእጆቹንና የእግሮቹንም አውራ ጣቶች ቈረጡ።

7ከዚያም አዶኒቤዜቅ፣ “የእጃቸውና የእግራቸው አውራ ጣቶች የተቈረጡባቸው ሰባ ነገሥታት ከገበታዬ ሥር የወደቀ ፍርፋሪ ይለቃቅሙ ነበር፤ አሁን ግን እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ የፈጸምሁትን አመጣብኝ” አለ፤ እነርሱም ወደ ኢየሩሳሌም አመጡት፤ በዚያም ሞተ።

8የይሁዳ ሰዎች ኢየሩሳሌምን ወግተው ያዟት፤ ከተማዪቱንም በሰይፍ ስለት መተው፣ በእሳት አቃጠሏት።

9ከዚያም በኋላ የይሁዳ ሰዎች በኰረብታማው አገር፣ በኔጌብና በምዕራቡ ኰረብታ ግርጌ የሚኖሩትን ከነዓናውያንን ለመውጋት ወረዱ፤ 10ቀደም ሲል ቂርያት አርባቅ ተብላ በምትጠራው በኬብሮን በሚኖሩት ከነዓናውያን ላይ ዘመቱ፤ ሴሲንን፣ አኪመንንና ተላሚንን ድል አደረጉ።

11ከዚያም ቀደም ሲል ቅርያትሤፍር ተብላ በምትጠራው በዳቤር በሚኖሩት ሰዎች ላይ ዘመቱ። 12ካሌብም፣ “ቅርያት ሤፍርን ወግቶ ለሚይዛት ሰው ልጄን ዓክሳንን እድርለታለሁ” አለ። 13በዚህ ጊዜ የካሌብ ወንድም የቄኔዝ ልጅ ጎቶንያል ከተማዪቱን ያዘ፤ ካሌብም ልጁን ዓክሳንን ዳረለት።

14እርሷም ወደ ጎቶንያል በመጣች ጊዜ፣ አባቷ የዕርሻ መሬት እንዲሰጠው ይለምነው ዘንድ አጥብቃ ነገረችው፤1፥14 ዕብራይስጡ፣ ሰብዓ ሊቃናትና ቩልጌት አጥብቆ ነገረው ይላሉ። ካሌብም እርሷ ከአህያዋ ላይ እንደ ወረደች “ምን እንዳደርግልሽ ትፈልጊያለሽ?” ሲል ጠየቃት።

15እርሷም፣ “እባክህ አንድ ነገር አድርግልኝ፤ በኔጌብ መሬት እንደ ሰጠኸኝ ሁሉ፣ አሁንም የውሃ ምንጭ ስጠኝ” አለችው፤ ካሌብም የላይኛውንና የታችኛውን ምንጮች ሰጣት።

16የቄናዊው የሙሴ ዐማት ዝርያዎች ከዓራድ አጠገብ በኔጌብ ውስጥ በይሁዳ ምድረ በዳ ካሉት ሕዝቦች ጋር አብረው ለመኖር፣ ከይሁዳ ሰዎች ጋር በመሆን ከባለ ዘንባባዋ ከተማ ከኢያሪኮ ወጡ።

17የይሁዳ ሰዎች ከወንድሞቻቸው ከስምዖን ልጆች ጋር ሆነው በጻፋት በሚኖሩት ከነዓናውያን ላይ ዘመቱ፤ ከተማዪቱንም ፈጽሞ ደመሰሷት1፥17 የዕብራይስጡ ቃል አንድን ነገር ወይም ሰው ሙሉ ለሙሉ በማጥፋት ለእግዚአብሔር መስጠትን የሚያሳይ ነው፤ ስለዚህ ከተማዪቱ ሔርማ1፥17 ሔርማ ማለት ጥፋት ማለት ነው ተብላ ተጠራች። 18ደግሞም የይሁዳ ሰዎች ጋዛ፣ አስቀሎና፣ አቃሮን የተባሉትን ከተሞች ከነግዛቶቻቸው ያዙ1፥18 ዕብራይስጡና የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም አልያዙም ይላሉ።

19እግዚአብሔር ከይሁዳ ሰዎች ጋር ነበር፤ ስለዚህ ኰረብታማውን አገር ያዙ፤ ነገር ግን በረባዳው ምድር የሚኖሩት ሰዎች ከብረት የተሠሩ ሠረገሎች ስለ ነበሯቸው ከዚያ አሳድደው ሊያስወጧቸው አልቻሉም። 20ሙሴ ባዘዘው መሠረት ኬብሮን ለካሌብ ተሰጠች፤ እርሱም ሦስቱን የዔናቅ ልጆች ከውስጧ አሳደደ። 21የብንያም ልጆች በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ኢያቡሳውያንን ከዚያ ሊያስወጧቸው አልቻሉም፤ ስለዚህ ኢያቡሳውያን እስከ ዛሬ ድረስ ከብንያማውያን ጋር በዚያ አብረው ይኖራሉ።

22የዮሴፍ ወገን ደግሞ ቤቴልን ወጉ፤ እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ነበር። 23እነርሱም ቀደም ሲል ሎዛ ትባል ወደ ነበረችው ወደ ቤቴል ሰላዮችን በላኩ ጊዜ፣ 24ሰላዮቹም አንድ ሰው ከከተማዪቱ ሲወጣ አይተው፤ “የከተማዪቱን መግቢያ አሳየን፤ እኛም ምሕረት እናደርግልሃለን” አሉት። 25እርሱም አሳያቸው፤ እነርሱም ከሰውየውና ከቤተ ሰቡ በስተቀር የከተማዪቱን ሕዝብ በሰይፍ ስለት ፈጁ። 26ሰውየውም ወደ ኬጢያውያን ምድር ሄዶ ከተማ ሠራ፤ ስሟንም ሎዛ ብሎ ጠራት፤ እስከ ዛሬም የምትጠራው በዚሁ ስም ነው።

27የምናሴ ነገድ ግን በቤትሳን፣ በታዕናክ፣ በዶር፣ በይብለዓም፣ በመጊዶንና በየአካባቢያቸው ያሉት መንደሮች ነዋሪውን ሕዝብ ስላላስወጡ፣ ከነዓናውያን ኑሯቸውን በዚያው ለማድረግ ወሰኑ። 28እስራኤላውያን በበረቱ ጊዜ ግን ከነዓናውያንን የጕልበት ሥራ እንዲሠሩ አስገደዷቸው እንጂ ፈጽሞ አላስወጧቸውም። 29እንደዚሁም የኤፍሬም ወገኖች በጌዝር የሚኖሩትን ከነዓናውያንን ማስወጣት አልቻሉም፤ ስለዚህ ከነዓናውያን በመካከላቸው እዚያው መኖርን ቀጠሉ። 30ዛብሎንም እንደዚሁ በቂድሮንና በነህሎል የነበሩትን በመካከላቸው የቀሩትን ከነዓናውያንን አላስወጣም፤ ነገር ግን የጕልበት ሥራ እንዲሠሩ አስገደዳቸው። 31አሴርም በዓኮ፣ በሲዶን፣ በአሕላብ፣ በአክዚብ፣ በሒልባ፣ በኣፌቅና በረአብ የሚኖሩትን አላስወጣም፤ 32በዚህ ምክንያት የአሴር ሕዝብ በምድሪቱ ካሉት ከነዓናውያን ጋር አብረው ኖሩ። 33ንፍታሌምም በቤት ሳሚስና በቤትዓናት የሚኖሩትን አላስወጣም፤ ስለዚህ የንፍታሌም ነገድ በምድሪቱ ከሚኖሩት ከነዓናውያን ጋር አብረው ኖሩ፤ ይሁን እንጂ በቤት ሳሚስና በቤትዓናት የሚኖሩት ለእነርሱ የጕልበት ሥራ ተገድደው ይሠሩ ነበር። 34የዳን ነገድ በኰረብታማው ምድር ብቻ እንዲወሰን እንጂ ወደ ሜዳማው አገር እንዲወርድ አሞራውያን አልፈቀዱለትም። 35አሞራውያንም በሔሬስ ተራራ፣ በኤሎንና በሸዓልቢም ኑሯቸውን ቀጠሉ፤ ይሁን እንጂ የዮሴፍ ወገን በበረታ ጊዜ ተገድደው የጕልበት ሥራ ከመሥራት አላመለጡም። 36የአሞራውያን ድንበር አቅራቢያም መተላለፊያ እስከ ሴላዕና ከዚያም የሚያልፍ ነበር።