ሕዝቅኤል 1 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ሕዝቅኤል 1:1-28

ሕያዋኑ ፍጡራንና የእግዚአብሔር ክብር

1በሠላሳኛው ዓመት፣1፥1 ወይም ዓመቴ በአራተኛው ወር፣ በአምስተኛው ቀን፣ በኮቦር ወንዝ አጠገብ በምርኮኞች መካከል ሳለሁ፣ ሰማያት ተከፈቱ፤ እኔም የእግዚአብሔርን ራእይ አየሁ።

2ንጉሡ ዮአኪን በተማረከ በአምስተኛው ዓመት፣ በአምስተኛው ቀን፣ 3በባቢሎናውያን1፥3 ወይም በከለዳውያን ምድር በኮቦር ወንዝ አጠገብ፣ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ቡዝ ልጅ፣1፥3 ወይም ወደ ካህኑ ቡዝ ልጅ ወደ ሕዝቅኤል ወደ ካህኑ ወደ ሕዝቅኤል መጣ፤ በዚያ የእግዚአብሔር እጅ በእርሱ ላይ ነበረች።

4እኔም አየሁ፤ ስመለከትም፣ እነሆ ዐውሎ ነፋስ ከሰሜን በኩል መጣ፤ ይኸውም በታላቅ ብርሃን የተከበበ፣ መብረቅን የሚረጭ ታላቅ ደመና ነበረ፤ የእሳቱም መኻል የጋለ ብረት ይመስል ነበር። 5በእሳቱም ውስጥ የአራት ሕያዋን ፍጡራን አምሳያ ነበረ፤ መልካቸውም የሰው ቅርጽ ይመስል ነበር። 6እያንዳንዳቸውም አራት አራት ፊትና አራት አራት ክንፍ ነበራቸው። 7እግራቸው ቀጥ ያለ ነበር፤ ኰቴያቸውም እንደ ጥጃ ኰቴ ያለ ሲሆን፣ እንደ ተወለወለ ናስም ያብለጨልጭ ነበር። 8በአራቱ ጐኖቻቸው ባሉት ክንፎቻቸው ሥር የሰው እጅ ነበራቸው። አራቱም ፊቶችና ክንፎች ነበሯቸው፤ 9ክንፎቻቸውም እርስ በርስ ይነካኩ ነበር። እያንዳንዱም ቀጥ ብሎ ይሄድ ነበር፤ ወደ ኋላቸውም ዞር ብለው አይመለከቱም ነበር።

10ፊታቸውም እንዲህ ነበር፤ አራቱም እያንዳንዳቸው የሰው ፊት ነበራቸው፤ በቀኝ በኩል የአንበሳ ፊት፣ በግራ በኩልም የበሬ ፊት ነበራቸው፤ እያንዳንዳቸውም ደግሞ የንስር ፊት ነበራቸው። 11እንግዲህ ፊታቸው ይህን ይመስል ነበር፤ ክንፋቸውም ወደ ላይ ተዘርግቶ ነበር፤ እያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት ክንፍ ነበራቸው፤ የእያንዳንዱም ክንፍ የሌላውን ክንፍ ይነካ ነበር፤ ሁለቱ ክንፎቻቸው ሰውነታቸውን ይሸፍኑ ነበር። 12እያንዳንዱ ቀጥ ብሎ ወደ ፊት ይሄድ ነበር፤ ወደ ኋላም ሳይዞር መንፈስ ወደሚሄድበት ሁሉ ይሄድ ነበር። 13የሕያዋን ፍጡራኑ መልክም እንደሚነድ የከሰል ፍምና የተቀጣጠለ ችቦ ይመስል ነበር፤ በፍጡራኑ መካከል እሳት ወዲያ ወዲህ ይንቀሳቀስ ነበር፤ ብርሃኑም ደማቅ ነበር፤ ከእሳቱም ውስጥ መብረቅ ይወጣ ነበር። 14ፍጡራኑም እንደ መብረቅ ብልጭታ ፍጥነት ወዲያ ወዲህ ይወረወሩ ነበር።

15ሕያዋን ፍጡራኑን ስመለከታቸው፣ አራት ፊቶች ባሉት በእያንዳንዱ ፍጡር አጠገብ አንዳንድ መንኰራኵር በምድር ላይ አየሁ። 16የመንኰራኵሮቹ መልክና አሠራር እንዲህ ነበር፤ እንደ ቢረሌ ያንጸባርቁ ነበር፤ የአራቱም ቅርጽ ተመሳሳይ ሆኖ፤ እያንዳንዱ መንኰራኵር በመንኰራኵር ውስጥ ተሰክቶ የተሠራ ይመስል ነበር። 17በሚሄዱበት ጊዜም፣ ፍጡራኑ ወደሚዞሩበት ወደ አራቱ አቅጣጫ ሁሉ መንቀሳቀስ ይችሉ ነበር፤ ፍጡራኑ በሚሄዱበትም ጊዜ መንኰራኵሮቹ ወዲያና ወዲህ1፥17 ወይም ወደ ሌላ አይሉም ነበር። 18የመንኰራኵሮቹ ክብ ጠርዝ ረዥምና አስፈሪ ነበር፤ የአራቱም መንኰራኵሮች ክብ ጠርዝ ዙሪያውን በዐይኖች የተሞላ ነበር።

19ሕያዋኑ ፍጡራን ሲንቀሳቀሱ፣ በአጠገባቸው ያሉ መንኰራኵሮችም ይንቀሳቀሱ ነበር፤ ሕያዋኑ ፍጡራን ከምድር ከፍ ከፍ ሲሉ፣ መንኰራኵሮቹም አብረዋቸው ከፍ ከፍ ይሉ ነበር። 20መንፈስ ወደሚሄድበት ሁሉ ይሄዳሉ፤ የሕያዋኑ ፍጡራን መንፈስ በውስጣቸው ስላለ መንኰራኵሮቹ አብረዋቸው ይነሣሉ፤ 21ፍጡራኑ ሲንቀሳቀሱ ይንቀሳቀሳሉ፤ ፍጡራኑ ቀጥ ብለው ሲቆሙ እነርሱም ይቆማሉ፤ ፍጡራኑ ከምድር ከፍ ከፍ ሲሉ፣ የሕያዋኑ ፍጡራን መንፈስ በውስጣቸው ስላለ መንኰራኵሮቹ አብረዋቸው ይነሣሉ።

22ከሕያዋኑ ፍጡራን ራስ በላይ የሚያስፈራና፤ እንደ በረዶ የሚያንጸባርቅ ጠፈር የሚመስል ነገር ነበር። 23ከጠፈሩም በታች የአንዱ ክንፍ ወደ ሌላው ተዘርግቶ ነበር፤ እያንዳንዱም ሰውነቱን የሚሸፍንበት ሁለት ክንፍ ነበረው። 24ፍጡራኑ በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ የክንፎቻቸውን ድምፅ ሰማሁ፤ ድምፁም እንደሚጐርፍ ውሃ ጩኸት፣ ሁሉን እንደሚችል1፥24 በዕብራይስጡ ሻዳይ ይላል አምላክ ድምፅና እንደ ሰራዊት ውካታ ነበር። መንቀሳቀሳቸውን ሲያቆሙም ክንፎቻቸውን ዝቅ ያደርጉ ነበር።

25መንቀሳቀሳቸውን አቁመው ክንፎቻቸውን ዝቅ እንዳደረጉ፣ ከራሳቸው በላይ ካለው ጠፈር ድምፅ ተሰማ። 26ከራሳቸው በላይ ካለው ጠፈር ከፍ ብሎ የሰንፔር1፥26 ወይም ላፒስ ላዙሊ ዙፋን የሚመስል ነገር ነበር፤ በዙፋኑም ላይ የሰው መልክ የሚመስል ነበር። 27ወገቡ ከሚመስለው ጀምሮ ወደ ላይ በእሳት መካከል እንዳለ የጋለ ብረት፣ ከወገቡም በታች እሳት ይመስል እንደ ነበር አየሁ፤ ደማቅ ብርሃንም በዙሪያው ነበር። 28በዝናብ ቀን በደመና ውስጥ እንደሚታየው ቀስተ ደመና በዙሪያው ያለው ጸዳል እንዲሁ ነበር።

ይህም የእግዚአብሔር ክብር መልክ አምሳያ ነበረ። ባየሁትም ጊዜ በግንባሬ ተደፋሁ፤ የአንድ ተናጋሪን ድምፅ ሰማሁ።