ሕዝቅኤል 19 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ሕዝቅኤል 19:1-14

ስለ እስራኤል መሳፍንት የወጣ ሙሾ

1“ስለ እስራኤል መሳፍንት ሙሾ አውጣ፤ 2እንዲህም በል፤

“ ‘እናትህ በአንበሶች መካከል እንዴት

ያለች አንበሳ ነበረች!

በደቦል አንበሶች መካከል ተጋደመች፤

ግልገሎቿንም በዚያ አሳደገች።

3ከግልገሎቿ መካከል አንዱን አሳደገችው፤

እርሱም ብርቱ አንበሳ ሆነ።

ግዳይ መንጠቅን ተማረ፤

ሰዎችንም በላ።

4አሕዛብም ስለ እርሱ ሰሙ፤

በጕድጓዳቸውም ገብቶ ተያዘ፤

እነርሱም በስናግ ጐትተው፣

ወደ ግብፅ ምድር ወሰዱት።

5“ ‘ተስፋዋ መጨናገፉን፣

የጠበቀችውም አለመሳካቱን ባየች ጊዜ፣

ከግልገሎቿ ሌላውን ወስዳ፣

ብርቱ አንበሳ አድርጋ አሳደገችው።

6እርሱም በአንበሶች መካከል ተጐማለለ፤

እየበረታም ሄደ፤

ግዳይ መንጠቅን ተማረ፤

ሰዎችንም በላ።

7ምሽጎቻቸውን አወደመ፤19፥7 ከታርጕም (ሰብዐ ሊቃናት ይመ) ጋር ተመሳሳይ ሲሆን፣ ዕብራይስጡ ግን ምሽጎቻቸውን ያውቃል ይላል።

ከተሞቻቸውንም ባድማ አደረገ፤

ምድሪቷና በውስጧ ያሉት ሁሉ፣

ከግሣቱ የተነሣ ተንቀጠቀጡ።

8በዙሪያው ያሉ አሕዛብ ተነሡበት፤

ከየአገሩም ሁሉ ተሰበሰቡበት፤

መረባቸውን ዘረጉበት፤

በጕድጓዳቸውም ገብቶ ተያዘ።

9በስናግም በመጐተት ቀፎ ውስጥ ከትተው፣

ወደ ባቢሎን ንጉሥ አመጡት፤

ድምፁ በእስራኤል ተራሮች ላይ፣

ዳግመኛ እንዳይሰማ፣

በእስር ቤት አኖሩት።

10“ ‘እናትህ በውሃ አጠገብ የተተከለ፣

በዕርሻ ውስጥ ያለ፣19፥10 ከሁለት የጥንት የዕብራይስጥ ቅጆች ጋር ተመሳሳይ ሲሆን አብዛኛዎቹ የጥንት ቅጆች ግን ያንተ ደም ይላሉ።

ከውሃም ብዛት የተነሣ፣

ያፈራና የተንሰራፋ የወይን ተክል

መሰለች።

11ቅርንጫፎቿ ለበትረ መንግሥት

የሚሆኑ፣ ጠንካሮች ነበሩ፤

ጥቅጥቅ ባሉ ቅጠሎች መካከል፣

በቁመቷና በብዙ ቅርንጫፎቿ፣

ዘለግ ብላ፣ ጐልታ ትታይ ነበር።

12ነገር ግን በቍጣ ተነቀለች፤

ወደ ምድርም ተጣለች።

የምሥራቅ ነፋስ አደረቃት፤

ፍሬዎቿንም አረገፈባት።

ብርቱዎቹ ቅርንጫፎቿ ክው አሉ፤

እሳትም በላቸው።

13አሁን ውሃ በተጠማ ደረቅ ምድር፣

በበረሓ ውስጥ ተተከለች።

14ከዋና ቅርንጫፎቿ19፥14 ወይም ከዋና ቅርንጫፎቿ ሥር ከአንዱ እሳት ወጣ፤

ፍሬዋንም በላ።

በትረ መንግሥት የሚሆን፣

አንድም ጠንካራ ቅርንጫፍ አልተረፈም።’

ይህ ሙሾ ነው፤ ለሐዘን እንጕርጕሮም ይሆናል።”