ሆሴዕ 5 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ሆሴዕ 5:1-15

በእስራኤል ላይ የተነገረ ፍርድ

1“እናንተ ካህናት፤ ይህን ስሙ!

እናንት እስራኤላውያን፤ አስተውሉ!

የንጉሥ ቤት ሆይ፤ ስሙ!

ይህ ፍርድ በእናንተ ላይ ነው፤

በምጽጳ ወጥመድ፣

በታቦርም ላይ የተዘረጋ መረብ ሆናችኋልና።

2ዐመፀኞች በግድያ በርትተዋል፤

ሁሉንም እቀጣቸዋለሁ።

3ስለ ኤፍሬም ሁሉን ዐውቃለሁ፤

እስራኤልም ከእኔ የተሰወረች አይደለችም፤

ኤፍሬም፣ አንተ አሁን አመንዝረሃል፤

እስራኤልም ረክሳለች።

4“የሠሩት ሥራ፣ ወደ አምላካቸው እንዲመለሱ

አይፈቅድላቸውም፤

የአመንዝራነት መንፈስ በልባቸው አለ፤

እግዚአብሔርንም አያውቁትም።

5የእስራኤል ትዕቢት በራሷ ላይ ይመሰክራል፤

እስራኤላውያንና ኤፍሬምም በኀጢአታቸው ይሰናከላሉ፤

ይሁዳም ደግሞ አብሯቸው ይሰናከላል።

6እግዚአብሔርን ለመሻት፣

የበግና የፍየል መንጋ እንዲሁም የቀንድ ከብቶቻቸውን ነድተው ሲሄዱ፣

እርሱ ስለ ተለያቸው፣

ሊያገኙት አይችሉም።

7ለእግዚአብሔር ታማኞች አልሆኑም፤

ዲቃሎች ወልደዋልና፤

ስለዚህ የወር መባቻ በዓላቸው፤

እነርሱንና ዕርሻቸውን ያጠፋል።

8“በጊብዓ መለከትን፣

በራማ እንቢልታን ንፉ፤

በቤትአዌን የማስጠንቀቂያ ድምፅ አሰሙ፤

‘ብንያም ሆይ፤ መጡብህ!’ በሉ።

9በቅጣት ቀን፣

ኤፍሬም ባድማ ይሆናል፣

በእስራኤል ነገዶች መካከል፣

በርግጥ የሚሆነውን ዐውጃለሁ።

10የይሁዳ መሪዎች፣

የወሰን ድንጋዮችን እንደሚነቅሉ ሰዎች ናቸው፤

እንደ ጐርፍ ውሃ፣

ቍጣዬን በላያቸው ላይ አፈስሳለሁ።

11ጣዖትን መከተል በመውደዱ፣5፥11 በዕብራይስጡ የዚህ ቃል ትርጕም አይታወቅም።

ኤፍሬም ተጨቍኗል፤

በፍርድም ተረግጧል።

12እኔ ለኤፍሬም እንደ ብል፣

ለይሁዳም ሕዝብ እንደ ነቀዝ ሆኛለሁ።

13“ኤፍሬም ሕመሙን፣

ይሁዳም ቍስሉን ባየ ጊዜ፣

ኤፍሬም ወደ አሦር ሄደ፤

ርዳታ ለመጠየቅ ወደ ታላቁ ንጉሥ መልእክተኛ ላከ፤

እርሱ ግን ሊያድናችሁ፣

ቍስላችሁንም ሊፈውስ አይችልም።

14እኔ ለኤፍሬም እንደ አንበሳ፣

ለይሁዳም እንደ ደቦል አንበሳ እሆናለሁና፤

ሰባብሬና አድቅቄአቸው እሄዳለሁ፤

ነጥቄ እወስዳቸዋለሁ፤ ማንም ሊያድናቸው አይችልም።

15በደላቸውንም እስኪያውቁ ድረስ፣

ወደ ስፍራዬ እመለሳለሁ፤

ፊቴን ይሻሉ፤

በመከራቸውም አጥብቀው

ይፈልጉኛል።”